መጽሐፈ ኢዮብ 1
1
ኢዮብ እንደ ተፈተነ
1አውስጢድ#ዕብ. “ዖፅ” ይላል። በሚባል ሀገር ስሙ ኢዮብ የተባለ አንድ ሰው ነበረ፤ ያም ሰው ቅን፥ ንጹሕና ጻድቅ፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፉ ሥራም ሁሉ የራቀ ነበር። 2ሰባትም ወንዶች፥ ሦስትም ሴቶች ልጆች ነበሩት። 3ከብቶቹም፦ ሰባት ሺህ በጎች፥ ሦስት ሺህ ግመሎች፥ አምስት መቶም ጥማድ በሬ፥ አምስት መቶም እንስት አህዮች ነበሩ፤ እጅግ ብዙም አገልጋዮች ነበሩት፤ ሥራውም በምድር ላይ ታላቅ ነበረ፤ ያም ሰው በምሥራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ገናና ነበረ።
4ወንዶች ልጆቹም ሄደው በየተራ በእያንዳንዳቸው ቤት ግብዣ ያደርጉ ነበር፤ ሦስቱ እኅቶቻቸውንም ከእነርሱ ጋር ይወስዱአቸው ነበር፤ ከእነርሱም ጋር ይበሉና ይጠጡ ነበር። 5የግብዣውም ቀኖች በተፈጸሙ ጊዜ ኢዮብ ይልክና ይቀድሳቸው ነበር፤ በማለዳም ገሥግሦ፦ ስለ ልጆቹ በቍጥራቸው መሥዋዕት ያቀርብ ነበር፤ አንድ ወይፈን ስለ ነፍሳቸው የኀጢአት መሥዋዕት ያቀርብ ነበር፤ ኢዮብ፥ “ምናልባት ልጆቼ በልባቸው በእግዚአብሔር ላይ ክፉ ነገር ያስቡ ይሆናል” ይል ነበርና።
6ከዕለታት አንድ ቀንም እንዲህ ሆነ፤ የእግዚአብሔር መላእክት#ዕብ. “የአምላክ ልጆች” ይላል። በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም መጡ፤ ሰይጣንም ደግሞ ከእነርሱ ጋር መጣ። 7እግዚአብሔርም ሰይጣንን፥ “ከወዴት መጣህ?” አለው። ሰይጣንም፥ “ምድርን ሁሉ ዞርሁአት፥ ከሰማይ በታችም ተመላለስሁና መጣሁ።” ብሎ ለእግዚአብሔር መለሰ። 8እግዚአብሔርም ሰይጣንን አለው፥ “በባሪያዬ በኢዮብ ላይ የምታስበው ነገር እንዳይኖር ተጠንቀቅ! በምድር ላይ እንደ እርሱ ቅን፥ ንጹሕና ጻድቅ፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፉ ሥራም ሁሉ የራቀ ሰው የለምና።” 9ሰይጣንም በእግዚአብሔር ፊት እንዲህ ብሎ መለሰ፥ “በውኑ ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚያመልከው በከንቱ ነውን? 10አንተ ቤቱን በውስጥም በውጭም፥ በዙሪያው ያለውንም ሁሉ አልሞላህለትምን? የእጁንም ሥራ ባርከህለታል፥ ከብቱንም በምድር ላይ አብዝተህለታል። 11ነገር ግን እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ ዳስስ፤ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል።” 12እግዚአብሔርም ሰይጣንን፥ “እነሆ፥ ለእርሱ ያለውን ሁሉ በእጅህ ሰጠሁህ፥ ነገር ግን በእርሱ ላይ እጅህን አትዘርጋ” አለው። ሰይጣንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ።
የኢዮብ ንብረት እንደ ጠፋና ልጆቹ እንደ ሞቱ
13አንድ ቀንም እንዲህ ሆነ፤ የኢዮብ ወንዶችና ሴቶች ልጆች በታላቅ ወንድማቸው ቤት ይበሉና የወይን ጠጅ ይጠጡ ነበር። 14መልእክተኛም ወደ ኢዮብ መጥቶ፥ “ጥምድ በሬዎችህ እርሻ ያርሱ ነበር፥ በአጠገባቸውም ሴቶች አህዮችህ ይሰማሩ ነበር፤ 15ማራኪዎችም#ዕብ. “የሳባ ሰዎች” ይላል። መጥተው ወሰዱአቸው፥ ብላቴኖችህንም በሰይፍ ስለት ገደሉ፥ እኔም ብቻዬን አምልጬ እነግርህ ዘንድ መጣሁ” አለው። 16እርሱም ገና ይህን ሲናገር ሌላ መልእክተኛ መጥቶ፦ ለኢዮብ እንዲህ አለው፥ “እሳት ከሰማይ ወደቀች፥ በጎችህንም አቃጠለች፥ ጠባቂዎችህንም በላች፤ እኔም ብቻዬን አምልጬ እነግርህ ዘንድ መጣሁ።” 17እርሱም ገና ይህን ሲናገር ሦስተኛው መልእክተኛ መጥቶ ለኢዮብ እንዲህ አለው፥ “ፈረሰኞች#ዕብ. “ከለዳውያን” ይላል። በሦስት ረድፍ ከብበው ግመሎችን ማርከው ወሰዱ፥ ብላቴኖችህንም በሰይፍ ስለት ገደሉ፤ እኔም ብቻዬን አምልጬ እነግርህ ዘንድ መጣሁ።” 18እርሱም ገና ይህን ሲናገር አራተኛው መልእክተኛ መጥቶ ለኢዮብ እንዲህ አለው፥ “ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ በታላቅ ወንድማቸው ቤት ሲበሉና የወይን ጠጅ ሲጠጡ፥ 19እነሆ፥ ዐውሎ ነፋስ ከምድረ በዳ ድንገት መጥቶ ቤቱን በአራት ማዕዘኑ መታው፥ ቤቱም በብላቴኖቹ ላይ ወደቀ፥ እነርሱም ሞቱ፤ እኔም ብቻዬን አምልጬ እነግርህ ዘንድ መጣሁ።”
20ኢዮብም ተነሣ መጐናጸፊያውንም ቀደደ፥ ራሱንም ተላጨ፥ በምድርም ላይ ተደፍቶ ሰገደ፤ 21እንዲህም አለ፥ “ከእናቴ ማኅፀን ራቁቴን ወጥቻለሁ፥ ራቁቴንም ወደ ምድር#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “ወደዚያው እመለሳለሁ” ይላል። እመለሳለሁ፤ እግዚአብሔር ሰጠ፥ እግዚአብሔርም ነሣ፤ እግዚአብሔርም እንደ ፈቀደ ሆነ#“እግዚአብሔር እንደ ፈቀደ ሆነ” የሚለው በዕብ. የለም። የእግዚአብብሔር ስም የተባረከ ይሁን።” 22በዚህም በደረሰበት ሁሉ ኢዮብ በእግዚአብሔር ፊት አልበደለም፥ ለእግዚአብሔርም ስንፍናን አልሰጠም።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 1: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ