መዝሙረ ዳዊት 101
101
ባዘነና ልመናውን በእግዚአብሔር ፊት ባፈሰሰ ጊዜ የባሕታዊ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “የድሃ” ይላል። ጸሎት።
1አቤቱ፥ ጸሎቴን ስማኝ፥
ጩኸቴም ወደ ፊትህ ይድረስ።
2በመከራዬ ቀን ፊትህን ከእኔ አትመልስ፤
ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፤
በጠራሁህ ቀን ፈጥነህ ስማኝ።
3ዘመኔ እንደ ጢስ አልቋልና፥
አጥንቶቼም እንደ ሣር ደርቀዋልና።
4ተቀሠፍሁ ልቤም እንደ ሣር ደረቀ።
እህል መብላት ተረስቶኛልና
5ከጩኸቴ ድምፅ የተነሣ ሥጋዬ በአጥንቶቼ ላይ ተጣበቀ።#ዕብ. እና ግሪክ “አጥንቶቼ ከሥጋየ ጋር ተጣበቁ” ይላል።
6እንደ ሜዳ አህያ#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “እርኩም” ይላል። ሆንኹ፤
ሌሊት በወና ቤት እንዳለ እንደ ጕጕት ሆንሁ።
7ተጋሁ፥ በሰገነትም እንደሚኖር ብቸኛ ድንቢጥ ሆንሁ።
8ጠላቶቼ ሁልጊዜ ይሰድቡኛል፥
የሚያሳድዱኝም ተማማሉብኝ።
9አመድን እንደ እህል ቅሜአለሁና፥
መጠጤንም ከእንባዬ ጋር ጠጥቻለሁና፥
10ከቍጣህ መቅሠፍት የተነሣ፥
አንስተኽ ጥለኸኛልና።
11ዘመኔም እንደ ጥላ አለፈ፤
እኔም እንደ ሣር ደርቄአለሁ።
12አንተ ግን፥ አቤቱ፥ ለዘለዓለም ትኖራለህ፥
መታሰቢያህም ለልጅ ልጅ ነው።
13አንተ ተነሥ፥ ጽዮንንም ይቅር በላት፥
ይቅር ትላት ዘንድ ጊዜዋ ነውና፥ ዘመንዋም ደርሶአልና፤
14ባሪያዎችህ ድንጋዮችዋን ወድደዋልና፥
መሬቷንም አክብረውታልና።
15አቤቱ፥ አሕዛብ ስምህን፥
ነገሥታትም ሁሉ ክብርህን ይፍሩ፤
16እግዚአብሔር ጽዮንን ይሠራታልና፥
በክብሩም ይገለጣልና።
17ወደ ድሆች ጸሎት ተመለከተ፥
ልመናቸውንም አልናቀም፥
18ይህችም ለሚመጣ ትውልድ ተጻፈች፥#ዕብ. “ይህ ለሚመጣው ትውልድ ይጻፍ” ይላል።
የሚፈጠርም ሕዝብ እግዚአብሔርን ያመሰግነዋል፤
19ከሰማይ ሆኖ መቅደሱን ተመልክቶአልና፥
እግዚአብሔር ከሰማይ ሆኖ ምድርን ጐብኝቶአልና፤
20የእስረኞችን ጩኸት ይሰማ ዘንድ፥
የተገደሉትንም ሰዎች ልጆች ያድን ዘንድ፤
21የእግዚአብሔርን ስም በጽዮን
ምስጋናውንም በኢየሩሳሌም ይነግሩ ዘንድ፤
22አሕዛብ በአንድነት በተሰበሰቡ ጊዜ
ነገሥታትም#መንግሥታትም። ለእግዚአብሔር ይገዙ ዘንድ።
23በኀይሉ ጎዳና መለሳቸው፥
የዘመኔን ማነስ ንገረኝ።
24በዘመኔ አኩሌታ አትውሰደኝ፤
ዓመቶችህ ለልጅ ልጅ ናቸው።
25አቤቱ፥ አንተ አስቀድመህ ምድርን መሠረትህ፥
ሰማያትም የእጅህ ሥራ ናቸው።
26እነርሱ ይጠፋሉ፥ አንተ ግን ትኖራለህ፥
ሁሉ እንደ ልብስ ያረጃል፥#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. በብዙ ቍጥር።
እንደ መጐናጸፊያም ትለውጣቸዋለህ፥ ይለወጡማል፤
27አንተ ግን ያው አንተ ነህ፥
ዓመትህም ከቶ አያልቅም።#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. በብዙ ቍጥር።
28የባሪያዎችህም ልጆች ይኖራሉ፥
ዘራቸውም ለዘለዓለም ይጸናል።
Currently Selected:
መዝሙረ ዳዊት 101: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ