መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 20
20
የንጉሥ ሕዝቅያስ መፈወስ
(ኢሳ. 38፥1-8፤21-22፤ 2ዜ.መ. 32፥24-26)
1በዚያም ወራት ሕዝቅያስ ታመመ፤ ለሞትም ደረሰ። ነቢዩም የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደ እርሱ መጥቶ፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ትሞታለህ እንጂ በሕይወት አትኖርምና ቤትህን አስተካክል” አለው። 2ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳው መልሶ እንዲህ ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፦ 3“አቤቱ፥ በፊትህ በእውነትና በፍጹም ልብ እንደ ሄድሁ፥ መልካም ነገርም እንዳደረግሁ አስብ።” ሕዝቅያስም እጅግ አለቀሰ። 4ኢሳይያስም ወደ መካከለኛው አደባባይ ሲደርስ እግዚአብሔር ተናገረው፤ እንዲህም አለው፦ 5“ተመልሰህ የሕዝቤን ንጉሥ ሕዝቅያስን እንዲህ በለው፦ የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጸሎትህን ሰምቻለሁ፥ እንባህንም አይቻለሁ፤ እነሆ፥ እኔ እፈውስሃለሁ፤ እስከ ሦስት ቀንም ድረስ ወደ እግዚአብሔር ቤት ትወጣለህ። 6በዕድሜህም ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት እጨምራለሁ፤ አንተንና ይህችን ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ እታደጋለሁ፤ ስለ እኔ፥ ስለ ባሪያዬም ስለ ዳዊት ይህችን ከተማ አጋርዳታለሁ።” 7ኢሳይያስም አለው፥ “የበለስ ጥፍጥፍ አምጥተህ በእባጭህ ላይ አድርግ ትፈወሳለህም።”
8ሕዝቅያስም ኢሳይያስን፥ “እግዚአብሔር እንዲፈውሰኝ፥ እኔስ እስከ ሦስት ቀን ድረስ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንድወጣ ምልክቱ ምንድን ነው?” አለው። 9ኢሳይያስም፥ “እግዚአብሔር የተናገረውን ነገር እንዲፈጽመው ከእግዚአብሔር ዘንድ ምልክቱ ይህ ይሆንልሃል፤ ጥላው ዐሥር ደረጃ ወደ ፊት ይሂድን? ወይስ ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላው ይመለስ?” አለ። 10ሕዝቅያስም ኢሳይያስን፥ “ጥላው ዐሥር ደረጃ ቢጨምር ቀላል ነገር ነው፤ እንዲህ አይሁን፤ ነገር ግን ጥላው ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ ይመለሰ” አለው። 11ነቢዩም ኢሳይያስ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፤ ጥላውም ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ ተመለሰ።
ከባቢሎን የመጡ መልእክተኞች
(ኢሳ. 39፥1-8)
12በዚያም ወራት የባቢሎን ንጉሥ መሮዳህ ሕዝቅያስ እንደ ታመመ ሰምቶ ነበርና የበልዳንን ልጅ በልዳንን#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “... የባቢሎን ንጉሥ የባልዳን ልጅ መሮዳህ ባልዳን ሕዝቅያስ እንደ ታመመ ሰምቶ ነበርና ደብዳቤና እጅ መንሻ ወደ ሕዝቅያስ ላከ” ይላል። ከመጻሕፍትና እጅ መንሻ ጋር ወደ ሕዝቅያስ ላከ። 13ሕዝቅያስም በእነርሱ ደስ አለው፤ ግምጃ ቤቱንም ሁሉ፥ ብሩንና ወርቁንም፥ ሽቱውንና የከበረውንም ዘይት፥ መሣሪያም ያለበትን ቤት በቤተ መዛግብቱም የተገኘውን ሁሉ አሳያቸው፤ በቤቱና በግዛቱ ሁሉ ካለው ሕዝቅያስ ያላሳያቸው የለም። 14ነቢዩ ኢሳይያስም ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ መጥቶ፥ “እነዚህ ሰዎች ምን አሉ? ከወዴትስ ወደ አንተ መጡ?” አለው። ሕዝቅያስም፥ “ከሩቅ ሀገር ከባቢሎን ወደ እኔ መጡ” አለው። 15እርሱም፥ “ምን አዩ?” አለው ሕዝቅያስም፥ “በቤቴ ያለውን ሁሉ አይተዋል፤ በቤተ መዛግብቴም ካለው ያላሳየኋቸው የለም” አለው።
16ኢሳይያስም ሕዝቅያስን አለው፥ “የእግዚአብሔርን ቃል ስማ። 17እነሆ፥ በቤትህ ያለው ሁሉ፥ አባቶችህም እስከ ዛሬ ያከማቹት ሁሉ ወደ ባቢሎን የሚፈልስበት ወራት ይመጣል፤ ምንም አይቀርም፥ ይላል እግዚአብሔር። 18ከአንተም ከሚወጡት ከምትወልዳቸው ልጆችህ ማርከው ይወስዳሉ፤ በባቢሎንም ንጉሥ ቤት ውስጥ ጃንደረቦች ይሆናሉ።” 19ሕዝቅያስም ኢሳይያስን፥ “እግዚአብሔር የተናገረው ቃል መልካም ነው። ደግሞም በዘመኔ ሰላም ይሁን” አለው። 20የቀረውም የሕዝቅያስ ነገር፥ ኀይሉም ሁሉ፥ ኵሬውንና መስኖውን እንደ ሠራ፥ ውኃውንም ወደ ከተማዪቱ እንዳመጣ፥ እነሆ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 21ሕዝቅያስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊት ከተማም ቀበሩት። ልጁ ምናሴም በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 20: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ