በበዓሉም ሊሰግዱ ከመጡት አንዳንዶቹ የግሪክ ሰዎች ነበሩ፤ እነርሱም ከገሊላ ቤተ ሳይዳ ወደሚሆን ወደ ፊልጶስ መጥተው፦ “ጌታ ሆይ፥ ኢየሱስን ልናይ እንወዳለን” ብለው ለመኑት። ፊልጶስም መጥቶ ለእንድርያስ ነገረው፤ እንድርያስና ፊልጶስ መጥተው ለኢየሱስ ነገሩት። ኢየሱስስም መለሰላቸው፥ እንዲህ ሲል፦ “የሰው ልጅ ይከብር ዘንድ ሰዓቱ ደርሶአል። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች። ነፍሱን የሚወድ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም በዚህ ዓለም የሚጠላ ለዘላለም ሕይወት ይጠብቃታል። የሚያገለግለኝ ቢኖር ይከተለኝ፥ እኔም ባለሁበት አገልጋዬ ደግሞ በዚያ ይሆናል፤ የሚያገለግለኝም ቢኖር አብ ያከብረዋል። “አሁን ነፍሴ ታውካለች ምንስ እላለሁ? አባት ሆይ፥ ከዚህ ሰዓት አድነኝ። ነገር ግን ስለዚህ ወደዚህ ሰዓት መጣሁ። አባት ሆይ፥ ስምህን አክብረው።” ስለዚህም፦ “አከበርሁት ደግሞም አከብረዋለሁ” የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ። በዚያ ቆመው የነበሩትም ሕዝብ በሰሙ ጊዜ፦ “ነጐድጓድ ነው” አሉ፤ ሌሎች፦ “መልአክ ተናገረው” አሉ። ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል፦ “ይህ ድምፅ ስለ እናንተ መጥቶአል እጂ ስለ እኔ አይደለም። አሁን የዚህ ዓለም ፍርድ ደርሶአል፤ አሁን የዚህ ዓለም ገዥ ወደ ውጭ ይጣላል፤ እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደ ሆነ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ።” በምን ዓይነትም ሞት ይሞት ዘንድ እንዳለው ሲያመለክታቸው ይህን ተናገረ። እንዲህ ሕዝቡ፦ “እኛስ ክርስቶስ ለዘላለም እንዲኖር ከሕጉ ሰምተናል አንተስ የሰው ልጅ ከፍ ከፍ ይል ዘንድ እንዲያስፈልገው እንዴት ትላላህ? ይህ የሰው ልጅ ማን ነው?” ብለው መለሱለት። ኢየሱስም፦ “ገና ጥቂት ጊዜ ብርሃን ከእናንተ ጋር ነው። ጨለማ እንዳይደርስባችሁ ብርሃን ሳለላችሁ ተመላለሱ፤ በጨለማም የሚመላለስ ወዴት እንዲሄድ አያውቅም። የብርሃን ልጆች እንድትሆ ብርሃን ሳለላችሁ በብርሃኑ እመኑ” አላቸው። ኢየሱስም ይህን ተናግሮ ሄደና ተሰወረባቸው። ነገር ግን ይህን ያህል ምልክት በፊታቸው ምንም ቢያደርግ፤ ነቢዩ ኢሳይያስ፦ “ጌታ ሆይ፥ ማን ምስክርነታችንን አመነ? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገለጠ?” ብሎ የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ በእርሱ አላመኑም። ኢሳይያስ ደግሞ፦ “በዓይኖቻቸው እንዳያዩ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ እንዳይመለሱም፥ እኔም እንዳልፈውሳቸው፥ ዓኖቻቸውን አሳወረ ልባቸውውንም አደነደነ” ብሎአልና ስለዚህ ማመን አቃታቸው። ክብሩን ስለ አየ ኢሳይያስ ይህን አለ፥ ስለ እርሱም ተናገረ። ከዚህም ጋር ከአለቆች ደግሞ ብዙዎች በእርሱ አመኑ፤ ነገር ግን ከምኵራብ እንዳያስወጡአቸው በፈሪሳውያን ምክንያት አልመሰከሩለትም፤ ከእግዚአብሔር ክብር ይልቅ የሰውን ክብር ወደዋልና። ኢየሱስም ጮኸ፥ እንዲህም አለ፦ “በእኔ የሚያምን በላከኝ ማመኑ ነው እንጂ በእኔ አይደለም፤ እኔንም የሚያይ የላከኝን ያያል። በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር እኔ ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ። ዓለምን ላድን እንጂ በዓለም ልፈርድ አልመጣሁምና ቃሌን ሰምቶ የማይጠብቀው ቢኖር የምፈርድበት እኔ አይደለሁም። የሚጥለኝ ቃሌንም የማይቀበለው እርሱ የሚፈርድበት አለው፤ እኔ የተናገርሁት ቃል እርሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል። እኔ ከራሴ አልተናገርሁምና፤ ነገር ግን የላከኝ አብ እርሱ የምለውን የምናገረውንም ትእዛዝ ሰጠኝ። ትእዛዙም የዘላለም ሕይወት እንደ ሆነች አውቃለሁ። ስለዚህ እኔ የምናገረውን አብ እንደ ነገረኝ እንዲሁ እናገራለሁ።”
የዮሐንስ ወንጌል 12 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ወንጌል 12:20-50
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos