ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 17
17
ሆሴዕ የመጨረሻ ንጉሥ ሆኖ በእስራኤል እንደ ነገሠ
1በይሁዳ ንጉሥ በአካዝ በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት የኤላ ልጅ ሆሴዕ በእስራኤል ላይ በሰማርያ ንጉሥ ሆነ፤ ዘጠኝ ዓመትም ነገሠ። 2በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ ነገር ግን ከእርሱ አስቀድሞ እንደ ነበሩት እንደ እስራኤል ነገሥታት አይደለም። 3የአሦርም ንጉሥ ስልምናሶር በእርሱ ላይ ወጣ፤ ሆሴዕም ተገዛለት፤ ግብርም አመጣለት። 4የአሦርም ንጉሥ በሆሴዕ ላይ ዐመፅ አገኘ፤ መልእክተኞችን ወደ ግብጽ ንጉሥ ወደ ሴጎር ልኮ ነበርና፤ እንደ ልማዱም በየዓመቱ ለአሦር ንጉሥ ግብር አልሰጠምና፤ ስለዚህ የአሦር ንጉሥ ይዞ በወህኒ ቤት አሰረው።
የእስራኤላውያን ተማርከው ወደ አሦር እንደ ሄዱ
5የአሦርም ንጉሥ በምድር ሁሉ ላይ ወጣ፤ ወደ ሰማርያም ወጥቶ ሦስት ዓመት ከበባት። 6በሆሴዕ በዘጠነኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ ሰማርያን ወሰደ፤ እስራኤልንም ወደ አሦር አፈለሰ፤ በአላሔና በአቦር በጎዛንም ወንዝ በሜዶንም ከተሞች አኖራቸው።
7የእስራኤልም ልጆች ከግብጽ ንጉሥ ከፈርዖን እጅ፥ ከግብጽ ምድር ያወጣቸውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን በድለው ነበርና፥ ሌሎችንም አማልክት አምልከው ነበርና፥ 8እግዚአብሔርም ከእስራኤል ልጆች ፊት ባሳደዳቸው በአሕዛብ ሥርዐት፥ የእስራኤልም ነገሥታት ባደረጓት ሥርዐት ሄደው ነበርና እንደዚህ ሆነ። 9የእስራኤልም ልጆች በአምላካቸው በእግዚአብሔር ላይ ቅን ያልሆነውን ንገር በስውር አደረጉ፤ በከተሞቻቸውም ሁሉ ከዘበኞች ግንብ ጀምሮ እስከ ተመሸገች ከተማ ድረስ በከፍታዎቹ ላይ መስገጃዎችን ሠሩ። 10በረጃጅሙ ኮረብታ ሁሉ ላይ በለመለመውም ዛፍ ሁሉ ታች ሐውልቶችንና የማምለኪያ ዐፀዶችን ተከሉ፤ 11እግዚአብሔርም ከፊታቸው ያወጣቸው አሕዛብ እንዳደረጉት፥ በኮረብቶቹ መስገጃዎች ሁሉ ላይ ያጥኑ ነበር፤ እግዚአብሔርንም ያስቆጡ ዘንድ ክፉ ነገር አደረጉ፤ 12እግዚአብሔርም የከለከላቸውን ጣዖቶች አመለኩ። 13እግዚአብሔርም “ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ለአባቶቻችሁም እንዳዘዝሁት፥ ባባሪያዎቼ በነቢያት የላክሁላችሁን ትእዛዜንና ሥርዐቴን ሕጌንም ሁሉ ጠብቁ፤” ብሎ በእያንዳንዱ ነቢይና በእያንዳንዱ ባለ ራእይ አፍ በእስራኤልና በይሁዳ መሰከረ። 14ነገር ግን አምላካቸውን እግዚአብሔርን እንዳላመኑ እንደ አባቶቻቸው አንገት አንገታቸውን አደነደኑ እንጂ አልሰሙም። 15ሥርዐቱንም፥ ከአባቶቻቸውም ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን፥ ያጸናላቸውንም ምስክሩን ናቁ፤ ከንቱ ነገርንም ተከተሉ፤ ምናምንቴዎችም ሆኑ፤ እግዚአብሔርም እንደ እነርሱ እንዳይሠሩ ያዘዛቸውን በዙሪያቸው ያሉትን አሕዛብ ተከተሉ። 16የአምላካቸውንም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ሁሉ ተዉ፤ ቀልጠው የተሠሩትንም የሁለቱን እንቦሶች ምስሎች አደረጉ፤ የማምለኪያ ዐፀድንም ተከሉ፤ ለሰማይ ሠራዊትም ሁሉ ሰገዱ፤ በኣልንም አመለኩ። 17ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በእሳት አሳለፉአቸው፤ ምዋርተኞችና አስማተኞችም ሆኑ፤ ያስቈጡትም ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር ለማድረግ ራሳቸውን ሸጡ። 18ስለዚህም እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ እጅግ ተቈጣ፤ ከፊቱም ጣላቸው፤ ከይሁዳም ነገድ ብቻ በቀር ማንም አልቀረም።
19ይሁዳም ደግሞ እስራኤል ባደረጋት ሥርዐት ሄደ እንጂ የአምላኩን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ አልጠበቀም። 20እግዚአብሔርም የእስራኤልን ዘር ሁሉ ጠላ፤ አስጨነቃቸውም፤ ከፊቱም እስኪጥላቸው ድረስ በበዝባዦች እጅ አሳልፎ ሰጣቸው። 21እስራኤልንም ከዳዊት ቤት ለየ፤ የናባጥንም ልጅ ኢዮርብዓምን አነገሡ፤ ኢዮርብዓምም እግዚአብሔርን ከመከተል እስራኤልን መለሰ፤ ታላቅም ኀጢአት አሠራቸው። 22-23የእስራኤልም ልጆች ኢዮርብዓም ባደረገው ኀጢአት ሁሉ ሄዱ፤ እግዚአብሔርም በባሪያዎቹ በነቢያቱ ሁሉ አፍ እንደ ተናገረው እስራኤልን ከፊቱ እስኪያወጣ ድረስ ከእርስዋ አልራቁም። እስራኤልም እስከ ዛሬ ድረስ ከምድሩ ወደ አሦር ፈለሰ።
አሦራውያን በእስራኤል ምድር እንዲሰፍሩ መደረጉ
24የአሦርም ንጉሥ ከባቢሎንና ከኩታ ከአዋና ከሐማት ከሴፈርዋይም ሰዎችን አመጣ፤ በእስራኤልም ልጆች ፋንታ በሰማርያ ከተሞች አኖራቸው፤ ሰማርያንም ወረሱአት፤ በከተሞችዋም ተቀመጡ። 25በዚያም መቀመጥ በጀመሩ ጊዜ እግዚአብሔርን አይፈሩትም ነበር፤ እግዚአብሔርም አንበሶች ሰደደባቸው፤ ይገድሉአቸውም ነበር። 26ስለዚህም ለአሦር ንጉሥ “ያፈለስኻቸው፥ በሰማርያም ከተሞች ያኖርኻቸው የአገሩን አምላክ ወግ አላወቁም፤ የአገሩን አምላክ ወግ አላወቁምና አንበሶችን ሰድዶባቸዋል፤ እነሆም፥ ገደሉአቸው፤” ብለው ተናገሩት።
27የአሦርም ንጉሥ “ከዚያ ካመጣችኋቸው ካህናት አንዱን ውሰዱ፤ ሄዶም በዚያ ይቀመጥ፤ የአገሩንም አምላክ ወግ ያስተምራቸው፤ ብሎ አዘዘ። 28ከሰማርያም ካፈለሱአቸው ካህናት አንዱ መጥቶ በቤቴል ተቀመጠ፤ እግዚአብሔርንም እንዴት እንዲፈሩት ያስተምራቸው ነበር። 29በየሕዝባቸውም አምላካቸውን አደረጉ፤ ሳምራውያንም በሠሩት በኮረብታው መስገጃዎች ሕዝቡ ሁሉ በሚኖሩበት ከተሞቻቸው አኖሩአቸው። 30የባቢሎንም ሰዎች ሱኮትበኖትን ሠሩ፤ የኩታም ሰዎች ኤርጌልን ሠሩ፤ የሐማትም ሰዎች አሲማትን ሠሩ፤ 31አዋውያንም ኤልባዝርንና ተርታቅን ሠሩ፤ የሴፈርዋይም ሰዎችም ለሴፈርዋይም አማልክት ለአድራሜሌክና ለአነሜሌክ ልጆቻቸውን በእሳት ያቃጥሉ ነበር። 32እግዚአብሔርንም ይፈሩ ነበር፤ ከመካከላቸውም ለኮረብታው መስገጃዎች ካህናት አደረጉ፤ በኮረብታውም መስገጃዎች ይሠዉ ነበር። 33እግዚአብሔርንም ሲፈሩ ከመካከላቸው እንደ ፈለሱት እንደ አሕዛብ ልማድ አምላካቸውን ያመልኩ ነበር።
34እስከ ዛሬ ድረስ እንደ ቀደመው ልማድ ያደርጋሉ፤ እግዚአብሔርንም አይፈሩም፤ እግዚአብሔርም እስራኤል ብሎ የጠራውን የያዕቆብን ልጆች እንዳዘዛቸው ሥርዐትና ፍርድ ሕግና ትእዛዝም አያደርጉም። 35እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፤ እንዲህም ብሎ አዘዛቸው “ሌሎች አማልክትን አትፍሩ፤ አትስገዱላቸው፤ አታምልኩአቸው፤ አትሠዉላቸው፤ 36ነገር ግን በታላቅ ኀይል በተዘረጋችም ክንድ ከግብጽ ምድር ያወጣችሁን እግዚአብሔርን እርሱን ፍሩ፤ ለእርሱም ስገዱ፤ ለእርሱም ሠዉ፤ 37የጻፈላችሁንም ሥርዐትና ፍርድ፥ ሕግና ትእዛዝም ለዘላለም ታደርጉ ዘንድ ጠብቁ፤ ሌሎች አማልክትንም አትፍሩ። 38ከእናንተም ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳን አትርሱ፤ ሌሎች አማልክትንም አትፍሩ። 39አምላካችሁን እግዚአብሔርን ፍሩ፤ እርሱም ከጠላቶቻችሁ ሁሉ እጅ ያድናችኋል። 40ነገር ግን እንደ ቀደመው ልማዳቸው አደረጉ እንጂ አልሰሙም። 41እነዚህም አሕዛብ እግዚአብሔርን ይፈሩ ነበር፤ ደግሞም የተቀረጹ ምስሎቻቸውን ያመልኩ ነበር፤ ልጆቻቸውም የልጅ ልጆቻቸውም አባቶቻቸው እንዳደረጉ እንዲሁ እስከ ዛሬ ድረስ ያደርጋሉ።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 17: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ