የእግዚአብሔርም ቃል ስለ ባኦስ እንዲህ ብሎ ወደ አናኒ ልጅ ወደ ኢዩ መጣ። “እኔ ከመሬት አንሥቼ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ አለቃ አድርጌሃለሁ፤ አንተ ግን በከንቱ ጣዖታቸው ያስቈጡኝ ዘንድ ሕዝቤን እስራኤልን በአሳታቸው በኢዮርብዓም መንገድ ሄድህ፤ ስለዚህም፥ እነሆ፥ ባኦስንና ቤቱን ፈጽሜ አጠፋለሁ፤ ቤትህንም እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት አደርጋለሁ። ከባኦስም ወገን በከተማዪቱ ውስጥ የሚሞተውን ውሾች ይበሉታል፤ በሜዳውም የሚሞተውን የሰማይ ወፎች ይበሉታል።” የቀረውም የባኦስ ነገር፥ የሠራውም ሁሉ፥ ኀይሉም ሁሉ፥ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ ነው። ባኦስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በቴርሳም ተቀበረ፤ ልጁም ኤላ በአሳ በሃያ ስድስተኛው ዓመተ መንግሥት በፋንታው ነገሠ። በእጁም ሥራ ያስቈጣው ዘንድ፥ እንደ ኢዮርብዓም ቤት በእግዚአብሔር ፊት ስላደረገው ክፋት ሁሉ እርሱንም ስለ ገደለው፥ የእግዚአብሔር ቃል በባኦስና በቤቱ ላይ ወደ አናኒ ልጅ ወደ ነቢዩ ኢዩ መጣ። የባኦስም ልጅ ኤላ በእስራኤል ላይ በቴርሳ ሁለት ዓመት ነገሠ። የእኩሌቶቹ ፈረሶች አለቃ ዘምሪም አሽከሮቹን ሁሉ ሰብስቦ ዐመፀ፤ ኤላም በቴርሳ ነበረ፤ በቴርሳም በነበረው በመጋቢው በአሳ ቤት ይሰክር ነበር። በይሁዳም ንጉሥ በአሳ በሃያ ሰባተኛው ዓመት ዘምሪ ገብቶ ወጋና ገደለው፤ በፋንታውም ነገሠ። ከነገሠና በዙፋኑም ከተቀመጠ በኋላ፥ የባኦስን ቤት ሁሉ አጠፋ፤ አንድ ወንድ እንኳ አላስቀረለትም። በነቢዩ በኢዩ አፍ በባኦስ ቤት ላይ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል፥ ባኦስና ልጁ ኤላ ስለ ሠሩት ኀጢአት ሁሉ፥ በርኵሰታቸው የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ያስቈጡት ዘንድ እስራኤልን ስለ አሳቱበት ኀጢአት፥ ዘምሪ የባኦስን ቤት ሁሉ እንዲሁ አጠፋ። የቀረውም የኤላ ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ ነው። በይሁዳም ንጉሥ በአሳ በሃያ ዘጠነኛው ዓመት ዘምሪ በቴርሳ ሰባት ቀን ነገሠ። የእስራኤል ሠራዊት ግን በፍልስጥኤም ሀገር በገባቶን ሰፍረው ነበር። በሰፈር ያሉ ሕዝቡም “ዘምሪ ከድቶ ኤላን ገደለው፥ በፋንታውም ነገሠ” ሲሉ ሰሙ። እስራኤልም ሁሉ በዚያ ቀን በሰፈሩ ውስጥ የሠራዊቱን አለቃ ዘንበሪን አነገሡ። ዘንበሪም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ከገባቶን ወጥተው ቴርሳን ከበቡ። በእርስዋም ተቀመጡ። ዘምሪም ከተማዪቱ እንደ ተያዘች ባየ ጊዜ ወደ ንጉሡ ቤት ግንብ ውስጥ ገባ፤ የንጉሡንም ቤት በራሱ ላይ በእሳት አቃጠለ፤ ሞተም። ስላደረገውም ኀጢአት፥ እስራኤልንም ስላሳተበት ኀጢአት፥ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አድርጎአልና፥ በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓምም መንገድ ሄዶአልና ሞተ። የቀረውም የዘምሪ ነገር፥ ያደረገውም ዐመፅ፥ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ ነው።
መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 16 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 16:1-20
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች