መዝሙረ ዳዊት 103
103
የዳዊት መዝሙር።
1ነፍሴ እግዚአብሔርን ታመሰግነዋለች፤#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “ነፍሴ ሆይ እግዚአብሔርን ባርኪ” ይላል።
አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ አንተ እጅግ ታላቅ ነህ፤
መታመንንና የጌትነትን ክብር ለበስህ።
2ብርሃንን እንደ ልብስ ተጐናጸፍህ፤
ሰማይንም እንደ መጋረጃ ዘረጋህ፤
3እልፍኙን በውኃ የሚሠራ፥
ደመናን መሄጃው የሚያደርግ፥
በነፋስ ክንፍም የሚሄድ፥
4መላእክቱን መንፈስ፥
አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል የሚያደርጋቸው።
5ለዘለዓለም እንዳትናወጥ፥
ምድርን መሠረታት፥ አጸናትም።
6ጥልቁም እንደ ልብስ ክዳኗ ነው፥
በተራሮችም ላይ ውኆች ይቆማሉ።
7ከተግሣጽህም የተነሣ ይሸሻሉ፥
ከነጐድጓድህም ድምፅ የተነሣ ይደነግጣሉ፤
8ወደ ተራሮች ይወጣሉ፥
ወደ ሜዳ፥ ወዳዘጋጀህላቸው ስፍራም ይወርዳሉ፥
9እንዳያልፉትም ድንበር አደረግህላቸው፥
ምድርን ይከድኑ ዘንድ እንዳይመለሱ።
10ምንጮችን ወደ ቆላዎች የሚልክ፤
በተራሮች መካከል ውኆች ያልፋሉ፤
11የዱር አራዊትን ሁሉ ያጠጣሉ፥
የበረሃ አህዮችም ጥማታቸውን ያረካሉ።
12የሰማይ ወፎችም በዚያ ይኖራሉ፤
በዋሻው መካከልም ይጮኻሉ።
13ተራሮችን ከውስጣቸው የሚያጠጣቸው፤
ከሥራህ ፍሬ ምድር ትጠግባለች።
14እህልን ከምድር ያወጣ ዘንድ፥
ለምለሙን ለሰው ልጆች አገልግሎት፥
ሣርንም ለእንስሳ ያበቅላል።
15ወይን የሰውን ልብ ደስ ያሰኛል፥
ዘይትም ፊትን ለማብራት ነው።
እህልም የሰውን ኀይል#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “ልብ” ይላል። ያጠነክራል።
16የዱር ዛፎች ሁሉ፥
የተከልኸው የሊባኖስ ዝግባም ይጠግባሉ።
17በዚያም ዎፎች ይዋለዳሉ፥
የሸመላ ቤትም ይጐራበታቸዋል።
18ረጃጅም ተራራዎች ለዋሊያዎች፥
ድንጋዮችም ለአሽኮኮዎች መሸሻ ናቸው።
19ጨረቃን በጊዜው ፈጠርህ፤
ፀሐይም መግቢያውን ያውቃል።
20ጨለማን ታመጣለህ ሌሊትም ይሆናል፤
በእርሱም የዱር አራዊት ሁሉ ይወጡበታል።
21የአንበሶች ግልገሎች ያገሣሉ፥ ይነጥቃሉም፥
ከእግዚአብሔርም ምግባቸውን ይሻሉ።
22ፀሐይ ስትወጣ ይገባሉ፥
በየዋሻቸውም ይውላሉ።
23ሰው ወደ ተግባሩ ይሰማራል፥
እስኪመሽም ድረስ ሲሠራ ይውላል።
24አቤቱ፥ ሥራህ እጅግ ታላቅ ነው፤
ሁሉን በጥበብ አደረግህ፥
የፈጠርኸውም ፍጥረት ምድርን ሞላ።
25ይህች ባሕር ታላቅና ሰፊ ናት፤
በዚያ ስፍር ቍጥር የሌለው ተንቀሳቃሽ፥
ታላላቆችና ታናናሾች እንስሶች አሉ።
26በዚያ ላይ መርከቦች ይሄዳሉ፥
በዚያም ላይ የፈጠርኸው ዘንዶ ይጫወታል።
27ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸው ዘንድ
እነዚህ ሁሉ አንተን ተስፋ ያደርጋሉ።
28በሰጠሃቸውም ጊዜ ይሰበስባሉ፤
እጅህን ፈትተህ ከቸርነትህ የተነሣ ሁሉን ታጠግባለህ።
29ፊትህን ብትመልስ ግን ይደነግጣሉ፤
ነፍሳቸውን ታወጣለህ፥ ይሞታሉም፥
ወደ አፈራቸውም ይመለሳሉ።
30መንፈስህን ትልካለህ፥ ይፈጠራሉም፥
የምድርንም ፊት ታድሳለህ።
31የእግዚአብሔር ክብር ለዘለዓለም ይሁን፤
እግዚአብሔር በሥራው ደስ ይለዋል።
32ምድርን ያያል፥ እንድትንቀጠቀጥም ያደርጋል፤
ተራሮችን ይዳስሳል፥ ይጤሳሉም።
33በሕይወቴ ሳለሁ እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ፥
ለአምላኬም በምኖርበት ዘመን ሁሉ እዘምራለሁ።
34በቃሌም ደስ አሰኘዋለሁ፥#ዕብ. “ቃሌ ለእርሱ ይጣፍጥ” ይላል።
እኔም በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል።
35ኃጥኣን ከምድር ይጠፋሉ፥
ዐመፀኞችም እንግዲህ አይኖሩም።#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “ይጥፉ ... አይኑር” ይላል።
ነፍሴ እግዚአብሔርን ታመሰግነዋለች።#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “ነፍሴ ሆይ እግዚአብሔርን አመስግኝ” ይላል።
Currently Selected:
መዝሙረ ዳዊት 103: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ