እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አንድ ሰው ከሥጋ ደዌ በሽታ ከዳነ በኋላ የሚፈጸምለት የመንጻት ሥርዓት ይህ ነው፦ ንጹሕ መሆኑ በሚነገርለት ቀን ወደ ካህኑ እንዲቀርብ ይደረግ፤ ካህኑም ከሰፈር ወደ ውጪ አውጥቶ ይመርምረው፤ በሽታው የተፈወሰ ከሆነ፥ ካህኑ ንጹሕ የሆኑ ሁለት ወፎችና የሊባኖስ ዛፍ እንጨት ቊራጭ፥ ቀይ የግምጃ ክርና የሂሶጵ ቅጠል ጨምሮ እንዲያመጣ ይዘዘው። ከዚህም በኋላ ካህኑ ከወፎቹ አንዱን ንጹሕ የምንጭ ውሃ ባለበት ጐድጓዳ የሸክላ ዕቃ ላይ እንዲታረድ ይዘዝ፤ ሌላውንም ወፍ ወስዶ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት ቊራጭ፥ ከቀዩ ከፈይ ክርና ከሂሶጱ ቅጠል ጋር በአንድነት ቀድሞ በታረደው ወፍ ደም ውስጥ ይንከረው፤ ደሙንም ከሥጋ ደዌ በሚነጻው ሰው ላይ ሰባት ጊዜ ይርጭ፤ ከዚያም በኋላ ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅለታል፤ በሕይወት ያለውንም ወፍ ወደ ሜዳ እንዲበር ይለቀዋል። ከበሽታው የነጻው ሰው ልብሱን ያጥባል፤ ጠጒሩን ሁሉ ይላጫል፤ ሰውነቱንም ይታጠባል፤ ከዚያም በኋላ የነጻ ሆኖ ወደ ሰፈር ይገባል፤ ነገር ግን እስከ ሰባት ቀን ከራሱ ድንኳን ውጪ መቈየት አለበት። በሰባተኛውም ቀን እንደገና ራሱን፥ ጢሙን፥ ቅንድቡንና በሌላውም ሰውነት ላይ ያለውን ጠጒር ሁሉ ተላጭቶ ልብሱን በውሃ ይጠብ፤ ሰውነቱንም ይታጠብ፤ ከዚያም በኋላ የነጻ ይሆናል። “በስምንተኛውም ቀን ምንም ነውር የሌለባቸውን ሁለት ተባዕት የበግ ጠቦቶችና አንድ ዓመት የሆናት አንዲት ቄብ ያምጣ፤ ከዚህም ጋር በወይራ ዘይት የተለወሰ ሦስት ኪሎ ግራም ዱቄትና የሊትር አንድ ሦስተኛ የሆነ የወይራ ዘይት ያምጣ። ካህኑም ሰውየውን ካመጣቸው ከእነዚህ ሁሉ መባዎች ጋር ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወስዶ በእግዚአብሔር ፊት ያቀርባል፤ ከዚህም በኋላ ካህኑ ተባዕት ከሆኑት ከሁለቱ የበግ ጠቦቶች አንዱን የሊትር አንድ ሦስተኛ ከሆነው የወይራ ዘይት ጋር ወስዶ የበደል ስርየት መሥዋዕት አድርጎ ያቀርባል። ካህኑ ይህን በመወዝወዝ ለእግዚአብሔር ልዩ መባ አድርጎ ያቀርበዋል። ጠቦቱንም ለኃጢአት ስርየት መሥዋዕትና ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርቡ እንስሶች በሚታረዱበት ቅዱስ ስፍራ ያርደዋል፤ ይህንንም የሚያደርግበት ምክንያት የበደል ዕዳ መሥዋዕት ልክ ለኃጢአት ስርየት እንደሚቀርበው መሥዋዕት የካህኑ ድርሻ ሆኖ ስለሚሰጥ ነው፤ እርሱም እጅግ የተቀደሰ ነው። ካህኑም ከጠቦቱ ደም ጥቂት ወስዶ የነጻ መሆኑን በሚያስታውቅለት ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንና የቀኝ እግሩን አውራ ጣቶች ይቀባ። ካህኑ ከወይራው ዘይት ጥቂት ወስዶ በግራ እጁ መዳፍ ላይ ያፍስስ፤ በቀኝ እጁ ጫፍ እያጠቀሰ ከእርሱ ጥቂቱን በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ጊዜ ይርጨው። በእጁ መዳፍ ላይ ካለውም ዘይት ጥቂት ወስዶ የነጻ መሆኑን ለማስታወቅ የሚነጻውን ሰው ቀኝ ጆሮ ጫፍ፥ የቀኝ እጁንና የቀኝ እግሩን አውራ ጣቶች ይቀባ፤ በእጁ መዳፍ ላይ የተረፈውንም ዘይት በሚነጻው ሰው ራስ ላይ ያፍስሰው፤ በዚህም ዐይነት ካህኑ በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል።
ኦሪት ዘሌዋውያን 14 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘሌዋውያን 14:1-18
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች