እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ለምጻሙ ሰው እንዲነጻ ወደ ካህኑ በሚወስዱት ጊዜ ሥርዐቱ እንዲህ ነው፦ ካህኑ ከሰፈር ወደ ውጭ ወጥቶ ይመርምረው፤ ሰውየው ከተላላፊ የቈዳ በሽታው ተፈውሶ ከሆነ፣ ካህኑ ስለሚነጻው ሰው፣ ለመብላት ከተፈቀደው የወፍ ዐይነት ሁለት ከነሕይወታቸው፣ የዝግባ ዕንጨት፣ ደመቅ ያለ ቀይ ድርና ሂሶጵ እንዲያመጣ ይዘዝ። ካህኑም ከወፎቹ አንዱን በሸክላ ዕቃ ውስጥ ባለ የምንጭ ውሃ ላይ እንዲታረድ ይዘዝ። በሕይወት ያለውንም ወፍ ከዝግባው ዕንጨት፣ ደመቅ ካለው ቀይ ድርና ከሂሶጵ ጋራ በምንጩ ውሃ ላይ በታረደው ወፍ ደም ውስጥ ይንከር። ከተላላፊ በሽታ የሚነጻውንም ሰው ሰባት ጊዜ ይርጨው፤ መንጻቱንም ያስታውቅ፤ በሕይወት ያለውንም ወፍ ወደ ውጭ ይልቀቀው። “የሚነጻው ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ጠጕሩን በሙሉ ይላጭ፤ ሰውነቱን በውሃ ይታጠብ፤ በሥርዐቱም መሠረት ንጹሕ ይሆናል። ከዚህም በኋላ ወደ ሰፈር መግባት ይችላል፤ ነገር ግን ሰባት ቀን ከድንኳኑ ውጭ ይቈይ። በሰባተኛውም ቀን ጠጕሩን በሙሉ ይላጭ፤ ራሱን፣ ጢሙን፣ ቅንድቡንና ሌላውንም ጠጕር ሁሉ ይላጭ። ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱን በውሃ ይታጠብ፤ ንጹሕም ይሆናል። “በስምንተኛው ቀን እንከን የሌለባቸውን ሁለት ተባዕት የበግ ጠቦቶችና ነውር የሌለባትን አንዲት የአንድ ዓመት እንስት በግ ያቅርብ፤ እንዲሁም ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ የኢፍ ሦስት ዐሥረኛ የላመ ዱቄት ያቅርብ፤ ደግሞ አንድ ሎግ ዘይት ያምጣ። ሰውየው የነጻ መሆኑን የሚያስታውቀው ካህን የሚነጻውን ሰውና መሥዋዕቶቹን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ በእግዚአብሔር ፊት ያቅርብ። “ካህኑም ከተባዕቱ ጠቦቶች በመውሰድ ከሎግ ዘይቱ ጋራ የበደል መሥዋዕት አድርጎ ያቅርብ፤ የሚወዘወዝ መሥዋዕት በማድረግም በእግዚአብሔር ፊት ይወዝውዛቸው። ጠቦቱንም፣ የኀጢአት መሥዋዕትና የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበት በተቀደሰው ስፍራ ይረደው፤ የኀጢአት መሥዋዕቱ ለካህኑ እንደሚሰጥ ሁሉ የበደል መሥዋዕቱም ለካህኑ ይሰጥ፤ ይህም እጅግ የተቀደሰ ነው። ካህኑ ከበደል መሥዋዕቱ ደም ወስዶ የሚነጻውን ሰው ቀኝ ጆሮ ታችኛውን ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣትና የቀኝ እግሩን አውራ ጣት ያስነካ። ካህኑም ከሎግ ዘይት ወስዶ በራሱ ግራ እጅ መዳፍ ውስጥ ይጨምር፤ ካህኑም የቀኝ እጁንም ጣት በመዳፉ በያዘው ዘይት ውስጥ በመንከር በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ጊዜ በጣቱ ይርጭ። ካህኑ በመዳፉ ውስጥ ከቀረው ዘይት ጥቂቱን ወስዶ የሚነጻውን ሰው ቀኝ ጆሮ ታችኛውን ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣትና የቀኝ እግሩን አውራ ጣት በበደል መሥዋዕቱ ደም ላይ ደርቦ ይቅባ። ካህኑም በመዳፉ ላይ የቀረውን ዘይት በሚነጻው ሰው ራስ ላይ ያድርግ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ያስተስርይለት።
ዘሌዋውያን 14 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘሌዋውያን 14
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘሌዋውያን 14:1-18
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች