እንዲህም ሆነ፤ በእስራኤል ንጉሥ በኤላ ልጅ በሆሴዕ በሦስተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የአካዝ ልጅ ሕዝቅያስ ነገሠ። መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሃያ አምስት ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የዘካርያስ ልጅ አቡ ነበረች። እርሱም አባቱ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገርን አደረገ። በኮረብታም ያሉትን መስገጃዎች አስወገደ፤ ሐውልቶችንም ቀለጣጠመ፤ ያማምለኪያ ዐፀዶችንም ቈረጠ፤ የእስራኤልም ልጆች እስከዚህ ዘመን ድረስ ያጥኑለት ነበርና ሙሴ የሠራውን የናሱን እባብ ሰባበረ፤ ስሙንም “ነሑሽታን” ብሎ ጠራው። በእስራኤልም አምላክ በእግዚአብሔር ታመነ፤ ከእርሱም በኋላ ከእርሱም በፊት ከነበሩት ከይሁዳ ነገሥታት ሁሉ እርሱን የሚመስል አልነበረም። ከእግዚአብሔርም ጋር ተጣበቀ፤ እርሱንም ከመከተል አልራቀም፤ እግዚአብሔርም ለሙሴ ያዘዘውን ትእዛዛቱን ጠበቀ። እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ፤ የሚሄድበትም መንገድ ተከናወነለት፤ በአሦርም ንጉሥ ላይ ዐመፀ፤ አልገበረለትም። ፍልስጥኤማውያንንም እስከ ጋዛና እስከ ዳርቻዋ ድረስ፥ ከዘበኞች ግንብ ጀምሮ እስከ ምሽጉ ከተማ ድረስ መታ። በንጉሡ በሕዝቅያስ በአራተኛው ዓመት፥ በእስራኤል ንጉሥ በኤላ ልጅ በሆሴዕ በሰባተኛው ዓመት፥ የአሦር ንጉሥ ስልምናሶር ወደ ሰማርያ ወጣ፤ ከበባትም። ከሦስት ዓመት በኋላም ወሰዳት፤ በሕዝቅያስ በስድስተኛው ዓመት፥ በእስራኤል ንጉሥ በሆሴዕ በዘጠነኛው ዓመት፥ ሰማርያ ተያዘች። የአሦር ንጉሥ እስራኤልን ወደ አሦር አፈለሰ፤ በአላሔና በአቦር በጎዛንም ወንዝ በሜዶንም ከተሞች አኖራቸው፤ የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰሙምና፥ ቃል ኪዳኑንም አፍርሰዋልና፥ የእግዚአብሔርም ባሪያ ሙሴ ያዘዘውን ሁሉ አልሰሙምና፥ አላደረጉምና።
ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 18 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 18:1-12
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች