መጽሐፈ ኢዮብ 4
4
የኤልፋዝ ንግግር
1ቴማናዊውም ኤልፋዝ መለሰ፥ እንዲህም አለ፦
2“በመከራ ሳለህ ነገር አታብዛ፥ የነገር ብዛት ምን ይጠቅምሃል?
3እነሆ፥ አንተ ብዙዎችን ታስተምር ነበር፥
የደከሙትንም እጆች ታበረታ ነበር፥
4በቃልህ በሽተኞችን ታስነሣ ነበር፥
የሚብረከረከውንም ጕልበት ታጸና ነበር።
5አሁን ግን ሕማም በአንተ ላይ መጥቶ ዳሰሰህ።
አንተም ተቸገርህ።
6ጥንቱን ፍርሀትህ፥ ተስፋህም፥
የመንገድህም ጠማማነት፥ ስንፍና አይደለምን?#ከዕብራይስጡ ጋር ልዩነት አለው።
7እባክህ አስብ፥ ንጹሕ ሆኖ የጠፋ ማን ነው?
ከጻድቃንስ የተደመሰሰ ማን ነው?
8እኔ እንዳየሁ፥ ኀጢኣትን የሚያርሱ፥ የሚዘሩአትም#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ባዶ ቦታን የሚያርሱና የሚዘሩ...” ይላል።
መከራን ለራሳቸው ያጭዳሉ።
9በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ይጠፋሉ፥
በቍጣውም መንፈስ ያልቃሉ።
10የአንበሳው ጩኸት፥ የአንበሳዪቱም ድምፅ፥
የእባቦችም አስፈሪ ጩኸት ጠፉ።
11“ገብረ ጉንዳን ምግብ በማጣት አለቀ፥
የአንበሳዪቱ ግልገሎችም እርስ በእርሳቸው ተላለቁ።
12ነገር ግን አንተ አንዳች እውነት አድርገህ ቢሆን ኖሮ፥
ይህ ሁሉ ባልደረሰብህም ነበር።
በእኔ ዘንድ ነገር ይነሣል፤
ዦሮዬም ከእርሱ ድምፅን ትሰማለች፤
ጥንቱን የነገረኝን አላምነውምን?
13በሰዎች ላይ ፍርሀት በወደቀ ጊዜ
በሌሊት ከፍርሀትና ከድምፅ ጋር
14ድንጋጤና መንቀጥቀጥ ያዙኝ፤
አጥንቶቼም ሁሉ እጅግ ተነዋወጡ፤
15መንፈሴም በፊቴ ዐለፈ፥
ሥጋዬም፥ ጠጕሬም ተቈጣ።
16ተነሣሁ፤ ነገር ግን አላወቅሁም፥
ተመለከትሁ፥ በዐይኖቼም ፊት መልክ አልነበረም።
ነገር ግን ጥላን አያለሁ፤ ድምፅንም እሰማለሁ፦
17በእግዚአብሔር ፊት ንጹሕ የሚሆን ሟች ማን ነው?
በሥራውስ የሚጸድቅ ሰው ማን ነው?
18እነሆ፥ አገልጋዮቹንም አይተማመናቸውም፥
መላእክቱንም በጭንቅ ይጠራጠራቸዋል።
19ይልቁንም ከአንድ ዐይነት ጭቃ የተፈጠርን እኛ፥
በተፈጠርንበት የጭቃ ቤት የሚኖሩትን
እንደ ብል ይጨፈልቃቸዋል።
20ከጥዋት እስከ ማታ አይኖሩም።
ራሳቸውን ማዳንና መርዳት አይችሉምና ጠፉ።
21እፍ ብሎባቸዋልና ይደርቃሉ፥
ጥበብም የላቸውምና ይጠፋሉ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 4: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ