ትንቢተ ኢሳይያስ 14
14
ስለ እስራኤል ሕዝብ ከስደት መመለስ
1እግዚአብሔርም ያዕቆብን ይምረዋል፤ እስራኤልንም ደግሞ ይመርጠዋል፤ በሀገራቸውም ያርፋሉ፤ መጻተኞችም ከእነርሱ ጋር አንድ ይሆናሉ፤ ከያዕቆብም ቤት ጋር ይጨመራሉ። 2አሕዛብም ይዘው ወደ ስፍራቸው ያመጡአቸዋል፤ የእስራኤልም ወገኖች ይካፈሏቸዋል፤ በዚያም ሀገር ይበዛሉ፤ በዚያም ወንዶች ባሮችና ሴቶች ባሮች ይሆናሉ። ማርከው የወሰዷቸውም ለእነርሱ ምርኮኞች ይሆናሉ፤ የገዙአቸውም ይገዙላቸዋል።
3በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ እግዚአብሔር ከኀዘንህና ከመከራህ፥ ከተገዛህለትም ከጽኑ ባርነት ያሳርፍሃል። 4ይህንም ሙሾ በባቢሎን ንጉሥ ላይ ታነሣለህ፤#ግእዝ “የባቢሎንን መንግሥት ዙፋን ትወስዳለህ” ይላል። እንዲህም ትላለህ፥ “አስጨናቂ እንዴት ዐረፈ! አስገባሪም እንዴት ጸጥ አለ! 5እግዚአብሔር የኀጢአተኞችን ቀንበርና የአለቆችን ቀንበር ሰብሮአልና። 6እግዚአብሔር በቍጣው መቅሠፍት አሕዛብን ገርፎአቸዋልና፥ ከቍጣውም መቅሠፍት አልራራላቸውምና። 7ምድርም ሁሉ ዐርፋ በጸጥታ ተቀምጣለች፤ እልልም ብላለች። 8የሊባኖስ ዛፎች፦ አንተ ከተዋረድህ ጀምሮ ማንም ይቈርጠን ዘንድ አልወጣብንም ብለው በአንተ ደስ አላቸው።
9“ሲኦልም በመምጣትህ ልትገናኝህ በታች ታወከች፤ የአሕዛብን ነገሥታት ሁሉ ከዙፋናቸው ያስነሡ፥ ምድርን የገዙአት አርበኞች ሁሉ በአንድነት በአንተ ላይ ተነሡ። 10እነዚህ ሁሉ፦ አንተ ደግሞ እንደ እኛ ተይዘሃል፤ እንደ እኛም ተቈጥረሃል። 11ከክብርህ ወደ ሲኦል ወደቅህ፤ በበታችህም ብል ተነጥፎአል፤ ትልም መደረቢያህ ሆኖአል” ብለው ይመልሱልሃል።
12“አንተ በንጋት የሚወጣ የአጥቢያ ኮከብ ሆይ፥ እንዴት ከሰማይ ወደቅህ! ወደ አሕዛብም መልእክትን የላክህ አንተ ሆይ፥ እንዴት እስከ ምድር ድረስ ተቀጠቀጥህ! 13አንተም በልብህ፦ ወደ ሰማይ ዐርጋለሁ፤ ዙፋኔንም ከሰማይ ከዋክብት በላይ ከፍ ከፍ አደርጋለሁ፤ በሰሜንም#ግእዝ “ደቡብ” ይላል። ዳርቻ በረዣዥም ተራሮች ላይ እቀመጣለሁ፤ 14ከደመናዎች ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ፤ በልዑልም እመሰላለሁ አልህ። 15ዛሬ ግን ወደ ሲኦል ትወድቃለህ፤ ወደ ምድር ጥልቅም ትወርዳለህ። 16የሚመለከቱህም ይደነቃሉ፤ እንዲህም ይላሉ፦ በውኑ ምድርን ያንቀጠቀጠ፥ መንግሥታትንም ያናወጠ፥ 17ዓለሙን ሁሉ ባድማ ያደረገ፥ ከተሞችንም ያፈረሰ፥ ምርኮኞቹንም ወደ ቤታቸው ያልሰደደ ሰው ይህ ነውን?
18“የአሕዛብ ነገሥታት ሁሉ በየቤታቸው በክብር አንቀላፍተዋል። 19አንተ ግን በጦር ተወግተው ወደ መቃብር ከሚወርዱ ብዙ ሙታን ጋር እንደ ረከሰ ሬሳ በተራሮች ላይ ትጣላለህ። 20ንጹሕ እንዳልሆነና በደም እንደ ረከሰ ልብስ አንተም ንጹሕ አይደለህም። ምድሬን አጥፍተሃልና፥ ሕዝቤንም ገድለሃልና ክፉ ዘር አንተ እንግዲህ ለዘለዓለም አትኖርም። 21እንዳይነሡም፥ ምድርንም እንዳይወርሱ፥ የዓለሙንም ፊት በጦርነት እንዳይሞሉ በአባቶቻቸው በደል ይገድሉአቸው ዘንድ ልጆችህን አዘጋጅ።” 22“በእነርሱ ላይ እነሣለሁ” ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ “ስምንና ቅሬታን፥ ዘርንና ትውልድንም አጠፋለሁ” ይላል እግዚአብሔር። 23“ባቢሎንን የወፎች መኖሪያ አደርጋታለሁ፤ እንደ ኢምንትም ትሆናለች፤ በጥፋትም እንደ ረግረግ ጭቃ አደርጋታለሁ” ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
በአሦር ላይ የተነገረ ትንቢት
24የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ምሎአል፥ “እንደ ተናገርሁ በእርግጥ ይሆናል፤ እንደ መከርሁም እንዲሁ ይጸናል። 25አሦርን በምድሬ ላይ እሰብረዋለሁ፤ በተራራዬም ላይ እረግጠዋለሁ፤ ቀንበሩም ከእነርሱ ላይ ይነሣል፤ ሸክሙም ከጫንቃቸው ላይ ይወገዳል።” 26በምድር ሁሉ ላይ እግዚአብሔር ያሰበው ዐሳብ ይህ ነው፤ በአሕዛብም ሁሉ የተዘረጋች እጅ ይህች ናት። 27ቅዱስ እግዚአብሔር ይህን መክሮአል፤ የእግዚአብሔርን ምክር የሚመልስ ማን ነው? የተዘረጋች እጁንስ የሚመልሳት ማን ነው?
በፍልስጥኤም ላይ የተነገረ ትንቢት
28ንጉሡ አካዝ በሞተበት ዓመት ይህ ነገር ሆነ። 29ፍልስጥኤም ሆይ፥ ከእባቡ ዘር እፉኝት ይወጣልና፥ ፍሬውም የሚበርርና እሳት የሚመስል እባብ ይሆናልና፥ የኀይላችሁ ቀንበር ተሰብሮአልና ሁላችሁም ደስ አይበላችሁ። 30ድሆችም በውስጣችሁ ይሰማራሉ፤ ድሆች ሰዎችም በሰላም ያርፋሉ፤ ዘራችሁንም ረኃብ ያጠፋቸዋል፤ ከእናንተም የቀሩት ያልቃሉ። 31እናንተ የከተሞች በሮች ሆይ፥ ወዮ በሉ፤ እናንተም ከተሞች ሆይ፥ ደንግጡ፥ ጩኹም፤ ፍልስጥኤማውያን ሆይ፥ ሁላችሁም ቀልጣችኋል፤ ጢስ ከሰሜን ይወጣልና፥ እንግዲህም አትኖሩምና።
32የአሕዛብ ነገሥታት ምን ይመልሳሉ? እግዚአብሔር ጽዮንን መሠረታት፤ ትሑታን የሆኑትንም ሕዝብ አዳናቸው።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 14: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ