በበዓሉ ጊዜ ሊሰግዱ ወደ ኢየሩሳሌም ከሄዱት ሰዎች መካከል፥ አንዳንድ ግሪኮች ይገኙ ነበር። እነርሱም ከገሊላ የቤተ ሳይዳ ሰው ወደ ሆነው ወደ ፊልጶስ ቀርበው፥ “ጌታዬ ሆይ፥ ኢየሱስን ማየት እንፈልጋለን” አሉት። ፊልጶስም ሄዶ ለእንድርያስ ነገረው፤ እንድርያስና ፊልጶስ አብረው ሄደው ለኢየሱስ ነገሩት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እነሆ፥ የሰው ልጅ የሚከበርበት ሰዓት ደርሶአል፤ እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ የስንዴ ቅንጣት በመሬት ወድቃ ካልሞተች፥ ብቻዋን ትቀራለች፤ ከሞተች ግን ብዙ ታፈራለች። ሕይወቱን የሚወድ ያጠፋታል፤ በዚህ ዓለም ሕይወቱን የሚጠላ ግን ለዘለዓለም ሕይወት ይጠብቃታል። እኔን ማገልገል የሚፈልግ ይከተለኝ፤ እኔ ባለሁበት አገልጋዬ በዚያ ይሆናል፤ የሚያገለግለኝንም አብ ያከብረዋል።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “እነሆ! ነፍሴ ተጨንቃለች፤ ምን ልበል? ‘አባት ሆይ! ከዚህች ሰዓት አድነኝ ልበልን?’ ይህን እንዳልል ግን እኔ የመጣሁት ለዚህች የመከራ ሰዓት ነው። አባት ሆይ! ስምህን አክብረው።” ከዚህ በኋላ “ስሜን አክብሬዋለሁ፤ ደግሞም አከብረዋለሁ!” የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ። በዚያ የቆሙ ሰዎች ይህን በሰሙ ጊዜ፥ “ነጐድጓድ ነው!” አሉ። ሌሎች ደግሞ “መልአክ ነው የተናገረው!” አሉ። ኢየሱስ ግን እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ይህ ድምፅ የመጣው ለእናንተ ሲል ነው እንጂ ለእኔ ሲል አይደለም፤ ይህ ዓለም የሚፈረድበት ጊዜ አሁን ነው፤ የዚህ ዓለም ገዢ ሰይጣን ወደ ውጪ የሚጣለው አሁን ነው፤ እኔም ከምድር ወደ ላይ ከፍ በተደረግሁ ጊዜ ሰውን ሁሉ ወደ እኔ አስባለሁ።” ኢየሱስ ይህን የተናገረው በምን ዐይነት ሞት እንደሚሞት ሲያመለክት ነበር። ሰዎቹም “በሕግ ተጽፎ የምናገኘው ‘መሲሕ ለዘለዓለም ይኖራል’ የሚል ነው፤ ታዲያ፥ አንተ፥ ‘የሰው ልጅ ወደ ላይ ከፍ ማለት አለበት’ እንዴት ትላለህ? ይህስ የሰው ልጅ ማን ነው?” አሉት። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “አሁን ለጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር ብርሃን አለ፤ ጨለማ እንዳይደርስባችሁ ብርሃን ሳለላችሁ ተመላለሱ፤ በጨለማ የሚመላለስ ወዴት እንደሚሄድ አያውቅም። የብርሃን ልጆች እንድትሆኑ ብርሃን ሳለላችሁ በብርሃን እመኑ።” ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ ሄደና ተሰወረባቸው። ኢየሱስም ብዙ ተአምራትን በፊታቸው ቢያደርግም እንኳ አይሁድ በእርሱ አላመኑም። ይህም የሆነው ነቢዩ ኢሳይያስ፥ “ጌታ ሆይ! ምስክርነታችንን ማን አመነ? የጌታስ ኀይል ለማን ተገለጠ?” ሲል የተናገረው ቃል እንዲፈጸም ነው። እንደገናም ኢሳይያስ እንዲህ ሲል አለማመናቸውን ገለጠ፦ “በዐይናቸው አይተውና በልባቸው አስተውለው እንዳይመለሱና እንዳይፈውሳቸው እግዚአብሔር ዐይናቸውን አሳውሮአል፤ ልባቸውንም አደንድኖአል።” ኢሳይያስ ይህን ያለው የመሲሕን ክብር ስላየ ነው፤ ስለዚህ ይህን ስለ ኢየሱስ ተናገረ። ሆኖም ከአይሁድ አለቆች እንኳ ብዙዎቹ በኢየሱስ አምነዋል፤ ነገር ግን ፈሪሳውያን ከምኲራብ እንዳያስወጡአቸው በመፍራት፥ በግልጥ አልመሰከሩለትም። ይህንንም ያደረጉት ከእግዚአብሔር ከሚገኘው ክብር ይልቅ ከሰው የሚገኘውን ክብር ስለ ወደዱ ነው። ኢየሱስም ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፦ “በእኔ የሚያምን በእኔ ብቻ ሳይሆን፥ በላከኝም ያምናል፤ እኔን የሚያይ የላከኝን ያያል፤ በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር እኔ ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ። ቃሌን ሰምቶ በሥራ ላይ የማያውለውን የምፈርድበት እኔ አይደለሁም፤ እኔ የመጣሁት ዓለምን ለማዳን ነው እንጂ በዓለም ላይ ለመፍረድ አይደለም። እኔን የማይፈልግና ቃሌንም የማይቀበለውን ሰው የሚፈርድበት አለ፤ እኔ የተናገርኩት ቃል በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል። እኔ በራሴ ሥልጣን አልተናገርኩም፤ እኔ የምለውንና የምናገረውን ትእዛዝ የሰጠኝ የላከኝ አብ ነው። የእርሱም ትእዛዝ የዘለዓለም ሕይወት እንደ ሆነ ዐውቃለሁ። ስለዚህ እኔ የምናገረው አብ የነገረኝን ነው።”
የዮሐንስ ወንጌል 12 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ወንጌል 12:20-50
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች