ኦሪት ዘሌዋውያን 14
14
ከለምጽ ደዌ የመንጻት ሕግ
1እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ 2“ለምጽ ለያዘው ሰው ሕጉ ይህ ነው፤ ከለምጽ በነጻበት ቀን ወደ ካህኑ ይወስዱታል። 3ካህኑም ከሰፈር ወደ ውጭ ይወጣል፤ ካህኑም ያየዋል፤ 4እነሆም፥ የለምጹ ደዌ ከለምጻሙ ላይ ቢጠፋ፥ ካህኑ ስለሚነጻው ሰው ሁለት ንጹሓን ዶሮዎች በሕይወታቸው፥ የዝግባም ዕንጨት፥ ቀይ ግምጃም፥ ሂሶጵም#ስሚዛ ያመጣ ዘንድ ያዝዛል። 5ካህኑም ከሁለቱ ዶሮዎች አንደኛዋን በሸክላ ዕቃ ውስጥ በምንጭ ውኃ ላይ ያርድ ዘንድ ያዝዛል። 6ያልታረደችውንም ዶሮ፥ ዝግባውንም ዕንጨት፥ ቀዩንም ግምጃ፥ ሂሶጱንም ወስዶ በምንጭ ውኃ ላይ በታረደችው ዶሮ ደም ውስጥ ይነክራቸዋል። 7ከለምጹም በሚነጻው ሰው ላይ ሰባት ጊዜ ይረጫል፤ ንጹሕም ይሆናል፤ ያልታረደችውን ዶሮ ወደ ሜዳ ይለቅቃታል። 8የነጻውም ሰው ልብሱን ያጥባል፤ ጠጕሩንም ሁሉ ይላጫል፤ በውኃም ይታጠባል፤ ንጹሕም ይሆናል። ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈር ይገባል፤ ነገር ግን ከቤቱ በውጭ ሆኖ ሰባት ቀን ይቀመጣል። 9በሰባተኛውም ቀን ጠጕሩን ሁሉ ይላጫል፤ ራሱንም፥ ጢሙንም፥ ቅንድቡንም፥ የገላውንም ጠጕር ሁሉ ይላጫል፤ ልብሱንም፥ ገላውንም በውኃ ያጥባል፤ ንጹሕም ይሆናል።
10“በስምንተኛው ቀን ነውር የሌለባቸውን፥ ዓመት የሞላቸውን ሁለት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ ነውር የሌለባትንም አንዲት የዓመት እንስት የበግ ጠቦት፥ ስለ እህልም ቍርባን ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሦስት እጅ የሆነ፥ በዘይት የተለወሰ መልካም የስንዴ ዱቄት፥ አንድ ማሰሮ ዘይትም ይወስዳል። 11የሚያነጻውም ካህን እነዚህን ነገሮች፥ የሚነጻውንም ሰው በምስክሩ ድንኳን ደጃፍ አጠገብ በእግዚአብሔር ፊት ያቀርባቸዋል። 12ካህኑም አንዱን ጠቦት ወስዶ ስለ በደል መሥዋዕት ያቀርባል፤ ያንም አንድ ማሰሮ ዘይት ስለ ልዩ ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ይለየዋል። 13የኀጢአትን መሥዋዕትና የሚቃጠለውን መሥዋዕት በሚያርዱበት በተቀደሰው ስፍራ ጠቦቱን ያርዱታል፤ የበደሉ መሥዋዕት ለካህኑ እንደሚሆን፥ እንዲሁ የኀጢአቱ መሥዋዕት ነውና፤#ዕብ. “የኀጢአቱ መሥዋዕት ለካህኑ እንደሚሆን እንዲሁ የበደል መሥዋዕት ነውና” ይላል። ቅዱሰ ቅዱሳን ነው። 14ካህኑም ከበደል መሥዋዕት ደም ወስዶ የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት ይቀባዋል። 15ካህኑም ከማሰሮው ዘይት ወስዶ በግራ እጁ ውስጥ ያፈስሰዋል። 16ካህኑም በግራ እጁ ውስጥ ባለው ዘይት ቀኝ ጣቱን ነክሮ ከዘይቱ በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ጊዜ በጣቱ ይረጫል። 17ካህኑም በእጁ ውስጥ ከቀረው ዘይት የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት የበደል መሥዋዕት ደም ባረፈበት ላይ ይቀባዋል። 18በካህኑም እጅ ውስጥ የቀረውን ዘይት ካህኑ በሚነጻው ሰው ራስ ላይ ያደርግበታል፤ ካህኑም በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል። 19ካህኑም የኀጢአቱን መሥዋዕት ያቀርባል፤ ካህኑም ከኀጢአቱ ለማንጻት ለሚነጻው ሰው ያስተሰርይለታል፤ ከዚህም በኋላ ካህኑ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያርዳል። 20ካህኑም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን በመሠዊያው ላይ በእግዚአብሔር ፊት ያቀርባል፤ ካህኑም ያስተሰርይለታል፤ እርሱም ንጹሕ ይሆናል።
21“ድሃም ቢሆን፥ በእጁም ገንዘብ ባይኖረው፥ ማስተስረያ ይሆንለት ዘንድ አንድ ጠቦት ስለ በደል የመለየት መሥዋዕት፥ ከመስፈሪያውም ከዐሥር እጅ አንድ እጅ የሆነ በዘይት የተለወሰ የስንዴ ዱቄት ለቍርባን፥ አንድ ማሰሮ ዘይትም ያመጣል። 22ሁለት ዋኖሶች፥ ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች በእጁ እንዳገኘ አንዲቱን ለኀጢአት መሥዋዕት፥ አንዲቱንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ይወስዳል። 23በስምንተኛውም ቀን ያነጹት ዘንድ ወደ ካህኑ ወደ ምስክሩ ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ያመጣቸዋል። 24ካህኑም የበደሉን መሥዋዕት የበግ ጠቦት የማሰሮውንም ዘይት ይወስዳል፤ በእግዚአብሔርም ፊት ለቍርባን ያቀርበዋል። 25የበደሉንም መሥዋዕት የበግ ጠቦት ያርዳል፤ ካህኑም ከበደሉ መሥዋዕት ደም ወስዶ የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት ይቀባዋል። 26ካህኑም ከዘይቱ በግራ እጁ ውስጥ ያፈስሰዋል። 27ካህኑም በግራ እጁ ውስጥ ከአለው ዘይት በቀኝ ጣቱ ሰባት ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ይረጨዋል። 28ካህኑም በእጁ ውስጥ ከአለው ዘይት የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት የበደል መሥዋዕት ደም ባረፈበት ላይ ይቀባዋል። 29በካህኑ እጅ ውስጥ የቀረውን ዘይት በሚነጻው ሰው ራስ ላይ ያደርገዋል፤ ካህኑም በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል። 30በእጁ ከአለው ከዋኖሶች ወይም ከርግብ ግልገሎች አንዱን ያቀርባል። 31አንዲቱን ለኀጢአት መሥዋዕት፥ ሌላዪቱንም ከእህል ቍርባን ጋር ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርባል፤ ካህኑም ለሚነጻው ሰው በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል። 32ለመንጻቱ የሚያስፈልገውን ነገር ለማያገኝ የለምጽ ደዌ ላለበት ሰው ሕጉ ይህ ነው።”
በቤት ላይ ስለሚታይ የለምጽ ደዌ ምልክት ሕግ
33እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ 34“ትወርሱአት ዘንድ እኔ ወደምሰጣችሁ ርስት ወደ ከነዓን ምድር በገባችሁ ጊዜ፥ እኔም የለምጽ ደዌ ምልክት በርስታችሁ ምድር ቤቶች ባደረግሁ ጊዜ፥ 35ባለቤቱ መጥቶ ካህኑን፦ ‘ደዌ በቤቴ ውስጥ እንዳለ አይቻለሁ’ ብሎ ይንገረው። 36ካህኑም በቤቱ ውስጥ ያለው ዕቃ ሁሉ እንዳይረክስ፥ እርሱ የለምጹን ምልክት ለማየት ወደ ቤት ሳይገባ፥ ቤቱን ባዶ እንዲያደርጉት ያዝዛል፤ በኋላም ካህኑ ቤቱን ለማየት ይገባል። 37የለምጹንም ምልክት ያያል፤ እነሆም፥ የለምጹ ምልክት በግንቡ ላይ በአረንጓዴና በቀይ ቢዥጐረጐር፥ መልኩም ወደ ግንቡ ውስጥ ቢጠልቅ፥ 38ካህኑ ከቤቱ ውስጥ ወደ ቤቱ በር ወጥቶ ሰባት ቀን ቤቱን ይዘጋዋል። 39ካህኑም በሰባተኛው ቀን ተመልሶ ቤቱን ያያል፤ 40እነሆም፥ ደዌው በቤቱ ግንብ ላይ ቢሰፋ፥ ካህኑ ደዌ ያለባቸውን ድንጋዮች እንዲያወጡ፥ ከከተማውም ወደ ውጭ ወደ ረከሰው ስፍራ እንዲጥሉአቸው ያዝዛል። 41ቤቱንም በውስጡ በዙሪያው ያስፍቀዋል፤ የፋቁትንም የምርጊቱን አፈር ከከተማው ወደ ውጭ ወደ ረከሰ ስፍራ ያፈስሱታል። 42በእነዚያም ድንጋዮች ስፍራ ሌሎች ድንጋዮችን ያገባሉ፤ ሌላም ጭቃ ወስደው ቤቱን ይመርጉታል።
43“ደዌውም ዳግም ቢመለስ፥ ድንጋዮቹም ከወጡ፥ ቤቱም ከተፋቀና ከተመረገ በኋላ በቤቱ ውስጥ ቢሰፋ፥ 44ካህኑ ገብቶ ያያል፤ እነሆም፥ ደዌው በቤቱ ውስጥ ቢሰፋ፥ በቤቱ ውስጥ ያለው እየፋገ የሚሄድ ለምጽ ነው፤ ርኩስ ነው። 45ቤቱንም፥ ድንጋዮቹንም፥ ዕንጨቱንም፥ የቤቱንም ምርጊት ሁሉ ያፈርሳል፤ እነርሱንም ከከተማው ወደ ውጭ ወደ ርኩስ ስፍራ ያወጣል። 46በተዘጋበትም ጊዜ ሁሉ ወደ ቤቱ የሚገባ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። 47በቤቱም የሚተኛ ልብሱን ያጥባል፤ እስከ ማታም ርኩስ ነው፤ በቤቱም የሚበላ ልብሱን ያጥባል፤ እስከ ማታም ርኩስ ነው።
48“ካህኑም ገብቶ ቢያየው፥ እነሆም፥ ቤቱ ከተመረገ በኋላ ደዌው በቤቱ ውስጥ ባይሰፋ፥ ደዌው ስለ ሻረ ካህኑ ቤቱን፦ ንጹሕ ነው ይለዋል። 49ካህኑም ቤቱን ለማንጻት ሁለት ዶሮዎች፥ የዝግባ ዕንጨት፥ ቀይ ግምጃ፥ ሂሶጵም#ሰሚዛ ይወስዳል። 50አንደኛዪቱንም ዶሮ በሸክላ ዕቃ ውስጥ ከምንጩ ውኃ በላይ ያርዳል። 51የዝግባውን ዕንጨት፥ ሂሶጱንም፥ ቀዩንም ግምጃ፥ ደኅነኛዪቱንም ዶሮ ወስዶ በታረደችው ዶሮ ደምና በምንጩ ውኃ ውስጥ ይነክራቸዋል፥ ቤቱንም ሰባት ጊዜ ይረጨዋል። 52ቤቱንም በዶሮዪቱ ደም በምንጩም ውኃ፥ በደኅነኛዪቱም ዶሮ፥ በዝግባውም ዕንጨት፥ በሂሶጱም፥ በቀዩም ግምጃ ያነጻዋል። 53ደኅነኛዪቱንም ዶሮ ከከተማ ወደ ሜዳ ይሰድዳታል፤ ለቤቱም ያስተሰርይለታል፤ ንጹሕም ይሆናል።
54“ይህም ሕግ ነው፤ ለሁሉ ዓይነት ለምጽና የቈረቈር ደዌ ሕጉ ይህ ነው፤ 55በልብስና በቤትም ላለ ለምጽ፥ 56ለዕባጭም፥ ለብጕርም፥ ለቋቍቻም፤ 57በሚረክስና በሚነጻ ጊዜ እንዲያስታውቅ ይህ የለምጽ ሕግ ነው።”
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 14: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ