መጽሐፈ መሳፍንት 10:6-16

መጽሐፈ መሳፍንት 10:6-16 አማ54

የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደ ገና ክፉ ሥራ ሠሩ በኣሊምንና አስታሮትን የሶርያንም አማልክት፥ የሲዶናንም አማልክት፥ የሞዓብንም አማልክት፥ የአሞንንም ልጆች አማልክት፥ የፍልስጥኤማውያንንም አማልክት አመለኩ፥ እግዚአብሔርንም ተዉ፥ አላመለኩትምም። የእግዚአብሔርም ቁጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፥ በፍልስጥኤማውያንና በአሞን ልጆች እጅ አሳልፎ ሰጣቸው። በዚያም ዓመት የእስራኤልን ልጆች ሥቃይ አበዙባቸው፥ በዮርዳኖስ ማዶ በአሞራውያን አገር በገለዓድ ውስጥ ያሉትን የእስራኤልን ልጆች ሁሉ አሥራ ስምንት ዓመት ተጋፉአቸው። የአሞንም ልጆች ከይሁዳ ከብንያምና ከኤፍሬም ቤት ጋር ደግሞ ሊዋጋ ዮርዳኖስን ተሻገሩ፥ እስራኤልም እጅግ ተጨነቁ። የእስራኤልም ልጆች፦ አምላካችንን ትተን በኣሊምን አምልከናልና አንተን በድለናል ብለው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። እግዚአብሔርም የእስራኤልን ልጆች አላቸው፦ ግብፃውያን፥ አሞራውያንም፥ የአሞንም ልጆች፥ ፍልስጥኤማውያንም፥ ሲዶናውያንም፥ አማሌቃውያንም፥ ማዖናውያንም አላስጨነቋችሁምን? ወደ እኔም ጮኻችሁ፥ እኔም ከእጃቸው አዳንኋችሁ። እናንተ ግን ተዋችሁኝ ሌሎችንም አማልክት አመለካችሁ፥ ስለዚህም ደግሞ አላድናችሁም። ሄዳችሁ የመረጣችኋቸውን አማልክት ጥሩ፥ እነርሱም በመከራችሁ ጊዜ ያድኑአችሁ። የእስራኤልም ልጆች እግዚአብሔርን፦ እኛ ኃጢአትን ሠርተናል፥ አንተ ደስ የሚያሰኝህን አድርግብን፥ ዛሬ ግን፥ እባክህ፥ አድነን አሉት። ሌሎችንም አማልክት ከመካከላቸው አስወገዱ፥ እግዚአብሔርንም አመለኩ፥ ነፍሱም ስለ እስራኤል ጉስቁልና አዘነች።