እስራኤላውያን ባዓልና ዐስታሮት የተባሉትን ባዕዳን አማልክት እንዲሁም የሶርያን፥ የሲዶናን፥ የሞአብን፥ የዐሞንንና የፍልስጥኤምን አማልክት በማምለክ እንደገና እግዚአብሔርን በደሉ፤ እርሱንም ማምለክ ተዉ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር በእስራኤላውያን ላይ ተቈጣ፤ ለፍልስጥኤማውያንና ለዐሞናውያን አሳልፎ ሰጣቸው። አሞናውያንና ፍልስጥኤማውያንም ከዮርዳኖስ ማዶ በአሞራውያን ምድር በገለዓድ ውስጥ የሚኖሩትን እስራኤላውያንን ለዐሥራ ስምንት ዓመት አስጨንቀው ገዙአቸው። ዐሞናውያን የይሁዳን፥ የብንያምንና የኤፍሬምን ነገዶች ለመውጋት ዮርዳኖስን ተሻገሩ፤ እስራኤላውያንም እጅግ ተጨነቁ። ከዚህ በኋላ እስራኤላውያን “አንተን አምላካችንን ትተን በዓል ተብለው የሚጠሩትን ባዕዳን አማልክት በመከተላችን በአንተ ላይ በደል ሠርተናል” በማለት ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። እግዚአብሔር እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ግብጻውያን፥ አሞራውያን፥ ዐሞናውያን፥ ፍልስጥኤማውያን፥ ሲዶናውያን፥ ዐማሌቃውያንና ማዖናውያን ከዚህ በፊት ጨቊነው በገዙአችሁ ጊዜ ወደ እኔ ጮኻችሁ ነበር፤ ታዲያ እኔስ ከእነርሱ ጭቈና በመታደግ አድኛችሁ አልነበረምን? እናንተ ግን እስከ አሁን ድረስ እኔን ትታችሁ ለባዕዳን አማልክት ሰገዳችሁ፤ ስለዚህ እኔ እናንተን ዳግመኛ አልታደጋችሁም፤ ሂዱ፤ ወደ መረጣችኋቸው ባዕዳን አማልክትም ጩኹ፤ መከራ በሚደርስባችሁ ጊዜም እስቲ እነርሱ ራሳቸው ያድኑአችሁ።” የእስራኤል ሕዝብ ግን እግዚአብሔርን “በእርግጥ በድለናል፤ አንተ በእኛ ላይ የፈለግኸውን አድርግብን፤ ብቻ እባክህ የዛሬን አድነን” አሉት። ባዕዳን አማልክታቸውንም አስወግደው፥ እግዚአብሔርን አመለኩ፤ እግዚአብሔርም ስለ እስራኤል መከራ እጅግ አዘነ።
መጽሐፈ መሳፍንት 10 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ መሳፍንት 10:6-16
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos