ለአምልኮ ወደ በዓሉ ከወጡት መካከል የግሪክ ሰዎችም ነበሩ። እነርሱም በገሊላ ከምትገኘው ከቤተ ሳይዳ ወደ ሆነው ሰው፣ ወደ ፊልጶስ መጥተው፣ “ጌታ ሆይ፤ እባክህን ኢየሱስን ለማየት እንፈልጋለን” አሉት። ፊልጶስም፤ ለእንድርያስ ሊነግረው ሄደ፤ እንድርያስና ፊልጶስም ለኢየሱስ ነገሩት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “የሰው ልጅ የሚከብርበት ሰዓቱ ደርሷል፤ እውነት እላችኋለሁ፤ የስንዴ ቅንጣት መሬት ላይ ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች። ነፍሱን የሚወድድ ያጣታል፤ በዚህ ዓለም ነፍሱን የሚጠላ ግን ለዘላለም ሕይወት ይጠብቃታል። የሚያገለግለኝ ቢኖር ይከተለኝ፤ እኔም ባለሁበት አገልጋዬም በዚያ ይሆናል፤ የሚያገለግለኝንም አባቴ ያከብረዋል። “አሁንስ ነፍሴ ተጨነቀች፤ ምን ልበል? አባት ሆይ፤ ከዚህች ሰዓት ብታድነኝስ? ይሁን፤ የመጣሁት ለዚህች ሰዓት ነውና። አባት ሆይ፤ ስምህን አክብረው!” ከዚያም፣ “አክብሬዋለሁ፤ ደግሞም አከብረዋለሁ” የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ። በዚያ የነበሩት፣ ድምፁን የሰሙት አያሌ ሰዎች፣ “ነጐድጓድ ነው” አሉ፤ ሌሎች ደግሞ፣ “መልአክ ተናገረው” አሉ። ኢየሱስም እንዲህ አለ፤ “ይህ ድምፅ የመጣው ስለ እኔ ሳይሆን ስለ እናንተ ነው፤ ይህ ዓለም የሚፈረድበት ጊዜ አሁን ነው፤ የዚህም ዓለም ገዥ አሁን ወደ ውጭ ይጣላል። እኔ ግን ከምድር ከፍ ከፍ ባልሁ ጊዜ ሰውን ሁሉ ወደ ራሴ እስባለሁ።” ይህን የተናገረው በምን ዐይነት ሞት እንደሚሞት ለማመልከት ነበር። ሕዝቡም፣ “እኛስ ክርስቶስ ለዘላለም እንደሚኖር ከሕግ ሰምተናል፤ ታዲያ፣ ‘የሰው ልጅ ከፍ ከፍ ማለት አለበት’ እንዴት ትላለህ? ይህስ ‘የሰው ልጅ’ ማን ነው?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል ተናገራቸው፤ “ከእንግዲህ ለጥቂት ጊዜ ብርሃን አለላችሁ፤ ጨለማ ሳይመጣባችሁ፣ ብርሃን ሳለላችሁ ተመላለሱ፤ በጨለማ የሚመላለስ ወዴት እንደሚሄድ አያውቅም። የብርሃን ልጆች እንድትሆኑ ብርሃን ሳለላችሁ በዚህ ብርሃን እመኑ።” ኢየሱስ ይህን ተናግሮ እንደ ጨረሰ ተለያቸው፤ ተሰወረባቸውም። ኢየሱስ እነዚህን ታምራዊ ምልክቶች ሁሉ በፊታቸው ቢያደርግም እንኳ፣ አሁንም አላመኑበትም፤ ይኸውም ነቢዩ ኢሳይያስ፣ “ጌታ ሆይ፤ መልእክታችንን ማን አምኗል? የጌታስ ክንድ ለማን ተገልጧል?” ያለው ቃል እንዲፈጸም ነው። ስለዚህ ማመን አልቻሉም፤ ይህም ኢሳይያስ በሌላ ቦታ እንዲህ ሲል እንደ ተናገረው ነው፤ “ዐይናቸውን አሳውሯል፤ ልባቸውንም አደንድኗል፤ ስለዚህ በዐይናቸው አያዩም፤ በልባቸውም አያስተውሉም፤ እንዳልፈውሳቸውም አይመለሱም።” ኢሳይያስ ይህን ያለው የኢየሱስን ክብር ስላየ ነው፤ ስለ እርሱም ተናገረ። ይህም ቢሆን፣ ከአለቆች መካከል እንኳ ሳይቀር ብዙዎች በርሱ አመኑ፤ ይሁን እንጂ ፈሪሳውያን ከምኵራብ እንዳያስወጧቸው ስለ ፈሩ ማመናቸውን አይገልጡም ነበር። ይህም የሆነው በእግዚአብሔር ከመመስገን ይልቅ በሰው መመስገንን ስለ ወደዱ ነው። ከዚያም ኢየሱስ ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፤ “ማንም በእኔ ቢያምን በእኔ ብቻ ሳይሆን በላከኝም ማመኑ ነው፤ እኔንም የሚያይ የላከኝን ያያል። በእኔ የሚያምን በጨለማ እንዳይኖር ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ። “ቃሌን ሰምቶ በማይፈጽመው ላይ የምፈርደው እኔ አይደለሁም፤ ዓለምን ላድን እንጂ በዓለም ላይ ልፈርድ አልመጣሁምና። በማይቀበለኝና ቃሌን በሚያቃልል ላይ የሚፈርድበት አለ፤ የተናገርሁት ቃል ራሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል፤ ምክንያቱም እኔ ከራሴ አልተናገርሁም፤ ነገር ግን የላከኝ አብ ምን እንደምናገርና እንዴት እንደምናገር አዘዘኝ። የርሱ ትእዛዝ ወደ ዘላለም ሕይወት እንደሚያደርስ ዐውቃለሁ፤ ስለዚህም የምለው ሁሉ አብ እንድናገረው የነገረኝን ብቻ ነው።”
ዮሐንስ 12 ያንብቡ
ያዳምጡ ዮሐንስ 12
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዮሐንስ 12:20-50
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos