የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 16

16
አካዝ በይሁዳ እንደ ነገሠ
(2ዜ.መ. 28፥1-27)
1በሮሜልዩ ልጅ በፋቁሔ በዐሥራ ሰባተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአታም ልጅ አካዝ ነገሠ። 2አካዝ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሃያ ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ዐሥራ ስድስት ዓመት ነገሠ፤ እንደ አባቱም እንደ ዳዊት በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አላደረገም። 3ነገር ግን በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፤ ደግሞም እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ፊት እንዳሳደዳቸው እንደ አሕዛብ ርኩሰት ልጁን በእሳት አሳለፈው። 4በመስገጃዎችና በኮረብቶቹ ላይ በለመለመውም ዛፍ ሁሉ በታች ይሠዋና ያጥን ነበር።
5በዚያን ጊዜም የሶርያ ንጉሥ ረአሶንና የእስራኤል ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ሊዋጉ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ አካዝንም ከበቡት፤ ሊያሸንፉት ግን አልቻሉም። 6በዚያም ዘመን የሶርያ ንጉሥ ረአሶን ኤላትን ወደ ሶርያ መለሰ፤ አይሁድንም ከኤላት አሳደደ፤ ኤዶማውያንም ወደ ኤላት መጥተው እስከ ዛሬ ድረስ በእርስዋ ተቀምጠዋል።
7አካዝም “እኔ ባሪያህና ልጅህ ነኝ፤ መጥተህ ከተነሡብን ከሶርያ ንጉሥና ከእስራኤል ንጉሥ እጅ አድነኝ፤” ብሎ ወደ አሦር ንጉሥ ወደ ቴልጌልቴልፌልሶር መልእክተኞችን ላከ። 8አካዝም በእግዚአብሔር ቤትና በንጉሡ ቤተ መዛግብት የተገኘውን ብርና ወርቅ ወስዶ ወደ አሦር ንጉሥ ገጸ በረከት አድርጎ ሰደደው። 9የአሦርም ንጉሥ ሰማው፤ የአሦርም ንጉሥ በደማስቆ ላይ ወጣባት፤ ወሰዳትም፤ ሕዝብዋንም ወደ ቂር አፈለሳቸው፤ ረአሶንንም ገደለ።
10ንጉሡ አካዝም የአሦርን ንጉሠ ቴልጌልቴልፌልሶርን ሊገናኘው ወደ ደማስቆ ሄደ፤ በደማስቆ የነበረውን መሠዊያ አየ፤ ንጉሡም አካዝ የመሠዊያውን ምሳሌና የአሠራሩን መልክ ወደ ካህኑ ወደ ኦርያ ላከው። 11ካህኑም ኦርያ መሠዊያ ሠራ፤ ንጉሡ አካዝ ከደማስቆ ልኮ እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ ካህኑ ኦርያ ንጉሡ አካዝ ከደማስቆ እስኪመጣ ድረስ ሠራው። 12ንጉሡም ከደማስቆ በመጣ ጊዜ መሠዊያውን አየ፤ ንጉሡም ወደ መሠዊያው ቀርቦ በእርሱ ላይ ወጣ። 13በመሠዊያውም ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን አሳረገ፥ የመጠጡንም ቍርባን አፈሰሰ፤ የደኅንነቱንም መሥዋዕት ደም ረጨ። 14በእግዚአብሔርም ፊት የነበረውን የናሱን መሠዊያ ከመቅደሱ ፊት ከመሠዊያውና ከእግዚአብሔር ቤት መካከል ፈቀቅ አድርጎ በመሠውያው አጠገብ በሰሜን በኩል አኖረው። 15ንጉሡ አካዝም “የሚቃጠለውን የጠዋት መሥዋዕት፥ የማታውንም የእህሉን ቍርባን፥ የንጉሡንም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን፥ ለአገሩም ሕዝብ የሚሆን የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን የመጠጡንም ቍርባን በታላቁ መሠዊያ ላይ አቅርብ፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ደም ሁሉ የሌላ መሥዋዕቱንም ደም ሁሉ ርጭበት፤ የናሱ መሠዊያ ግን እኔ እጠይቅበት ዘንድ ይሁን፤” ብሎ ካህኑን ኦርያን አዘዘው። 16ካህኑ ኦርያ ንጉሡ አካዝ እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ አደረገ።
17ንጉሡም አካዝ የመቀመጫዎችን ክፈፍ ቈረጠ፤ ከእነርሱም የመታጠቢያውን ሰኖች ወሰደ፤ ኵሬውንም ከበታቹ ከነበሩት ከናሱ በሬዎች አወረደው፤ በጠፍጣፋውም ድንጋይ ላይ አኖረው። 18በእግዚአብሔርም ቤት የዙፋኑን መሠረት ሠራ፤ ስለ አሦርም ንጉሥ በውጭ ያለውን የንጉሡን መንገድ ወደ እግዚአብሔር ቤት አዞረው። 19የቀረውም አካዝ ያደረገው ነገር በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 20አካዝም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ፤ ልጁም ሕዝቅያስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ