መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 18
18
የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ
(2ዜ.መ. 29፥1-2፤ 31፥1)
1እንዲህም ሆነ፤ የእስራኤል ንጉሥ የኤላ ልጅ ሆሴዕ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የአካዝ ልጅ ሕዝቅያስ ነገሠ። 2መንገሥ በጀመረ ጊዜም የሃያ አምስት ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የዘካርያስ ልጅ አቡ ትባል ነበር። 3እርሱም አባቱ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገርን አደረገ። 4በኮረብታም ያሉትን መስገጃዎች አስወገደ፤ ሐውልቶችንም ሰባበረ፤ የማምለኪያ ዐፀዶችንም ነቃቀለ፤ የእስራኤል ልጆች እስከዚህ ዘመን ድረስ ያጥኑለት ነበርና ሙሴ የሠራውን የናሱን እባብ አጠፋ፤ ስሙንም “ነሑስታን” ብሎ ጠራው። 5በእስራኤልም አምላክ በእግዚአብሔር ታመነ፤ ከእርሱ በፊት#ዕብ. “ከእርሱ በኋላና ከእርሱ በፊት” ይላል። ከነበሩት ከይሁዳ ነገሥታት ሁሉ እርሱን የሚመስል አልነበረም። 6እግዚአብሔርንም ተከተለ፤ እርሱንም ከመከተል አልራቀም፤ እግዚአብሔርም ለሙሴ ያዘዘውን ትእዛዛቱን ጠበቀ። 7በሚሠራውም ሥራ ሁሉ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረ፤ በአሦርም ንጉሥ ላይ ዐመፀ፤ አልተገዛለትምም። 8ፍልስጥኤማውያንንም እስከ ጋዛና እስከ ዳርቻዋ ድረስ፥ ከዘበኞች ግንብ ጀምሮ እስከ ምሽጉ ከተማ ድረስ አጠፋ።
9ሕዝቅያስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፥ የእስራኤል ንጉሥ የኤላ ልጅ ሆሴዕ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት፥ የአሦር ንጉሥ ስልምናሶር ወደ ሰማርያ ወጣ፤ ከበባትም። 10በሦስተኛውም ዓመት ያዛት፤ በሕዝቅያስ በስድስተኛው ዓመተ መንግሥት፥ በእስራኤል ንጉሥ በሆሴዕ በዘጠነኛው ዓመተ መንገሥት፥ ሰማርያ ተያዘች። 11የአሦርም ንጉሥ እስራኤልን ወደ አሦር አፈለሰ፤ በአላሔና በአቦር በጎዛንም ወንዝ፥ በሜዶንም አውራጃዎች አኖራቸው፤ 12የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰሙምና፥ ቃል ኪዳኑንም አፍርሰዋልና፥ የእግዚአብሔርም ባሪያ ሙሴ ያዘዘውን ሁሉ አልሰሙምና፤ አላደረጉምምና።
13ሕዝቅያስም በነገሠ በዐሥራ አራተኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ወደ ይሁዳ ወደ ተመሸጉት ከተሞች ሁሉ ወጣ፤ ወሰዳቸውም። 14የይሁዳም ንጉሥ ሕዝቅያስ፥ “በድያለሁ፥ ከእኔ ተመለስ፤ የምትጭንብኝንም ሁሉ እሸከማለሁ” ብሎ ወደ አሦር ንጉሥ ወደ ለኪሶ መልእክተኞችን ላከ። የአሦርም ንጉሥ በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ላይ ሦስት መቶ መክሊት ብርና ሠላሳ መክሊት ወርቅ ጫነበት። 15ሕዝቅያስም በእግዚአብሔር ቤትና በንጉሡ ቤተ መዛግብት የተገኘውን ብር ሁሉ ሰጠው። 16በዚያን ጊዜም ሕዝቅያስ ከእግዚአብሔር መቅደስ ደጆችና የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ከለበጣቸው መቃኖች ወርቁን ቈረጠ፤ ለአሦርም ንጉሥ ሰጠው።
17የአሦርም ንጉሥ ተርታንንና ራፌስን ራፋስቂስንም ከብዙ ሠራዊት ጋር ከለኪሶ ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ ወደ ኢየሩሳሌም ላካቸው። ወጥተውም ወደ ኢየሩሳሌም ደረሱ፤ በአጣቢውም እርሻ መንገድ ባለችው በላዪኛዪቱ ኩሬ መስኖ አጠገብ ቆሙ። 18ሕዝቅያስንም ጠሩ፤ የቤቱም አዛዥ የኬልቅዩ ልጅ ኤልያቄም ጸሓፊውም ሳምናስ ታሪክ ጸሓፊውም የአሳፍ ልጅ ዮአስ ወደ እነርሱ ወጡ።
19ራፋስቂስም አላቸው፥ “ለሕዝቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦ ታላቁ ንጉሥ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ ይህ የምትተማመንበት መተማመኛ ምንድን ነው? 20የከንፈር ቃል ለሰልፍ ምክርና ኀይል እንደሚሆን ትናገራለህ፤ አሁንም በእኔ ላይ ያመፅኸው በማን ተማምነህ ነው? 21እነሆ፥ በዚህ በተቀጠቀጠ በሸምበቆ በትር በግብፅ ትታመናለህ፤ ሰው ቢመረኰዘው ተሰብሮ በእጁ ይገባል፥ ያቈስለውማል፤ የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን ለሚታመኑበት ሁሉ እንዲሁ ነው። 22እናንተም፦ በአምላካችን በእግዚአብሔር እንታመናለን ብትሉኝ፥ ሕዝቅያስ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን፦ በኢየሩሳሌም ባለው በዚህ መሠዊያ ፊት ስገዱ ብሎ የኮረብታ መስገጃዎቹንና መሠዊያዎቹን ያስፈረሰ ይህ አይደለምን? 23አሁንም እንግዲህ ከጌታዬ ከአሦር ንጉሥ ጋር ተወራረድ፤ የሚቀመጡባቸውንም ሰዎች ማግኘት ቢቻልህ እኔ ሁለት ሺህ ፈረሶች እሰጥሃለሁ። 24ስለ ሰረገሎችና ስለ ፈረሶች በግብፅ ስትታመን፥ ከጌታዬ አገልጋዮች የሚያንሰውን የአንዱን አለቃ ፊት ትመልስ ዘንድ እንዴት ይቻልሃል? 25አሁን በውኑ ያለ እግዚአብሔር ትእዛዝ ይህን ስፍራ እናጠፋ ዘንድ ወጥተናልን? እግዚአብሔር፦ ወደዚች ሀገር ወጥታችሁ አጥፉአት አለን።”
26የኬልቅዩም ልጅ ኤልያቄም ሳምናስም ዮአስም ራፋስቂስን፥ “እኛ እንሰማለንና በሱርስት ቋንቋ ለአገልጋዮችህ ተናገር፤ በዕብራይስጥም ቋንቋ አትናገረን፤ በቅጥርም ላይ ያለው ሕዝብ በሚሰማው ቋንቋ ለምን ትናገራለህ?” አሉት። 27ራፋስቂስ ግን፥ “በውኑ ጌታዬ ይህን ቃል እናገር ዘንድ ወደ እናንተና ወደ ጌታችሁ ልኮኛልን? ከእናንተ ጋር ኵሳቸውን ይበሉ ዘንድ ሽንታቸውንም ይጠጡ ዘንድ በቅጥር ላይ ወደ ተቀመጡት ሰዎች አይደለምን?” አላቸው። 28ራፋስቂስም ቆሞ በታላቅ ድምፅ በዕብራይስጥ ቋንቋ እንዲህ ብሎ ጮኸ፥ “የታላቁን የአሦር ንጉሥ ቃል ስሙ፤ 29ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ ከእጄ ያድናችሁ ዘንድ አይችልምና ሕዝቅያስ አያታልላችሁ፤ 30ሕዝቅያስም፦ እግዚአብሔር በእርግጥ ያድነናል፤ ይህችንም ከተማ የአሦር ንጉሥ ሊይዛት አይችልም እያለ በእግዚአብሔር እንድትታመኑ አያድርጋችሁ። 31ሕዝቅያስንም አትስሙ፤ የአሶር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ ከእኔ ጋር ታረቁ፤ ወደ እኔም ውጡ፤ እያንዳንዳችሁም ከወይናችሁና ከበለሳችሁ ብሉ፤ ከጕድጓዳችሁም ውኃ ጠጡ፤ 32ይህም መጥቼ ምድራችሁን ወደምትመስለው ምድር፥ እህልና የወይን ጠጅ፥ እንጀራና ወይን፥ ወይራና ማር ወዳለባት ምድር እስካፈልሳችሁ ድረስ በሕይወት እንድትኖሩ፥ እንዳትሞቱም ነው። ሕዝቅያስም፦ እግዚአብሔር ያድናችኋል ብሎ ያታልላችኋልና አትስሙት። 33በውኑ የአሕዛብ አማልክት አገሮቻቸውን ከአሦር ንጉሥ እጅ አድነዋቸዋልን? 34የኤማትና የአርፋድ አማልክት ወዴት አሉ? የሴፋሩዋይምና የሄና የዒዋም አማልክት ወዴት አሉ? ስማርያን ከእጄ አድነዋታልን? 35እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ከእጄ ያድናት ዘንድ ከሀገሮቹ አማልክት ሁሉ ሀገሩን ከእጄ ያዳነ ማን ነው?”
36ሕዝቡም ዝም አሉ፥ አንዳችም ቃል አልመለሱለትም፤ ንጉሡ እንዳይመልሱለት አዝዞ ነበርና። 37የቤቱ አዛዥ የኬልቅዩ ልጅ ኤልያቄም፥ ጸሓፊው ሳምናስ፥ ታሪክ ጸሓፊውም የአሳፍ ልጅ ዮአስ ልብሳቸውን ቀድደው ወደ ሕዝቅያስ ገቡ፥ የራፋስቂስንም ቃል ነገሩት።
Currently Selected:
መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 18: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ