ዮሐንስ 12:20-50
ዮሐንስ 12:20-50 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከጽርዕ ሰዎችም ይሰግዱ ዘንድ ለበዓል የወጡ ነበሩ። እነርሱም ከገሊላ፥ የቤተ ሳይዳ ሰው ወደ ሆነው ወደ ፊልጶስ ሄደው፥ “አቤቱ፥ ጌታ ኢየሱስን ልናየው እንወድዳለን” ብለው ለመኑት። ፊልጶስም ሄዶ ለእንድርያስ ነገረው፤ እንድርያስና ፊልጶስም ሄደው ለጌታችን ለኢየሱስ ነገሩት። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “አሁን የሰው ልጅ ይከብር ዘንድ ጊዜው ደረሰ። እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ የስንዴ ቅንጣት በምድር ላይ ካልወደቀችና ካልሞተች ብቻዋን ትኖራለች፤ ከሞተች ግን ብዙ ፍሬን ታፈራለች። ነፍሱን የሚወዳት ይጥላታል፤ በዚህ ዓለም ነፍሱን የሚጥላትም ለዘለዓለም ሕይወት ይጠብቃታል። እኔን የሚያገለግለኝ ካለ ይከተለኝ፤ የሚያገለግለኝ እኔ ባለሁበት በዚያ ይኖራልና፤ እኔን የሚያገለግለኝንም አብ ያከብረዋል። “አሁንስ ነፍሴ ታወከች፤ ግን ምን እላለሁ? አባት ሆይ፥ ከዚች ሰዓት ነፍሴን አድናት፤ ነገር ግን ስለዚህ ነገር ለዚች ሰዓት ደርሻለሁ። አባት ሆይ፥ ልጅህን አክብረው።” ከሰማይም፥ “አከበርሁህ፤ ደግሞም እንደገና አከብርሃለሁ፤” የሚል ቃል መጣ። በዚያ ቆመው ይሰሙ የነበሩ ሕዝብ ግን “ነጐድጓድ ነው” አሉ፤ “መልአክ ተናገረው” ያሉም አሉ። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “ይህ ቃል የመጣ ስለ እናንተ ነው እንጂ ስለ እኔ አይደለም። አሁን የዚህ ዓለም ፍርድ ደረሰ፤ ከእንግዲህስ ወዲህ የዚህን ዓለም ገዥ ወደ ውጭ አስወጥተው ይሰዱታል። እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ካልሁ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ።” ይህንም ያለ በምን ዐይነት ሞት ይሞት ዘንድ እንዳለው ሲያመለክታቸው ነው። ሕዝቡም፥ “እኛስ ክርስቶስ ለዘለዓለም እንዲኖር በኦሪት ሰምተን ነበር፤ እንግዲህ እንዴት አንተ ‘የሰው ልጅ ከፍ ከፍ ይል ዘንድ አለው’ ትለናለህ? እንግዲህ ይህ የሰው ልጅ ማን ነው?” ብለው መለሱለት። ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፥ “ ገና ለጥቂት ጊዜ ብርሃን ከእናንተ ጋር ነው፤ በጨለማ የሚመላለስ የሚሄድበትን አያውቅምና ጨለማ እንዳያገኛችሁ ብርሃን ሳለላችሁ ተመላለሱ፤ የብርሃን ልጆች ትሆኑ ዘንድ ብርሃን ሳለላችሁ በብርሃን እመኑ” ጌታችን ኢየሱስም ይህን ተናግሮ ሄደ፤ ተሰወራቸውም። ይህንም ያህል ተአምራት በፊታቸው ሲያደርግ አላመኑበትም። “አቤቱ፥ ምስክርነታችንን ማን ያምነናል? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገለጠ?” ያለው የነቢዩ የኢሳይያስ ቃል ይደርስ ዘንድ። ስለዚህም ማመን ተሳናቸው፤ ኢሳይያስ ዳግመኛ እንዲህ ብሎአልና። “በዐይናቸው አይተው፥ በልባቸውም አስተውለው እንዳይመለሱና እንዳልፈውሳቸው ዐይኖቻቸው ታወሩ፤ ልባቸውም ደነደነ።” ኢሳይያስ ጌትነቱን አይቶአልና፥ ይህን ተናገረ፤ ስለ እርሱም መሰከረ። ከሕዝቡ አለቆችም ያመኑበት ብዙዎች ነበሩ፤ ነገር ግን ከምኵራብ አስወጥተው እንዳይሰዱአቸው በፈሪሳውያን ምክንያት አልመሰከሩለትም። ከእግዚአብሔር ክብር ይልቅ የሰውን ክብር ወደዋልና። ጌታችን ኢየሱስም ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፥ “በእኔ የሚያምን በላከኝም ነው እንጂ በእኔ ብቻ የሚያምን አይደለም። እኔን ያየ የላከኝን አየ። በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር ብርሃን እኔ ወደ ዓለም መጣሁ። ቃሌን ሰምቶ የማይጠብቀውን እኔ የምፈርድበት አይደለሁም፤ ዓለምን ላድን እንጂ በዓለም ልፈርድበት አልመጣሁምና። የሚክደኝን፥ ቃሌንም የማይቀበለውን ግን የሚፈርድበት አለ፤ እኔ የተናገርሁት ቃል እርሱ በመጨረሻዪቱ ቀን ይፈርድበታል። የተናገርሁት ከእኔ የሆነ አይደለምና፤ ነገር ግን የላከኝ አብ እንድናገር፥ እንዲህም እንድል እርሱ ትእዛዝን ሰጠኝ። ትእዛዙም የዘለዓለም ሕይወት እንደ ሆነ አውቃለሁ፤ እኔም የምናገረውን አብ እንዳለኝ እንዲሁ እናገራለሁ።”
ዮሐንስ 12:20-50 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ለአምልኮ ወደ በዓሉ ከወጡት መካከል የግሪክ ሰዎችም ነበሩ። እነርሱም በገሊላ ከምትገኘው ከቤተ ሳይዳ ወደ ሆነው ሰው፣ ወደ ፊልጶስ መጥተው፣ “ጌታው፤ እባክህን፣ ኢየሱስን ለማየት እንፈልጋለን” አሉት። ፊልጶስም፤ ለእንድርያስ ሊነግረው ሄደ፤ እንድርያስና ፊልጶስም ለኢየሱስ ነገሩት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “የሰው ልጅ የሚከብርበት ሰዓቱ ደርሷል፤ እውነት እላችኋለሁ፤ የስንዴ ቅንጣት መሬት ላይ ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች። ሕይወቱን የሚወድድ ያጣታል፤ በዚህ ዓለም ሕይወቱን የሚጠላ ግን ለዘላለም ሕይወት ይጠብቃታል። የሚያገለግለኝ ቢኖር ይከተለኝ፤ እኔም ባለሁበት አገልጋዬም በዚያ ይሆናል፤ የሚያገለግለኝንም አባቴ ያከብረዋል። “አሁንስ ነፍሴ ተጨነቀች፤ ምን ልበል? አባት ሆይ፤ ከዚህች ሰዓት ብታድነኝስ? ይሁን፤ የመጣሁት ለዚህች ሰዓት ነውና። አባት ሆይ፤ ስምህን አክብረው።” ከዚያም፣ “አክብሬዋለሁ፤ ደግሞም አከብረዋለሁ” የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ። በዚያ የነበሩት፣ ድምፁን የሰሙት አያሌ ሰዎች፣ “ነጐድጓድ ነው” አሉ፤ ሌሎች ደግሞ፣ “መልአክ ተናገረው” አሉ። ኢየሱስም እንዲህ አለ፤ “ይህ ድምፅ የመጣው ስለ እኔ ሳይሆን ስለ እናንተ ነው፤ ይህ ዓለም የሚፈረድበት ጊዜ አሁን ነው፤ የዚህም ዓለም ገዥ አሁን ወደ ውጭ ይጣላል። እኔ ግን ከምድር ከፍ ከፍ ባልሁ ጊዜ ሰውን ሁሉ ወደ ራሴ እስባለሁ።” ይህን የተናገረው በምን ዐይነት ሞት እንደሚሞት ለማመልከት ነበር። ሕዝቡም፣ “እኛስ ክርስቶስ ለዘላለም እንደሚኖር ከሕግ ሰምተናል፤ ታዲያ፣ ‘የሰው ልጅ ከፍ ከፍ ማለት አለበት’ እንዴት ትላለህ? ይህስ ‘የሰው ልጅ’ ማን ነው?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል ተናገራቸው፤ “ከእንግዲህ ለጥቂት ጊዜ ብርሃን አለላችሁ፤ ጨለማ ሳይመጣባችሁ፣ ብርሃን ሳለላችሁ ተመላለሱ፤ በጨለማ የሚመላለስ ወዴት እንደሚሄድ አያውቅም። የብርሃን ልጆች እንድትሆኑ ብርሃን ሳለላችሁ በዚህ ብርሃን እመኑ።” ኢየሱስ ይህን ተናግሮ እንደ ጨረሰ ተለያቸው፤ ተሰወረባቸውም። ኢየሱስ እነዚህን ታምራዊ ምልክቶች ሁሉ በፊታቸው ቢያደርግም እንኳ፣ አሁንም አላመኑበትም፤ ይኸውም ነቢዩ ኢሳይያስ፣ “ጌታ ሆይ፤ ምስክርነታችንን ማን አመነ? የጌታ ክንድስ ለማን ተገለጠ?” ያለው ቃል እንዲፈጸም ነው። ስለዚህ ማመን አልቻሉም፤ ይህም ኢሳይያስ በሌላ ቦታ እንዲህ ሲል እንደ ተናገረው ነው፤ “ዐይናቸውን አሳውሯል፤ ልባቸውንም አደንድኗል፤ ስለዚህ በዐይናቸው አያዩም፤ በልባቸውም አያስተውሉም፤ እንዳልፈውሳቸውም አይመለሱም።” ኢሳይያስ ይህን ያለው የኢየሱስን ክብር ስላየ ነው፤ ስለ እርሱም ተናገረ። ይህም ቢሆን፣ ከአለቆች መካከል እንኳ ሳይቀር ብዙዎች በእርሱ አመኑ፤ ይሁን እንጂ ፈሪሳውያን ከምኵራብ እንዳያስወጧቸው ስለ ፈሩ ማመናቸውን አይገልጡም ነበር። ይህም የሆነው በእግዚአብሔር ከመመስገን ይልቅ በሰው መመስገንን ስለ ወደዱ ነው። ከዚያም ኢየሱስ ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፤ “ማንም በእኔ ቢያምን በእኔ ብቻ ሳይሆን በላከኝም ማመኑ ነው፤ እኔንም የሚያይ የላከኝን ያያል። በእኔ የሚያምን በጨለማ እንዳይኖር ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ። “ቃሌን ሰምቶ በማይፈጽመው ላይ የምፈርደው እኔ አይደለሁም፤ ዓለምን ላድን እንጂ በዓለም ላይ ልፈርድ አልመጣሁምና። በማይቀበለኝና ቃሌን በሚያቃልል ላይ የሚፈርድበት አለ፤ የተናገርሁት ቃል ራሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል፤ ምክንያቱም እኔ ከራሴ አልተናገርሁም፤ ነገር ግን የላከኝ አብ ምን እንደምናገርና እንዴት እንደምናገር አዘዘኝ። የእርሱ ትእዛዝ ወደ ዘላለም ሕይወት እንደሚያደርስ ዐውቃለሁ፤ ስለዚህም የምለው ሁሉ አብ እንድናገረው የነገረኝን ብቻ ነው።”
ዮሐንስ 12:20-50 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በበዓሉም ሊሰግዱ ከመጡት አንዳንዶቹ የግሪክ ሰዎች ነበሩ፤ እነርሱም ከገሊላ ቤተ ሳይዳ ወደሚሆን ወደ ፊልጶስ መጥተው፦ “ጌታ ሆይ፥ ኢየሱስን ልናይ እንወዳለን” ብለው ለመኑት። ፊልጶስም መጥቶ ለእንድርያስ ነገረው፤ እንድርያስና ፊልጶስ መጥተው ለኢየሱስ ነገሩት። ኢየሱስስም መለሰላቸው፥ እንዲህ ሲል፦ “የሰው ልጅ ይከብር ዘንድ ሰዓቱ ደርሶአል። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች። ነፍሱን የሚወድ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም በዚህ ዓለም የሚጠላ ለዘላለም ሕይወት ይጠብቃታል። የሚያገለግለኝ ቢኖር ይከተለኝ፥ እኔም ባለሁበት አገልጋዬ ደግሞ በዚያ ይሆናል፤ የሚያገለግለኝም ቢኖር አብ ያከብረዋል። “አሁን ነፍሴ ታውካለች ምንስ እላለሁ? አባት ሆይ፥ ከዚህ ሰዓት አድነኝ። ነገር ግን ስለዚህ ወደዚህ ሰዓት መጣሁ። አባት ሆይ፥ ስምህን አክብረው።” ስለዚህም፦ “አከበርሁት ደግሞም አከብረዋለሁ” የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ። በዚያ ቆመው የነበሩትም ሕዝብ በሰሙ ጊዜ፦ “ነጐድጓድ ነው” አሉ፤ ሌሎች፦ “መልአክ ተናገረው” አሉ። ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል፦ “ይህ ድምፅ ስለ እናንተ መጥቶአል እጂ ስለ እኔ አይደለም። አሁን የዚህ ዓለም ፍርድ ደርሶአል፤ አሁን የዚህ ዓለም ገዥ ወደ ውጭ ይጣላል፤ እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደ ሆነ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ።” በምን ዓይነትም ሞት ይሞት ዘንድ እንዳለው ሲያመለክታቸው ይህን ተናገረ። እንዲህ ሕዝቡ፦ “እኛስ ክርስቶስ ለዘላለም እንዲኖር ከሕጉ ሰምተናል አንተስ የሰው ልጅ ከፍ ከፍ ይል ዘንድ እንዲያስፈልገው እንዴት ትላላህ? ይህ የሰው ልጅ ማን ነው?” ብለው መለሱለት። ኢየሱስም፦ “ገና ጥቂት ጊዜ ብርሃን ከእናንተ ጋር ነው። ጨለማ እንዳይደርስባችሁ ብርሃን ሳለላችሁ ተመላለሱ፤ በጨለማም የሚመላለስ ወዴት እንዲሄድ አያውቅም። የብርሃን ልጆች እንድትሆ ብርሃን ሳለላችሁ በብርሃኑ እመኑ” አላቸው። ኢየሱስም ይህን ተናግሮ ሄደና ተሰወረባቸው። ነገር ግን ይህን ያህል ምልክት በፊታቸው ምንም ቢያደርግ፤ ነቢዩ ኢሳይያስ፦ “ጌታ ሆይ፥ ማን ምስክርነታችንን አመነ? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገለጠ?” ብሎ የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ በእርሱ አላመኑም። ኢሳይያስ ደግሞ፦ “በዓይኖቻቸው እንዳያዩ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ እንዳይመለሱም፥ እኔም እንዳልፈውሳቸው፥ ዓኖቻቸውን አሳወረ ልባቸውውንም አደነደነ” ብሎአልና ስለዚህ ማመን አቃታቸው። ክብሩን ስለ አየ ኢሳይያስ ይህን አለ፥ ስለ እርሱም ተናገረ። ከዚህም ጋር ከአለቆች ደግሞ ብዙዎች በእርሱ አመኑ፤ ነገር ግን ከምኵራብ እንዳያስወጡአቸው በፈሪሳውያን ምክንያት አልመሰከሩለትም፤ ከእግዚአብሔር ክብር ይልቅ የሰውን ክብር ወደዋልና። ኢየሱስም ጮኸ፥ እንዲህም አለ፦ “በእኔ የሚያምን በላከኝ ማመኑ ነው እንጂ በእኔ አይደለም፤ እኔንም የሚያይ የላከኝን ያያል። በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር እኔ ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ። ዓለምን ላድን እንጂ በዓለም ልፈርድ አልመጣሁምና ቃሌን ሰምቶ የማይጠብቀው ቢኖር የምፈርድበት እኔ አይደለሁም። የሚጥለኝ ቃሌንም የማይቀበለው እርሱ የሚፈርድበት አለው፤ እኔ የተናገርሁት ቃል እርሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል። እኔ ከራሴ አልተናገርሁምና፤ ነገር ግን የላከኝ አብ እርሱ የምለውን የምናገረውንም ትእዛዝ ሰጠኝ። ትእዛዙም የዘላለም ሕይወት እንደ ሆነች አውቃለሁ። ስለዚህ እኔ የምናገረውን አብ እንደ ነገረኝ እንዲሁ እናገራለሁ።”
ዮሐንስ 12:20-50 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በበዓሉ ጊዜ ሊሰግዱ ወደ ኢየሩሳሌም ከሄዱት ሰዎች መካከል፥ አንዳንድ ግሪኮች ይገኙ ነበር። እነርሱም ከገሊላ የቤተ ሳይዳ ሰው ወደ ሆነው ወደ ፊልጶስ ቀርበው፥ “ጌታዬ ሆይ፥ ኢየሱስን ማየት እንፈልጋለን” አሉት። ፊልጶስም ሄዶ ለእንድርያስ ነገረው፤ እንድርያስና ፊልጶስ አብረው ሄደው ለኢየሱስ ነገሩት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እነሆ፥ የሰው ልጅ የሚከበርበት ሰዓት ደርሶአል፤ እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ የስንዴ ቅንጣት በመሬት ወድቃ ካልሞተች፥ ብቻዋን ትቀራለች፤ ከሞተች ግን ብዙ ታፈራለች። ሕይወቱን የሚወድ ያጠፋታል፤ በዚህ ዓለም ሕይወቱን የሚጠላ ግን ለዘለዓለም ሕይወት ይጠብቃታል። እኔን ማገልገል የሚፈልግ ይከተለኝ፤ እኔ ባለሁበት አገልጋዬ በዚያ ይሆናል፤ የሚያገለግለኝንም አብ ያከብረዋል።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “እነሆ! ነፍሴ ተጨንቃለች፤ ምን ልበል? ‘አባት ሆይ! ከዚህች ሰዓት አድነኝ ልበልን?’ ይህን እንዳልል ግን እኔ የመጣሁት ለዚህች የመከራ ሰዓት ነው። አባት ሆይ! ስምህን አክብረው።” ከዚህ በኋላ “ስሜን አክብሬዋለሁ፤ ደግሞም አከብረዋለሁ!” የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ። በዚያ የቆሙ ሰዎች ይህን በሰሙ ጊዜ፥ “ነጐድጓድ ነው!” አሉ። ሌሎች ደግሞ “መልአክ ነው የተናገረው!” አሉ። ኢየሱስ ግን እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ይህ ድምፅ የመጣው ለእናንተ ሲል ነው እንጂ ለእኔ ሲል አይደለም፤ ይህ ዓለም የሚፈረድበት ጊዜ አሁን ነው፤ የዚህ ዓለም ገዢ ሰይጣን ወደ ውጪ የሚጣለው አሁን ነው፤ እኔም ከምድር ወደ ላይ ከፍ በተደረግሁ ጊዜ ሰውን ሁሉ ወደ እኔ አስባለሁ።” ኢየሱስ ይህን የተናገረው በምን ዐይነት ሞት እንደሚሞት ሲያመለክት ነበር። ሰዎቹም “በሕግ ተጽፎ የምናገኘው ‘መሲሕ ለዘለዓለም ይኖራል’ የሚል ነው፤ ታዲያ፥ አንተ፥ ‘የሰው ልጅ ወደ ላይ ከፍ ማለት አለበት’ እንዴት ትላለህ? ይህስ የሰው ልጅ ማን ነው?” አሉት። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “አሁን ለጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር ብርሃን አለ፤ ጨለማ እንዳይደርስባችሁ ብርሃን ሳለላችሁ ተመላለሱ፤ በጨለማ የሚመላለስ ወዴት እንደሚሄድ አያውቅም። የብርሃን ልጆች እንድትሆኑ ብርሃን ሳለላችሁ በብርሃን እመኑ።” ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ ሄደና ተሰወረባቸው። ኢየሱስም ብዙ ተአምራትን በፊታቸው ቢያደርግም እንኳ አይሁድ በእርሱ አላመኑም። ይህም የሆነው ነቢዩ ኢሳይያስ፥ “ጌታ ሆይ! ምስክርነታችንን ማን አመነ? የጌታስ ኀይል ለማን ተገለጠ?” ሲል የተናገረው ቃል እንዲፈጸም ነው። እንደገናም ኢሳይያስ እንዲህ ሲል አለማመናቸውን ገለጠ፦ “በዐይናቸው አይተውና በልባቸው አስተውለው እንዳይመለሱና እንዳይፈውሳቸው እግዚአብሔር ዐይናቸውን አሳውሮአል፤ ልባቸውንም አደንድኖአል።” ኢሳይያስ ይህን ያለው የመሲሕን ክብር ስላየ ነው፤ ስለዚህ ይህን ስለ ኢየሱስ ተናገረ። ሆኖም ከአይሁድ አለቆች እንኳ ብዙዎቹ በኢየሱስ አምነዋል፤ ነገር ግን ፈሪሳውያን ከምኲራብ እንዳያስወጡአቸው በመፍራት፥ በግልጥ አልመሰከሩለትም። ይህንንም ያደረጉት ከእግዚአብሔር ከሚገኘው ክብር ይልቅ ከሰው የሚገኘውን ክብር ስለ ወደዱ ነው። ኢየሱስም ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፦ “በእኔ የሚያምን በእኔ ብቻ ሳይሆን፥ በላከኝም ያምናል፤ እኔን የሚያይ የላከኝን ያያል፤ በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር እኔ ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ። ቃሌን ሰምቶ በሥራ ላይ የማያውለውን የምፈርድበት እኔ አይደለሁም፤ እኔ የመጣሁት ዓለምን ለማዳን ነው እንጂ በዓለም ላይ ለመፍረድ አይደለም። እኔን የማይፈልግና ቃሌንም የማይቀበለውን ሰው የሚፈርድበት አለ፤ እኔ የተናገርኩት ቃል በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል። እኔ በራሴ ሥልጣን አልተናገርኩም፤ እኔ የምለውንና የምናገረውን ትእዛዝ የሰጠኝ የላከኝ አብ ነው። የእርሱም ትእዛዝ የዘለዓለም ሕይወት እንደ ሆነ ዐውቃለሁ። ስለዚህ እኔ የምናገረው አብ የነገረኝን ነው።”
ዮሐንስ 12:20-50 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በበዓሉም ሊሰግዱ ከመጡት አንዳንዶቹ የግሪክ ሰዎች ነበሩ፤ እነርሱም ከገሊላ ቤተሳይዳ ወደሚሆን ወደ ፊልጶስ መጥተው “ጌታ ሆይ! ኢየሱስን ልናይ እንወዳለን፤” ብለው ለመኑት። ፊልጶስም መጥቶ ለእንድርያስ ነገረው፤ እንድርያስና ፊልጶስ መጥተው ለኢየሱስ ነገሩት። ኢየሱስ ስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “የሰው ልጅ ይከብር ዘንድ ሰዓቱ ደርሶአል። እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች። ነፍሱን የሚወድ ያጠፋታል፤ ነፍሱንም በዚህ ዓለም የሚጠላ ለዘለዓለም ሕይወት ይጠብቃታል። የሚያገለግለኝ ቢኖር ይከተለኝ፤ እኔም ባለሁበት አገልጋዬ ደግሞ በዚያ ይሆናል፤ የሚያገለግለኝም ቢኖር አብ ያከብረዋል። “አሁን ነፍሴ ታውካለች፤ ምንስ እላለሁ? አባት ሆይ! ከዚህ ሰዓት አድነኝ። ነገር ግን ስለዚህ ወደዚህ ሰዓት መጣሁ። አባት ሆይ! ስምህን አክብረው።” ስለዚህም “አከበርሁት፤ ደግሞም አከብረዋለሁ፤” የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ። በዚያ ቆመው የነበሩትም ሕዝብ በሰሙ ጊዜ “ነጐድጓድ ነው፤” አሉ፤ ሌሎች “መልአክ ተናገረው፤” አሉ። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ “ይህ ድምፅ ስለ እናንተ መጥቷል እጂ ስለ እኔ አይደለም። አሁን የዚህ ዓለም ፍርድ ደርሶአል፤ አሁን የዚህ ዓለም ገዥ ወደ ውጭ ይጣላል፤ እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደሆነ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ።” በምን ዓይነትም ሞት ይሞት ዘንድ እንዳለው ሲያመለክታቸው ይህን ተናገረ። እንዲህ ሕዝቡ “እኛስ ክርስቶስ ለዘለዓለም እንዲኖር ከሕጉ ሰምተናል፤ አንተስ የሰው ልጅ ከፍ ከፍ ይል ዘንድ እንዲያስፈልገው እንዴት ትላላህ? ይህ የሰው ልጅ ማን ነው?” ብለው መለሱለት። ኢየሱስም “ገና ጥቂት ጊዜ ብርሃን ከእናንተ ጋር ነው። ጨለማ እንዳይደርስባችሁ ብርሃን ሳለላችሁ ተመላለሱ፤ በጨለማም የሚመላለስ ወዴት እንዲሄድ አያውቅም። የብርሃን ልጆች እንድትሆኑ ብርሃን ሳለላችሁ በብርሃኑ እመኑ፤” አላቸው። ኢየሱስም ይህን ከተናገረ በኋላ ሄዶ ተሰወረባቸው። ነገር ግን ይህን ያህል ምልክት በፊታቸው ምንም ቢያደርግም፤ እነርሱ ግን በእርሱ አላመኑም። ይህም ነቢዩ ኢሳይያስ “ጌታ ሆይ! ማን ምስክርነታችንን አመነ? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገለጠ?” ብሎ የተናገረው ቃል እንዲፈጸም ነው። ስለዚህ ማመን ተሳናቸው፤ ኢሳይያስ እንዲህ ብሎአልና፥ “በዐይኖቻቸው እንዳያዩ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ እንዳይመለሱም፥ እኔም እንዳልፈውሳቸው፥ ዐኖቻቸውን አሳወረ፤ ልባቸውውንም አደነደነ።” ክብሩን ስላየ ኢሳይያስ ይህን አለ፤ ስለ እርሱም ተናገረ። ከዚህም ጋር ከአለቆች ደግሞ ብዙዎች በእርሱ አመኑ፤ ነገር ግን ከምኵራብ እንዳያስወጡአቸው በፈሪሳውያን ምክንያት አልመሰከሩለትም፤ ከእግዚአብሔር ክብር ይልቅ የሰውን ክብር ወደዋልና። ኢየሱስም ጮኸ፤ እንዲህም አለ “በእኔ የሚያምን በላከኝ ማመኑ ነው እንጂ በእኔ አይደለም፤ እኔንም የሚያይ የላከኝን ያያል። በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር እኔ ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ። ዓለምን ላድን እንጂ በዓለም ልፈርድ አልመጣሁምና፤ ቃሌን ሰምቶ የማይጠብቀው ቢኖር የምፈርድበት እኔ አይደለሁም። የማይቀበለኝ ቃሌንም የማይሰማ እርሱ የሚፈርድበት አለው፤ እኔ የተናገርሁት ቃል እርሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል። እኔ ከራሴ አልተናገርሁምና፤ ነገር ግን የላከኝ አብ እርሱ የምለውን የምናገረውንም ትእዛዝ ሰጠኝ። ትእዛዙም የዘለዓለም ሕይወት እንደ ሆነች አውቃለሁ። ስለዚህ እኔ የምናገረውን አብ እንደ ነገረኝ እንዲሁ እናገራለሁ።”