ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 18

18
ሕዝቅያስ በይሁዳ ላይ እንደ ነገሠ
(2ዜ.መ. 29፥1-231፥1)
1እንዲህም ሆነ፤ በእስራኤል ንጉሥ በኤላ ልጅ በሆሴዕ በሦስተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የአካዝ ልጅ ሕዝቅያስ ነገሠ። 2መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሃያ አምስት ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የዘካርያስ ልጅ አቡ ነበረች። 3እርሱም አባቱ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገርን አደረገ። 4በኮረብታም ያሉትን መስገጃዎች አስወገደ፤ ሐውልቶችንም ቀለጣጠመ፤ ያማምለኪያ ዐፀዶችንም ቈረጠ፤ የእስራኤልም ልጆች እስከዚህ ዘመን ድረስ ያጥኑለት ነበርና ሙሴ የሠራውን የናሱን እባብ ሰባበረ፤ ስሙንም “ነሑሽታን” ብሎ ጠራው። 5በእስራኤልም አምላክ በእግዚአብሔር ታመነ፤ ከእርሱም በኋላ ከእርሱም በፊት ከነበሩት ከይሁዳ ነገሥታት ሁሉ እርሱን የሚመስል አልነበረም። 6ከእግዚአብሔርም ጋር ተጣበቀ፤ እርሱንም ከመከተል አልራቀም፤ እግዚአብሔርም ለሙሴ ያዘዘውን ትእዛዛቱን ጠበቀ። 7እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ፤ የሚሄድበትም መንገድ ተከናወነለት፤ በአሦርም ንጉሥ ላይ ዐመፀ፤ አልገበረለትም። 8ፍልስጥኤማውያንንም እስከ ጋዛና እስከ ዳርቻዋ ድረስ፥ ከዘበኞች ግንብ ጀምሮ እስከ ምሽጉ ከተማ ድረስ መታ።
9በንጉሡ በሕዝቅያስ በአራተኛው ዓመት፥ በእስራኤል ንጉሥ በኤላ ልጅ በሆሴዕ በሰባተኛው ዓመት፥ የአሦር ንጉሥ ስልምናሶር ወደ ሰማርያ ወጣ፤ ከበባትም። 10ከሦስት ዓመት በኋላም ወሰዳት፤ በሕዝቅያስ በስድስተኛው ዓመት፥ በእስራኤል ንጉሥ በሆሴዕ በዘጠነኛው ዓመት፥ ሰማርያ ተያዘች። 11የአሦር ንጉሥ እስራኤልን ወደ አሦር አፈለሰ፤ በአላሔና በአቦር በጎዛንም ወንዝ በሜዶንም ከተሞች አኖራቸው፤ 12የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰሙምና፥ ቃል ኪዳኑንም አፍርሰዋልና፥ የእግዚአብሔርም ባሪያ ሙሴ ያዘዘውን ሁሉ አልሰሙምና፥ አላደረጉምና።
የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ይሁዳን እንደ ውረረ
(2ዜ.መ. 32፥1-19ኢሳ. 36፥1-22)
13በንጉሡም በሕዝቅያስ በዐሥራ አራተኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ወደ ይሁዳ ወደ ተመሸጉት ከተሞች ሁሉ ወጣ፤ ወሰዳቸውም። 14የይሁዳም ንጉሥ ሕዝቅያስ “በድያለሁ፤ ከእኔ ተመለስ፤ የምትጭንብኝን ሁሉ እሸከማለሁ፤” ብሎ ወደ አሦር ንጉሥ ወደ ለኪሶ ላከ። የአሦርም ንጉሥ በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ላይ ሦስት መቶ መክሊት ብርና ሠላሳ መክሊት ወርቅ ጫነበት። 15ሕዝቅያስም በእግዚአብሔር ቤትና በንጉሡ ቤተ መዛግብት የተገኘውን ብር ሁሉ ሰጠው። 16በዚያን ጊዜም ሕዝቅያስ ከእግዚአብሔር መቅደስ ደጆችና የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ከለበጣቸው መቃኖች ወርቁን ቈረጠ፤ ለአሦርም ንጉሥ ሰጠው።
17የአሦርም ንጉሥ ተርታንንና ራፌስን ራፋስቂስንም ከብዙ ሠራዊት ጋር ከለኪሶ ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ ወደ ኢየሩሳሌም ላከ። ወጥተውም ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ በመጡም ጊዜ በአጣቢው እርሻ መንገድ ባለችው በላይኛይቱ ኩሬ መስኖ አጠገብ ቆሙ። 18ንጉሡንም ጠሩ፤ የቤቱም አዛዥ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም ጸሐፊውም ሳምናስ ታሪክ ጸሐፊውም የአሳፍ ልጅ ዮአስ ወደ እነርሱ ወጡ።
19ራፋስቂስም አላቸው “ለሕዝቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት ‘ታላቁ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፤ ይህ የምትታመንበት መተማመኛ ምንድር ነው? 20የከንፈር ቃል ለሰልፍ ምክርና ኀይል እንደሚሆን ትናገራለህ፤ አሁንም በእኔ ላይ ያመፅኸው በማን ተማምነህ ነው? 21እነሆ፥ በዚህ በተቀጠቀጠ በሸምበቆ በትር በግብጽ ትታመናለህ፤ ሰው ቢመረኰዘው ተሰብሮ በእጁ ይገባል፤ ያቈስለውማል፤ የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን ለሚታመኑበት ሁሉ እንዲሁ ነው።’ 22እናንተም ‘በአምላካችን በእግዚአብሔር እንታመናለን፤’ ብትሉኝ፥ ሕዝቅያስ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ‘በኢየሩሳሌም ባለው በዚህ መሠዊያ ፊት ሰገዱ፤’ ብሎ የኮረብታ መስገጃዎቹንና መሠዊያውቹን ያስፈረሰ ይህ አይደለምን? 23አሁን እንግዲህ ከጌታዬ ከአሦር ንጉሥ ጋር ተወራረድ፤ የሚቀመጡባቸውንም ሰዎች ማግኘት ቢቻልህ እኔ ሁለት ሺህ ፈረሶች እሰጥሃለሁ። 24ስለ ሠረገሎችና ሰለ ፈረሰኞች በግብጽ ስትታመን፥ ከጌታዬ ባሪያዎች የሚያንሰውን የአንዱ አለቃ ፊት ትቃወም ዘንድ እንዴት ይቻልሃል? 25አሁን በውኑ ያለ እግዚአብሔር ትእዛዝ ይህን ስፍራ አጠፋ ዘንድ ወጥቻለሁን? እግዚአብሔር ‘ወደዚች አገር ወጥተህ አጥፋት፤’ አለኝ።” 26የኬልቅያስም ልጅ ኤልያቄም ሳምናስም ዮአስም ራፋስቂስን “እኛ እንሰማለንና እባክህ፥ በሶርያ ቋንቋ ለባሪያዎችህ ተናገር፤ በቅጥርም ላይ ባለው ሕዝብ ጆሮ በአይሁድ ቋንቋ አትናገረን፤” አሉት። 27ራፋስቂስ ግን “ጌታዬ ይህን ቃል እናገር ዘንድ ወደ አንተና ወደ ጌታህ ልኮኛልን? ከእናንተ ጋር ኵሳቸውን ይበሉ ዘንድ ሽንታቸውንም ይጠጡ ዘንድ በቅጥር ላይ ወደ ተቀመጡት ሰዎች አይደለምን?” አላቸው። 28ራፋስቂስም ቆሞ በታላቅ ድምፅ በአይሁድ ቋንቋ እንዲህ ብሎ ጮኽ “የታላቁን የአሦር ንጉሥ ቃል ስሙ፤ ንጉሡ እንዲህ ይላል 29‘ከእጄ ያድናችሁ ዘንድ አይችልምና ሕዝቅያስ አያታልላችሁ፤ 30ሕዝቅያስም “እግዚአብሔር በእርግጥ ያድነናል፤ ይህችም ከተማ በአሦር ንጉሥ እጅ አትሰጥም፤” ብሎ በእግዚአብሔር እንድትታመኑ አያድርጋችሁ። 31ሕዝቅያስንም አትስሙ፤’ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል ‘ከእኔ ጋር ታረቁ፤ ወደ እኔም ውጡ፤ እያንዳንዳችሁም ከወይናችሁና ከበለሳችሁ ብሉ፤ ከጕድጓዳችሁም ውሃ ጠጡ፤ 32ይህም መጥቼ ምድራችሁን ወደምትመስለው ምድር፥ እህልና የወይን ጠጅ፥ እንጀራና ወይን፥ ወይራና ማር ወዳለባት ምድር እስካፈልሳችሁ ድረስ በሕይወት እንድትኖሩ እንዳትሞቱም ነው። ሕዝቅያስም “እግዚአብሔር ያድነናል፤” ብሎ ቢያታልላችሁ አትስሙት። 33በውኑ የአሕዛብ አማልክት አገሮቻቸውን ከአሦር ንጉሥ እጅ አድነዋቸዋልን? 34የሐማትና የአርፋድ አማልክት ወዴት አሉ? የሴፈርዋይምና የሄና የዒዋም አማልክት ወዴት አሉ? ሰማርያን ከእጄ አድነዋታልን? 35እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ከእጄ ያድን ዘንድ ከአገሮቹ አማልክት ሁሉ አገሩን ከእጄ ያዳነ ማን ነው?’”
36ሕዝቡም ዝም አሉ፤ አንዳችም አልመለሱለትም፤ ንጉሡ እንዳይመልሱለት አዝዞ ነበርና። 37የቤቱ አዛዥ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም ጸሐፊውም ሳምናስ ታሪክ ጸሐፊም የአሳፍ ልጅ ዮአስ ልብሳቸውን ቀድደው ወደ ሕዝቅያስ መጡ፤ የራፋስቂስንም ቃል ነገሩት።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ