ኦሪት ዘሌዋውያን 14:1-18

ኦሪት ዘሌዋውያን 14:1-18 አማ54

እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ በመንጻቱ ቀን የለምጻሙ ሕግ ይህ ይሆናል፤ ወደ ካህኑ ይወስዱታል። ካህኑም ከሰፈር ወደ ውጭ ይወጣል፤ ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ የለምጹ ደዌ ከለምጻሙ ላይ ቢጠፋ፥ ካህኑ ስለሚነጻው ሰው ሁለት ንጹሐን ወፎች በሕይወታቸው፥ የዝግባም እንጨት፥ ቀይ ግምጃም፥ ሂሶጵም ያመጣ ዘንድ ያዝዛል። ካህኑም ከሁለቱ ወፎች አንዱን በሸክላ ዕቃ ውስጥ በምንጭ ውኃ ላይ ያርድ ዘንድ ይዝዛል። ሕያውንም ወፍ ዝግባውንም እንጨት ቀዩንም ግምጃ ሂሶጱንም ወስዶ ከሕያው ወፍ ጋር በምንጭ ውኃ ላይ በታረደው ወፍ ደም ውስጥ ይነክራቸዋል። ከለምጹ በሚነጻው ሰው ላይ ሰባት ጊዜ ይረጫል፤ ንጹሕም ነው ይለዋል፥ ሕያውንም ወፍ ወደ ሜዳ ይለቅቀዋል። የነጻውም ሰው ልብሱን ያጥባል፥ ጠጕሩንም ሁሉ ይላጫል፥ በውኃም ይታጠባል፥ ንጹሕም ይሆናል። ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈር ይገባል፥ ነገር ግን ከድንኳኑ በውጭ ሆኖ ሰባት ቀን ይቀመጣል። በሰባተኛውም ቀን ጠጕሩን ሁሉ ይላጫል፤ ራሱንም፥ ጢሙንም፥ ቅንድቡንም፥ የገላውንም ጠጕር ሁሉ ይላጫል፤ ልብሱንም፥ ገላውንም በውኃ ያጥባል፤ ንጹሕም ይሆናል። በስምንተኛውም ቀን ነውር የሌለባቸውን ሁለት ተባት ጠቦት፥ ነውር የሌለባትንም አንዲት የዓመት እንስት ጠቦት፥ ስለ እህልም ቍርባን ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሦስት እጅ የሆነ በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ አንድ የሎግ መስፈሪያም ዘይት ይወስዳል። የሚያነጻውም ካህን እነዚህን ነገሮች የሚነጻውንም ሰው በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አጠገብ በእግዚአብሔር ፊት ያኖራቸዋል። ካህኑም አንዱን ጠቦት ወስዶ ስለ በደል መሥዋዕት ያቀርበዋል፥ ያንንም የሎግ መስፈሪያ ዘይት፤ ስለ መወዝወዝ ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ይወዘውዘዋል። የኃጢአትን መሥዋዕትና የሚቃጠለውን መሥዋዕት በሚያርዱበት በተቀደሰው ስፍራ ጠቦቱን ያርደዋል፤ የኃጢአቱ መሥዋዕት ለካህኑ እንደሚሆን፥ እንዲሁ የበደል መሥዋዕት ነው፤ ቅዱሰ ቅዱሳን ነው። ካህኑም ከበደል መሥዋዕት ደም ወስዶ የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት ያስነካዋል። ካህኑም ከዘይቱ ከሎግ መስፈሪያው ወስዶ በግራ እጁ ውስጥ ያፈስሰዋል። ካህኑም በግራ እጁ ውስጥ ባለው ዘይት ቀኝ ጣቱን ነክሮ ከዘይቱ በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ጊዜ በጣቱ ይረጫል። ካህኑም በእጁ ውስጥ ከቀረው ዘይት የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት የበደል መሥዋዕት ደም ባረፈበት ላይ ያስነካዋል። በካህኑም እጅ ውስጥ የቀረውን ዘይት በሚነጻው ሰው ራስ ላይ ያደርግበታል፤ ካህኑም በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል።