ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 18:1-12

ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 18:1-12 አማ05

የኤላ ልጅ ሆሴዕ በእስራኤል በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የአካዝ ልጅ ሕዝቅያስ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤ በነገሠም ጊዜ ዕድሜው ኻያ አምስት ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ኻያ ዘጠኝ ዓመት ገዛ፤ እናቱም አቢያ ተብላ የምትጠራ የዘካርያስ ልጅ ነበረች፤ የቀድሞ አባቱን የንጉሥ ዳዊትን መልካም አርአያነት በመከተል እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠራ። የአሕዛብን የማምለኪያ ስፍራዎችን ደመሰሰ፤ የድንጋይ ዐምዶችን ሰባበረ፤ አሼራ ተብላ በምትጠራው ሴት አምላክ ስም የተቀረጹትን ምስሎች ሁሉ አንከታክቶ ጣለ፤ ሙሴ ከነሐስ ሠርቶት የነበረውን ኔሑሽታን ተብሎ የሚጠራውን የእባብ ምስል ሰባብሮ አደቀቀ፤ እስከዚያን ጊዜ ድረስ ግን እስራኤላውያን ለእርሱ ዕጣን ያጥኑለት ነበር። ሕዝቅያስ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ተማመነ፤ ከእርሱ በፊትም ሆነ ከእርሱ ወዲህ እርሱን የመሰለ ሌላ ንጉሥ በይሁዳ አልተነሣም፤ ሕዝቅያስ ለእግዚአብሔር ታማኝ ስለ ሆነ ከእርሱ መንገድ የራቀበት ጊዜ የለም፤ እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጣቸውን ትእዛዞች ሁሉ በጥንቃቄ ይፈጽም ነበር። ስለዚህም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ሆኖ ስለሚረዳው የሚሠራው ሁሉ በተቃና ሁኔታ ይከናወንለት ነበር፤ ሕዝቅያስ በአሦር ንጉሠ ነገሥት ላይ ዐምፆ ለእርሱ መገዛትን አሻፈረኝ አለ። ፍልስጥኤማውያንንም ድል ነሥቶ ከትንሽ መንደር እስከ ታላቅ ከተማ ጋዛንና በዙሪያው የሚገኘውን ግዛት ጭምር እነርሱ የሚኖሩበትን ስፍራ ሁሉ ወረረ። ሕዝቅያስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት ይህም ማለት ሆሴዕ በእስራኤል በነገሠ በሰባተኛው ዓመት፥ የአሦር ንጉሥ ሰልምናሶር በእስራኤል ላይ አደጋ በመጣል ሰማርያን ከበበ፤ በተከበበችበትም በሦስተኛው ዓመት ሰማርያ በሙሉ ተያዘች፤ ይህም የሆነው ሕዝቅያስ በነገሠ በስድስተኛው ዓመት፥ ሆሴዕ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት ነበር። የአሦር ንጉሠ ነገሥት እስራኤላውያንን ማርኮ ወደ አሦር በመውሰድ ከእነርሱ ጥቂቶቹ በሐላሕ ከተማ ጥቂቶቹ በጎዛን አውራጃ በሚገኘው በሐቦር ወንዝ አጠገብ፥ ሌሎቹ ደግሞ በሜዶን ከተሞች እንዲሰፍሩ አደረገ። ሰማርያ የወደቀችበት ምክንያት እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር ባለመታዘዛቸው ነው፤ ይኸውም እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን አፈረሱ፤ የእግዚአብሔር አገልጋይ በሆነው በሙሴ አማካይነት ለተሰጠ ሕግ ሁሉ ታዛዦች ሆነው አልተገኙም፤ ቃሉን ማዳመጥም ሆነ ሕጉን መጠበቅ አልፈለጉም።