2 ነገሥት 18:1-12

2 ነገሥት 18:1-12 NASV

የእስራኤል ንጉሥ የኤላ ልጅ ሆሴዕ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የአካዝ ልጅ ሕዝቅያስ ነገሠ። በነገሠም ጊዜ ዕድሜው ሃያ ዐምስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ገዛ። እናቱ የዘካርያስ ልጅ ስትሆን፣ ስሟ አቢያ ይባል ነበር። አባቱ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነገር አደረገ። በየኰረብታው ላይ ያሉትን የማምለኪያ ዐምዶች አስወገደ፤ አዕማደ ጣዖታትን ሰባበረ፤ የአሼራን ምስል ዐምዶች ቈራረጠ፤ ሙሴ የሠራውን የናስ እባብ፣ እስራኤላውያን እስከ እነዚያ ጊዜያት ድረስ ዕጣን ያጤሱለት ስለ ነበር ሰባበረው፤ ይህም ነሑሽታን ይባል ነበር። ሕዝቅያስም በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ታመነ፤ ከርሱ በፊትም ሆነ ከርሱ በኋላ ከይሁዳ ነገሥታት ሁሉ፣ እንደ እርሱ ያለ አልነበረም። ከእግዚአብሔር ጋራ ተጣበቀ፤ እርሱን ከመከተል ወደ ኋላ አላለም፤ እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠውንም ትእዛዞች ጠበቀ። እግዚአብሔር ከርሱ ጋራ ስለ ነበር የሚያደርገው ሁሉ ተከናወነለት። በአሦር ንጉሥ ላይ ዐመፀ፤ ግብር መገበሩንም ተወ። እስከ ጋዛና እስከ ግዛቷ ዳርቻ በመዝለቅ ፍልስጥኤማውያንን ከመጠበቂያ ማማ እስከ ተመሸገችው ከተማ ድረስ ድል አደረጋቸው። ሕዝቅያስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፣ የእስራኤልም ንጉሥ የኤላ ልጅ ሆሴዕ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት፣ የአሦር ንጉሥ ስልምናሶር ወደ ሰማርያ ገሥግሦ ከተማዪቱን ከበባት፤ በሦስተኛውም ዓመት መጨረሻ ያዛት። ሰማርያ የተያዘችውም ሕዝቅያስ በነገሠ በስድስተኛው ዓመት፣ ሆሴዕ በእስራኤል ላይ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት ነበር። የአሦር ንጉሥ እስራኤልን ማርኮ ወደ አሦር በማፍለስ በአላሔ፣ በጎዛን ውስጥ በአቦር ወንዝ አጠገብና በማዴ ከተሞች አሰፈራቸው። ይህ የደረሰባቸውም የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ያዘዘውን የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ ከመስማት ይልቅ ኪዳኑን ስላፈረሱ ነበር፤ ትእዛዞቹን አላደመጡም፤ ደግሞም አልፈጸሙም።