መጽሐፈ ኢዮብ 3
3
ኢዮብ የተወለደበትን ቀን እንደ ረገመ
1ከዚያም በኋላ ኢዮብ አፉን ከፈተ፥ የተወለደባትንም ቀን ረገመ። 2እንዲህም አለ፦
3“ያች የተወለድሁባት ቀን ትጥፋ፥
ያችም፦ ወንድ ልጅ ነው ያሉባት ሌሊት።
4ያች ቀን ጨለማ ትሁን፤
እግዚአብሔር ከላይ አይመልከታት፥
ብርሃንም አይብራባት።
5ጨለማና የሞት ጥላ ያግኙአት፤
ጭጋግም ይምጣባት፤
6ያች ቀንም የተረገመች ትሁን።
ያችም ሌሊት ጨለማ ይምጣባት፤
በዓመቱ ቀኖች መካከል አትኑር፤
በወሮች ቀኖች ውስጥም ገብታ አትቈጠር።
7ለዚያም ሌሊት ጭንቅ ይሁን፥
እልልታ ወይም ደስታ አይግባባት።
8ነገር ግን ሌዋታንን ለመግደል የተዘጋጀ
ያችን ቀን የሚረግም ይርገማት።
9የዚያ ሌሊት ኮከቦች ይጨልሙ፤
ሌሊቱም በጨለማ ይኑር፤
ወደ ብርሃንም አይምጣ፤
የንጋት ኮከብም ሲወጣ አይይ፤
10የእናቴን ማኅፀን ደጅ አልዘጋምና፥
መከራውንም ከዐይኔ አልሰወረምና።
11በማኅፀን ሳለሁ ስለ ምን አልሞትሁም?
ከሆድስ በወጣሁ ጊዜ ወዲያውኑ ስለ ምን አልጠፋሁም?
12ጕልበቶች ስለ ምን ደገፉኝ?
ጡትስ ስለ ምን ጠባሁ?
13አሁንም ተኝቼ ዝም ባልሁ ነበር፤
አንቀላፍቼም ባረፍሁ ነበር፤
14በሰይፋቸው ከከበሩ
ከምድር ነገሥታትና መካሮች ጋር፥
15ወይም ወርቅን ካበዙ፥
ቤታቸውንም ብር ከሞሉ አለቆች ጋር፥
16ወይም ከእናቱ ማኅፀን እንደ ወጣ ጭንጋፍ፥
ብርሃንም እንዳላዩ ሕፃናት በሆንሁ ነበር።
17ኃጥኣን በዚያ በቍጣው መቅሠፍት ይቃጠላሉ፤
በዚያም በሥጋቸው የተጨነቁት ያርፋሉ።
18በዚያም የጥንት ዘመን ሰዎች በአንድነት፥
የአስጨናቂውን ድምፅ አይሰሙም።
19ታናሹና ታላቁ በዚያ አሉ፤
ጌታውን ያገለገለ ባሪያም በዚያ አለ።
20በመራራነት ላሉት ብርሃን፥
በነፍስ ለተጨነቁትም ሕይወት፥
21የተሰወረ ሀብትን ከሚቈፍሩ ይልቅ፥
ሞትን ለሚመኙ ለማያገኙትም፥
22ባገኙትም ጊዜ ደስ ለሚላቸው፥
ሕይወት ስለ ምን ተሰጠ?
23ሞት ለሰው ዕረፍቱ ነው፥
እግዚአብሔርም ከእርሱ ከለከለው።
24ከአዝመራዬ#ግሪክ ሰባ. ሊ. እና ዕብ. “ከእንጀራዬ በፊት” ይላል። በፊት ልቅሶዬ መጥቶአልና፥
ስለ ደረሰብኝም አስፈሪ ነገር ሁልጊዜ አለቅሳለሁ።
25የተጠራጠርሁት#ግእዝ “ያልጠረጠርሁት” ይላል። ነገር መጥቶብኛልና፥
ያሰብሁትም#ግእዝ “ያላሰብሁት” ይላል። ደርሶብኛል።
26ተዘልዬ አልተቀመጥሁም፥
ፀጥታም አላገኘሁም፥ አላረፍሁም።
ነገር ግን መከራ ደረሰችብኝ።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 3: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ