መጽሐፈ መቃብያን ሣልስ 10
10
1የሙታንን ትንሣኤ ከአላመንህ ሳይወለዱ ነፍሳት በክረምት ምን ያህል እንደሚነሡ ስማ፤ ቀድሞ እፍ እንዳለባቸው የእግዚአብሔር መንፈስ በእነርሱ ላይ ያርፋልና። 2እንዲሞቱም ቀድሞ በቃሉ ያዛቸዋል። 3ሥጋቸው ፈርሶ ሳለ እርሱ እንደ ወደደ ይነሣሉ፤ ዳግመኛም ይታደሳሉ። 4ዳግመኛም ዝናም በሚወርድ ጊዜ ምድርንም በሚአረካት ጊዜ ይነሣሉ፤ ቀድሞም እንደ ተሠራላቸው ይኖራሉ። 5በደማዊት ነፍስ ሕያዋን የሚሆኑትና በምድር ላይ የሚንቀሳቀስ፥ ውኃም የሚያስገኛቸው ሁሉ እርሱ አዝዞአልና ተፈጠሩ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃው ላይ ይሰፍፍ ነበርና፤ በመንፈሱና በቃሉም ደማዊት ነፍስ ትሰጣቸዋለች። 6ሙታን አይነሡም የምትል አንተ ልበ-ዕውር እስኪ ተመልከት፤ በመንፈሱና በቃሉ ያለ አባትና እናት ይፈጠራሉና፤ ጥበብ ካለህስ ሙታን በፈጣሪያቸው በእግዚአብሔር ቃል አይነሡም እንዴት ትላለህ? 7አንተስ ንስሓ ግባ፤ ወደ እምነትህም ተመለስ፤ በመቃብር ኣመድና ትቢያ የሆኑ ሙታን በእግዚአብሔር ቃል ይነሣሉና። 8ቀድሞ ቃሉ እንደ ተናገረ ከእግዚአብሔር በተገኘ በይቅርታ ጠል ይነሣሉ፤ ያም ቃል ሁሉን ዞሮ ሙታንን እንደ ወደደ ያስነሣቸዋል። 9ተነሥተህም በፊቱ እንደምትቆም ዕወቅ፤ እንደ አሳብህም በመቃብር የምትቀር አይምሰልህ። 10እንዲህ አይደለም፥ በምድር እንደ ሠራኸው ሥራ በጎም ቢሆን፥ ክፉም ቢሆን፥ ተነሥተህ ዋጋህን ትቀበላለህ፤ ይህች የፍዳ ቀን ናትና። 11በትንሣኤም ጊዜ በሠራኸው ኀጢአትህ ሁሉ ፍዳህን ትቀበላለህ፤ ከሕፃንነትህ ጀምሮ እስከዚያ ጊዜ ድረስ የተጻፈ ዕዳህን ትጨርሳለህ፤ ኀጢአትህንም ትክድ ዘንድ እንደዚህ ዓለም ሥራ በኀጢአትህ የምታመካኘው ምክንያት የለህም።
12ሐሰተኛ ቃልህን በፊትህ እውነት እንደምታደርገው፥ የተናገርኸው ሐሰቱንም ነገር እውነት እንደምታደርገው፥ በዚያ የምታመካኘው ምክንያት የለህም። 13እርሷ የሠራኸውን ክፉ ሥራህን ሁሉ የምታውቅብህ ስለሆነ በፈጣሪዋ በእግዚአብሔር ፊትም የምትገልጥብህ ስለ ሆነ የእግዚአብሔር ቃሉ በአንተ አድሮ ይናገርብሃልና። 14በዚያም ስለ ሠራኸው ኀጢአትህ ታፍራለህ፤ በመልካም ሥራቸው ከሚመሰገኑ ጋር ትመሰገን ዘንድ ነው እንጂ በፍርድ ቀን በመላእክትና በሰዎች ፊት እንዳታፍር ወደዚያ ሳትደርስ በዚህ ንስሓ ለመግባት ፍጠን።
15ከመላእክት ጋራ እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑ ያለ ኀፍረት ከፈጣሪያቸው ዋጋቸውን ይቀበላሉ፤ ደስም ይላቸዋል፤ ነገር ግን በሥጋህ በሕይወት ሳለህ በጎ ሥራን ካልሠራህ ከጻድቃን ጋር እድል የለህም። 16ዕውቀት ሳለህ፥ ዋጋና ገብያም ሳለህ አልተዘጋጀህምና፥ ገንዘብም ሳለህ ለተራበው አላጐረስኸውምና የማይረባ ጸጸት ይሆንብሃል። 17ልብስም ሳለህ የታረዘውን አላለበስኸውምና፥ ሥልጣንም ሳለህ የተበደለውን አላዳንኸውምና። 18ዕውቀትም ሳለህ ተመልሶ ንስሓ ይገባ ዘንድ፥ ቀድሞ ባለማወቅ የሠራውንም ኀጢአቱን እግዚአብሔር ይቅር ይለው ዘንድ ኃጥኡን ሰው አላስተማርኸውምና፥ ድል መንሣትንም ትችል ዘንድ ኀይል ሳለህ ከሚጣሉህ ከአጋንንት ጋር አልተዋጋህም። 19ጽናትም ሳለህ በሥጋ ያለ የሕፃንነትህን ኀይል ታደክም ዘንድ በዓለም ያለ ሥጋን ለማስደሰት ያይደለ ለጽድቅ ራስህን ታስገዛ ዘንድ አልጾምህም፤ አልጸለይህምም።
20በዓለም በአለ ደስታ፥ በጣፋጭ ምግቦችና በማለፊያ መጠጥ አይደለም፤ በቀጭን ልብስም በወርቅና በብር በማጌጥም አይደለም። 21በከበሩ በሕንደኬ ዕንቍዎች፥ በጳዝዮንና በመረግድ አይደለም፤ ይህ የሚገባ የሰው ጌጥ አይደለም። 22ለሰውስ ጌጡ ንጽሕና፥ ጥበብና ዕውቅት፥ ያለ መቅናትና ያለ ምቀኝነት፥ ያለ መጠራጠርና ያለ ጠብ በሚገባ መዋደድ ነው። 23ባልንጀራህን እንደ ራስህ እየወደድህ፥ ክፉ ባደረገብህ ሰውም ክፉ ነገር ሳታደርግ፥ መከራውን ለታገሡ ሰዎች ወደ ተሰጠ ማደሪያም ትገባ ዘንድ፥ ቅድስት ምድርን በትዕግሥትና በዕውቀት፥ በትንሣኤም ጊዜ መንግሥተ ሰማይን ተስፋ በማድረግ ከወረስዋት ሰዎች ጋር ዋጋህን ይሰጥህ ዘንድ ነው። 24“ከሞትን በኋላ አንነሣም” አትበሉ፤ ይኽን የሚናገሩና የሚያስቡ ሰዎችን በትንሣኤ ጊዜ እንዳይድኑ ዲያብሎስ ተስፋ ያስቈርጣቸዋልና፥ ትንሣኤም በደረሰችባቸው ጊዜ ያውቃሉ፤ ኀጢአታቸውን ያስብባቸው ዘንድ ባለ ማወቅ ኀጢአት የሠሩ ሰዎች በትንሣኤ ጊዜ ፈጽመው ያዝናሉ፤ በዚያች ቀን እንደሚነሡ አላመኑበትምና። 25ስለዚህም በምድር ላይ እንደ ሠሩት ሥራቸው ክፋት ይወቀሳሉ፤ በሥጋ በአንድነት የሚነሡባትን የካዷትንም ትንሣኤ ያዩአታል። 26ሥራቸውንም ስላላሳመሩ ያንጊዜ ያለቅሳሉ፤ ቢቻላቸውስ በዚያ የሚያለቅሱ እንዳይሆኑ፥ በዚህ ዓለም ቢያለቅሱ በተሻላቸው ነበር። 27በዚህ በፈቃዳችን ካላለቀስን፥ በዚያ ያለፈቃዳችን ያስለቅሱናል፤ በዚህ ንስሓን ካላዘጋጀን፥ በዚያ የማይረባና የማይጠቅም ጩኸትንና ልቅሶን እናዘጋጃለን። 28ከሞት ወደ ሕይወት፥ ከምታልፍ ከዚህች ዓለምም ወደ ላይኝ`ዋ መንግሥተ ሰማይ፥ ከዚች ምድራዊት ብርሃንም ወደ ሰማያዊት ብርሃን ትሸጋገሩ ዘንድ መልካም ሥራን አዘጋጁ። 29የሙታን ትንሣኤን ከሚያምኑ ሰዎች ጋር በማያልቅ ደስታ በመንግሥተ ሰማይ ደስ ይልህ ዘንድ በምድር ያለች ደስታን እንቢ በላት፤ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም አሜን።
Currently Selected:
መጽሐፈ መቃብያን ሣልስ 10: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ