መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 19
19
ሕዝቅያስ የኢሳይያስን ምክር እንደ ጠየቀ
(ኢሳ. 37፥1-7)
1ንጉሡም ሕዝቅያስ ይህን በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ፥ ማቅም ለበሰ፥ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ገባ። 2የቤቱንም አዛዥ ኤልያቄምን ጸሓፊውንም ሳምናስን የካህናቱንም አለቆች ማቅ ለብሰው ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ነቢዩ ኢሳይያስ ይሄዱ ዘንድ ላካቸው። 3እነርሱም አሉት፥ “ሕዝቅያስ እንዲህ ይላል፦ ይህ ቀን የመከራና የተግሣጽ የዘለፋም ቀን ነው፤ ልጆች የሚወለዱበት ጊዜ ደርሶአል፤ እናትም ለማማጥ ኀይል የላትም። 4ምናልባት በሕያው አምላክ ላይ ይገዳደር ዘንድ ጌታው የአሦር ንጉሥ የላከውን የራፋስቂስን ቃል ሁሉ አምላክህ እግዚአብሔር ይሰማ እንደሆነ፥ አምላክህ እግዚአብሔርም ስለ ሰማው ቃል ይገሥጸው እንደ ሆነ፥ ስለዚህ ለቀረው ቅሬታ ጸልይ።” 5እንዲሁ የንጉሡ የሕዝቅያስ ብላቴኖች ወደ ኢሳይያስ መጡ። 6ኢሳይያስም አላቸው፥ “ለጌታችሁ እንዲህ በሉት፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የአሦር ንጉሥ ብላቴኖች ስለ ተሳደቡት፥ ስለ ሰማኸው ቃል አትፍራ። 7እነሆ፥ በላዩ መንፈስን እሰድዳለሁ፤ ወሬንም ይሰማል፤ ወደ ምድሩም ይመለሳል፤ በምድሩም በሰይፍ እንዲወድቅ አደርገዋለሁ በሉት።”
ሰናክሬም በሕዝቅያስ ላይ እንደ ተገዳደረ
(ኢሳ. 37፥8-20)
8የአሦርም ንጉሥ ከለኪሶ እንደ ራቀ ሰምቶ ነበርና ራፋስቂስ ተመልሶ በሎምና ሲዋጋ አገኘው። 9እርሱም፥ “የኢትዮጵያ ንጉሥ ቲርሐቅ ሊወጋህ መጥቶአል” የሚል ወሬ በሰማ ጊዜ ተመልሶ ወደ ሕዝቅያስ መልእክተኞችን ላከ፤ እንዲህ ሲል፦ 10“ለይሁዳ ንጉሥ ለሕዝቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦ ኢየሩሳሌም በአሦር ንጉሥ እጅ አትሰጥም ብሎ የምትታመንበት አምላክህ አያታልልህ። 11እነሆ፥ የአሦር ነገሥታት በምድር ሁሉ ላይ ያደረጉትን፥ እንዴትስ እንዳጠፉአቸው ሰምተሃል፤ አንተስ ትድናለህን? 12አባቶች ያጠፉአቸውን፥ ጎዛንን፥ ካራንን፥ ራፌስን በታኤሴቴም የነበሩትንም የዔድንን ልጆች፥ የአሕዛብ አማልክት አዳኑአቸውን? 13የሐማት ንጉሥ፥ የአርፋድ ንጉሥ፥ የሴፋሩሄም ከተማ ንጉሥ፥ የኤናና የዓዋ ንጉሥ ወዴት አሉ?”
14ሕዝቅያስም ደብዳቤውን ከመልእክተኞች እጅ ተቀብሎ አነበበው፤ ሕዝቅያስም ወደ እግዚአብሔር ቤት ወጥቶ በእግዚአብሔር ፊት ዘረጋው። 15ሕዝቅያስም ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ጸለየ፥ “በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ የእስራኤል አምላክ አቤቱ፥ አንተ ብቻህን የምድር ነገሥታት ሁሉ አምላክ ነህ፤ ሰማይንና ምድርን ፈጥረሃል ። 16አቤቱ፥ ጆሮህን አዘንብልና ስማ፥ አቤቱ፥ ዐይንህን ክፈትና እይ፤ በሕያው አምላክ ላይ ይገዳደር ዘንድ የላከውን የሰናክሬምን ቃል ስማ። 17አቤቱ፥ በእውነት የአሦር ነገሥት አሕዛብን አጥፍተዋል፤ 18አማልክቶቻቸውንም በእሳት ላይ ጥለዋል፤ የእንጨትና የድንጋይ የሰው እጅ ሥራ ነበሩ እንጂ አማልክት አልነበሩምና፤ ስለዚህ አጥፍተዋቸዋል። 19እንግዲህም አምላካችን አቤቱ፥ የምድር መንግሥታት ሁሉ አንተ ብቻ እግዚአብሔር አምላክ እንደ ሆንህ ያውቁ ዘንድ ከአሦር ንጉሥ እጅ አድነን።”
ኢሳይያስ ለሕዝቅያስ እንደ ላከ
(ኢሳ. 37፥21-38)
20የአሞጽም ልጅ ኢሳይያስ እንዲህ ብሎ ወደ ሕዝቅያስ ላከ፥ “የሠራዊት ጌታ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ስለ አሦር ንጉሥ ስለ ሰናክሬም ወደ እኔ የለመንኸውን ሰምቻለሁ። 21ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ፥ ሰድቦሻልና ንቆሻልምና፥ የኢየሩሳሌም ልጅ፥ በአንቺ ላይ ራሱን ነቅንቋልና እግዚአብሔር በእርሱ ላይ የተናገረው ቃል ይህ ነው፦#ምዕ. 19 ቍ. 21 ላይ ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ ቀላል አድርጋሃለች በንቀትም ስቃብሃለች የኢየሩሳሌም ልጅ በላይህ ራስዋን ነቅንቃለች” ይላል። 22የተገዳደርኸው፥ የሰደብኸውስ ማን ነው? ቃልህንስ ከፍ ከፍ ያደረግኸው፥ ዐይንህንም ወደ ላይ ያነሣኸው በማን ላይ ነው? በእስራኤል ቅዱስ ላይ ነው። 23አንተስ በመልእክተኞችህ እጅ በእግዚአብሔር ላይ ተገዳደርህ፤ እንዲህም አልህ፦ በሰረገላዬ ብዛት ወደ ተራሮች ከፍታ፥ ወደ ሊባኖስ ጥግ እወጣለሁ፤ ረጃጅሞችንም ዝግባዎች የተመረጡትንም ጥዶች እቈርጣለሁ፤ ወደ ሀገሩም ዳርቻና ወደ ቀርሜሎስ ዱር እገባለሁ። 24ዕረፍት አደረግሁ፤ የባዕድ ውኃንም ጠጣሁ፥ የተገደበውንም ውኃ ሁሉ በእግሬ ጫማ አደርቃለሁ።
25“እኔ ጥንቱን እንደ ሠራሁት፥ ቀድሞውንም እንዳደረግሁት አልሰማህምን? አሁንም የተመሸጉትን ከተሞች የፍርስራሽ ክምር እስኪሆኑ ድረስ እንድታፈርስ አደረግሁህ። 26ስለዚህም የሚኖሩባቸው ሰዎች እጆቻቸው ዝለዋል፤ ደንግጠውም አፍረዋል፤ እንደ ምድረ በዳ ሣር፥ እንደ ለምለምም ቡቃያ፥ በሰገነትም ላይ እንዳለ ሣር፥ ሳይሸት ዋግ እንደ መታውም እህል ሆነዋል። 27እኔ ግን መቀመጫህንና መውጫህን መግቢያህንም፥ በእኔም ላይ የተቈጣኸውን ቍጣ ዐውቄአለሁ። 28ቍጣህና ትዕቢትህ ወደ ጆሮዬ ደርሶአልና ስለዚህ ስናጋዬን በአፍንጫህ፥ ልጓሜንም በከንፈርህ አደርጋለሁ፤ በመጣህበት መንገድም እመልስሃለሁ።
29“ይህም ለአንተ ምልክት ይሆንልሃል፤ በዚህ ዓመት የገቦውን፥ በሁለተኛውም ዓመት ከገቦው የበቀለውን ትበላለህ፤ በሦስተኛውም ዓመት ትዘራለህ፤ ታጭድማለህ፥ ወይንም ትተክላለህ፤ ፍሬውንም ትበላለህ። 30የዳነው የይሁዳ ቤት ቅሬታ ሥሩን ወደ ታች ይሰድዳል፤ ወደ ላይም ያፈራል። 31ከኢየሩሳሌም ቅሬታ፥ ከጽዮንም ተራራ የዳነ ይወጣልና፤ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቅንአት ይህን ያደርጋል።” 32እንደዚህ አይደለምን? እግዚአብሔር ስለ አሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፥ “ወደዚች ከተማ አይገባም፥ ፍላጻንም አይወረውርባትም፤ በጋሻም አይመጣባትም፥ የአፈርንም ድልድል አይደለድልባትም። 33በመጣበት መንገድ በዚያ ይመለሳል እንጂ፥ ወደዚህችም ከተማ አይገባም፥ ይላል እግዚአብሔር። 34ስለ እኔም፥ ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊትም ይህችን ከተማ እጋርዳታለሁ።”
35በዚያችም ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ መጣ፤ ከአሦራውያንም ሰፈር መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ገደለ፤ ማለዳም በተነሡ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሁሉ በድኖች ነበሩ። 36የአሦርም ንጉሥ ሰናክሬም ተነሥቶ ሄደ፤ ተመልሶም በነነዌ ተቀመጠ። 37በአምላኩም በሲድራክ ቤት ሲሰግድ ልጆቹ አድራሜሌክና ሶርሶር በሰይፍ ገደሉት፤ ወደ አራራትም ሀገር ኰበለሉ። ልጁም አስራዶን በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 19: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ