መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 21
21
የምናሴ ዘመነ መንግሥት
(2ዜ.መ. 33፥1-20)
1ምናሴም በነገሠ ጊዜ ዐሥራ ሁለት ዓመት ሆኖት ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ኀምሳ አምስት ዓመት ነገሠ፤ የእናቱም ስም ሐፍሴባ ነበረ። 2እግዚአብሔርም ከእስራኤል ልጆች ፊት እንዳራቃቸው እንደ አሕዛብ ርኵሰት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገርን አደረገ። 3አባቱም ሕዝቅያስ ያፈረሳቸውን የኮረብታውን መስገጃዎች መልሶ ሠራ፤ የእስራኤልም ንጉሥ አክዓብ እንዳደረገው ለበዓል መሠዊያን ሠራ፤ የማምለኪያ ዐፀድንም ተከለ፤ ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ ሰገደ አመለካቸውም። 4እግዚአብሔርም፥ “ስሜን በኢየሩሳሌም አኖራለሁ” ባለው በእግዚአብሔር ቤት መሠዊያን ሠራ። 5በእግዚአብሔርም ቤት በሁለቱ ወለሎች ላይ ለሰማይ ሠራዊት ሁሉ መሠዊያን ሠራ። 6ልጁንም በእሳት ሠዋ፤ ሞራ ገላጭም ሆነ፤ አስማትም አደረገ፤ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችንም ሰበሰበ፤ በእግዚአብሔርም ፊት እጅግ ክፉ ነገር አደረገ፤ ኣስቈጣውም። 7እግዚአብሔርም ለዳዊትና ለልጁ ለሰሎሞን፥ “በዚህ ቤት ከእስራኤልም ነገድ ሁሉ በመረጥኋት በኢየሩሳሌም ስሜን ለዘለዓለም አኖራለሁ፤ 8ያዘዝኋቸውንም ሁሉ ፥ ባሪያዬም ሙሴ ያዘዛቸውን ሕግ ሁሉ ቢያደርጉ ቢጠብቁም ለአባቶቻቸው ከሰጠኋት ምድር የእስራኤልን እግር እንደገና አላንቀሳቅስም” ባለው ቤት የሠራውን የማምለኪያ ዐፀድ የተቀረጸውንም ምስል አቆመ። 9ነገር ግን አልሰሙም፤ እግዚአብሔርም ከእስራኤል ልጆች ፊት ካጠፋቸው ከአሕዛብ ይልቅ በእግዚአብሔር ዐይኖች ፊት ክፉ ይሠሩ ዘንድ ምናሴ አሳታቸው።
10እግዚአብሔርም በባሪያዎቹ በነቢያት ቃል እንዲህ ሲል ተናገረ፦ 11“የይሁዳ ንጉሥ ምናሴ ከእርሱ በፊት የነበሩ አሞራውያን ከሠሩት ሁሉ ይልቅ ይህን ክፉ ርኵሰት አድርጎአልና፥ ይሁዳንም ደግሞ በጣዖታቱ አስቶአልና፥ 12ስለዚህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ የሚሰማውን ሁሉ ሁለቱ ጆሮቹን ጭው የሚያደርግ ክፉ ነገርን በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ አመጣለሁ። 13የሰማርያንም ገመድ የአክዓብንም ቤት ቱንቢ በኢየሩሳሌም ላይ እዘረጋለሁ፤ የሽቱ ዕቃ እንዲወለወል ኢየሩሳሌምን ወልውዬ በፊቷ እገለብጣታለሁ። 14የሕዝቡንም ቅሬታ እጥላለሁ፤ በጠላቶቻቸውም እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ ለጠላቶቻቸውም ሁሉ ምርኮና ብዝበዛ ይሆናሉ፤ 15አባቶቻቸውን ከግብፅ ከአወጣኋቸው ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በፊቴ ክፉ ሠርተዋልና፥ አስቈጥተውኝማልና።”
16ደግሞም ምናሴ በእግዚአብሔር ዐይኖች ፊት ክፉ ይሠራ ዘንድ ይሁዳን ካሳተበት ኀጢአት ሌላ ከዳር እስከ ዳር ኢየሩሳሌምን እስኪሞላት ድረስ እጅግ ብዙ ንጹሕ ደምን አፈሰሰ። 17የምናሴም የቀረው ነገርና የሠራው ሥራ ሁሉ፥ ያደረገውም ኀጢአት፥ እነሆ፥ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 18ምናሴም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በቤቱም አጠገብ ባለው በዖዛ አትክልት ቦታ ተቀበረ፤ ልጁም አሞጽ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
የአሞጽ ዘመነ መንግሥት
(2ዜ.መ. 33፥21-25)
19አሞጽም#ዕብ. “አሞን” ይላል። በነገሠ ጊዜ ሃያ ሁለት ዓመት ሆኖት ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሁለት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የዮጥባ ሰው የሐሩስ ልጅ ሚሱላም ነበረች። 20አባቱ ምናሴም እንዳደረገ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሠራ። 21አባቱም በሄደበት መንገድ ሁሉ ሄደ፤ አባቱም ያመለካቸውን ጣዖታት አመለከ፥ ሰገደላቸውም። 22የአባቶቹንም አምላክ እግዚአብሔርን ተወ፥ በእግዚአብሔርም መንገድ አልሄደም። 23የአሞጽም ብላቴኖች አሴሩበት፤ ንጉሡንም በቤቱ ውስጥ ገደሉት። 24የሀገሩ ሕዝብ ግን በንጉሡ በአሞጽ ላይ ያሴሩትን ሁሉ ገደሉ፤ የሀገሩም ሕዝብ ልጁን ኢዮስያስን በእርሱ ፋንታ አነገሡት። 25የአሞጽም የቀረው ነገርና የሠራው ሥራ ሁሉ፥ እነሆ፥ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 26በዖዛም የአትክልት ቦታ ባለው መቃብሩ ቀበሩት፤ ልጁም ኢዮስያስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 21: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ