የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መሳፍንት 10:6-16

መሳፍንት 10:6-16 NASV

እስራኤላውያን እንደ ገና በእግዚአብሔር ላይ ክፉ ድርጊት ፈጸሙ፤ በኣልንና አስታሮትን እንዲሁም የአራምን፣ የሲዶናን፣ የሞዓብን፣ የአሞንንና የፍልስጥኤማውያንን አማልክት አመለኩ፤ እስራኤላውያን እግዚአብሔርን ስለ ተዉና ስላላገለገሉት፣ እግዚአብሔርም ተቈጣቸው፤ በፍልስጥኤማውያንና በአሞናውያን እጅ ሸጣቸው፤ እነርሱም በዚያ ዓመት ሰበሯቸው፤ አደቀቋቸውም፤ ለዐሥራ ስምንት ዓመታት ከዮርዳኖስ ማዶ ባለው የአሞራውያን ምድር፣ በገለዓድ የነበሩትን እስራኤላውያንን ሁሉ አሠቃዩአቸው። እንዲሁም አሞናውያን ይሁዳን፣ ብንያምንና የኤፍሬምን ቤት ለመውጋት ዮርዳኖስን ስለ ተሻገሩ እስራኤላውያን እጅግ ተጨነቁ። ከዚያም እስራኤላውያን፣ “አንተን አምላካችንን በመተው የበኣልን አማልክት በማምለካችን አንተን በድለናል” ብለው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። እግዚአብሔርም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ግብጻውያን፣ አሞራውያን፣ አሞናውያን፣ ፍልስጥኤማውያን፣ ሲዶናውያን፣ አማሌቃውያንና ማዖናውያን አሠቃዩአችሁ፤ እናንተም እንድረዳችሁ ወደ እኔ ጮኻችሁ፤ ታዲያ እኔ ከእጃቸው አላዳንኋችሁምን? እናንተ ግን እኔን ትታችሁ ሌሎች አማልክትን አመለካችሁ፤ ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲያ አላድናችሁም፤ ሂዱና ወደ መረጣችኋቸው አማልክት ጩኹ፤ መከራ በሚያገኛችሁ ጊዜ እስኪ ያድኗችሁ።” እስራኤላውያንም እግዚአብሔርን፣ “ኀጢአት ሠርተናል፤ መልካም መስሎ የታየህን አድርግብን፤ እባክህን የዛሬን ብቻ አድነን” አሉት። ከዚያም በመካከላቸው ያሉትን ባዕዳን አማልክት አስወገዱ፤ እግዚአብሔርንም አመለኩ፤ እግዚአብሔርም እስራኤል ስትጐሳቈል ዝም ብሎ ማየት አልቻለም።