እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ “ለምጽ ለያዘው ሰው ሕጉ ይህ ነው፤ ከለምጽ በነጻበት ቀን ወደ ካህኑ ይወስዱታል። ካህኑም ከሰፈር ወደ ውጭ ይወጣል፤ ካህኑም ያየዋል፤ እነሆም፥ የለምጹ ደዌ ከለምጻሙ ላይ ቢጠፋ፥ ካህኑ ስለሚነጻው ሰው ሁለት ንጹሓን ዶሮዎች በሕይወታቸው፥ የዝግባም ዕንጨት፥ ቀይ ግምጃም፥ ሂሶጵም ያመጣ ዘንድ ያዝዛል። ካህኑም ከሁለቱ ዶሮዎች አንደኛዋን በሸክላ ዕቃ ውስጥ በምንጭ ውኃ ላይ ያርድ ዘንድ ያዝዛል። ያልታረደችውንም ዶሮ፥ ዝግባውንም ዕንጨት፥ ቀዩንም ግምጃ፥ ሂሶጱንም ወስዶ በምንጭ ውኃ ላይ በታረደችው ዶሮ ደም ውስጥ ይነክራቸዋል። ከለምጹም በሚነጻው ሰው ላይ ሰባት ጊዜ ይረጫል፤ ንጹሕም ይሆናል፤ ያልታረደችውን ዶሮ ወደ ሜዳ ይለቅቃታል። የነጻውም ሰው ልብሱን ያጥባል፤ ጠጕሩንም ሁሉ ይላጫል፤ በውኃም ይታጠባል፤ ንጹሕም ይሆናል። ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈር ይገባል፤ ነገር ግን ከቤቱ በውጭ ሆኖ ሰባት ቀን ይቀመጣል። በሰባተኛውም ቀን ጠጕሩን ሁሉ ይላጫል፤ ራሱንም፥ ጢሙንም፥ ቅንድቡንም፥ የገላውንም ጠጕር ሁሉ ይላጫል፤ ልብሱንም፥ ገላውንም በውኃ ያጥባል፤ ንጹሕም ይሆናል። “በስምንተኛው ቀን ነውር የሌለባቸውን፥ ዓመት የሞላቸውን ሁለት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ ነውር የሌለባትንም አንዲት የዓመት እንስት የበግ ጠቦት፥ ስለ እህልም ቍርባን ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሦስት እጅ የሆነ፥ በዘይት የተለወሰ መልካም የስንዴ ዱቄት፥ አንድ ማሰሮ ዘይትም ይወስዳል። የሚያነጻውም ካህን እነዚህን ነገሮች፥ የሚነጻውንም ሰው በምስክሩ ድንኳን ደጃፍ አጠገብ በእግዚአብሔር ፊት ያቀርባቸዋል። ካህኑም አንዱን ጠቦት ወስዶ ስለ በደል መሥዋዕት ያቀርባል፤ ያንም አንድ ማሰሮ ዘይት ስለ ልዩ ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ይለየዋል። የኀጢአትን መሥዋዕትና የሚቃጠለውን መሥዋዕት በሚያርዱበት በተቀደሰው ስፍራ ጠቦቱን ያርዱታል፤ የበደሉ መሥዋዕት ለካህኑ እንደሚሆን፥ እንዲሁ የኀጢአቱ መሥዋዕት ነውና፤ ቅዱሰ ቅዱሳን ነው። ካህኑም ከበደል መሥዋዕት ደም ወስዶ የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት ይቀባዋል። ካህኑም ከማሰሮው ዘይት ወስዶ በግራ እጁ ውስጥ ያፈስሰዋል። ካህኑም በግራ እጁ ውስጥ ባለው ዘይት ቀኝ ጣቱን ነክሮ ከዘይቱ በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ጊዜ በጣቱ ይረጫል። ካህኑም በእጁ ውስጥ ከቀረው ዘይት የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት የበደል መሥዋዕት ደም ባረፈበት ላይ ይቀባዋል። በካህኑም እጅ ውስጥ የቀረውን ዘይት ካህኑ በሚነጻው ሰው ራስ ላይ ያደርግበታል፤ ካህኑም በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል።
ኦሪት ዘሌዋውያን 14 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘሌዋውያን 14:1-18
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች