አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 16:1-20

አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 16:1-20 አማ05

የሐናኒ ልጅ በሆነው በነቢዩ ኢዩ አማካይነት እግዚአብሔር ስለ ባዕሻ የተናገረው ቃል ይህ ነው፦ “እኔ ግን ከትቢያ አንሥቼ የሕዝቤ የእስራኤል መሪ አደረግሁህ፤ ታዲያ አንተ እንደ ኢዮርብዓም ኃጢአት ሠራህ፤ ሕዝቤንም ወደ ኃጢአት መራህ፤ የኃጢአታቸውም ብዛት የእኔን ቊጣ አነሣሥቶአል፤ ስለዚህም ኢዮርብዓምን እንዳስወገድኩ አንተንና ቤተሰብህንም አስወግዳለሁ። በከተማይቱ ውስጥ የሚሞተውን ማንኛውንም የቤተሰብህን አባል ውሾች ይበሉታል፤ በየገጠሩም ሜዳ ላይ የሚሞተውን አሞራዎች ይበሉታል።” ባዕሻ ያደረገው ሌላው ነገርና የጀግንነት ሥራዎቹም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፤ ባዕሻ ሞተ፤ በቲርጻም ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ኤላ ነገሠ። እግዚአብሔር በነቢዩ ኢዩ አማካይነት በባዕሻና በቤተሰቡ ላይ ያን የትንቢት ቃል የተናገረበት ምክንያት፥ ባዕሻ በፈጸመው ኃጢአት እግዚአብሔርን ስላሳዘነ ነበር፤ ባዕሻ እግዚአብሔርን ያስቈጣውም ከእርሱ ፊት የነበረው ንጉሥ ባደረገው ዐይነት ስለ ሠራው ክፉ ነገር ብቻ ሳይሆን የኢዮርብዓምንም ቤተሰብ ሁሉ በመግደሉ ጭምር ነው። አሳ በይሁዳ በነገሠ በሃያ ስድስተኛው ዓመት የባዕሻ ልጅ ኤላ የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፤ መኖሪያውንም በቲርጻ አድርጎ ሁለት ዓመት ገዛ። የሠረገላዎቹ እኩሌታ ኀላፊ የሆነ ዚምሪ ተብሎ የሚጠራ ከጦር መኰንኖቹ አንዱ በንጉሡ ላይ ዐደመ፤ አንድ ቀን ኤላ በቲርጻ ከተማ የቤተ መንግሥቱ ኀላፊ በሆነው አርጻ ተብሎ በሚጠራው ባለሟሉ ቤት ብዙ መጠጥ ጠጥቶ ሰክሮ ነበር። በዚህን ጊዜ ዚምሪ ወደዚያ ቤት ሰተት ብሎ ገብቶ ኤላን ገደለው፤ እርሱም በኤላ እግር ተተክቶ ነገሠ፤ ይህም የሆነው የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሃያ ሰባተኛው ዓመት ነበር። ዚምሪ እንደ ነገሠ ወዲያውኑ የባዕሻ ቤተሰብ አባላት የሆኑትን በሙሉ ገደለ፤ የባዕሻ ዘመድና ወዳጅ የሆነውን ወንድ ሁሉ በሞት ቀጣ። በዚህም ዐይነት እግዚአብሔር በነቢዩ ኢዩ አማካይነት በባዕሻ ላይ ባናገረው ትንቢት መሠረት ዚምሪ የባዕሻን ቤተሰብ በሙሉ ፈጀ። ይህም የሆነበት ምክንያት ባዕሻና ልጁ ኤላ ጣዖት በማምለካቸውና የእስራኤልን ሕዝብ ወደ ኃጢአት በመምራታቸው የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ቊጣ በማነሣሣታቸው ነው። ኤላ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። አሳ በይሁዳ በነገሠ በሃያ ሰባተኛው ዓመት ዚምሪ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ መኖሪያውንም በቲርጻ አድርጎ በእስራኤል ላይ ሰባት ቀን ብቻ ነገሠ፤ በዚያን ጊዜ የእስራኤል ወታደሮች በፍልስጥኤም የምትገኘውን የጊበቶንን ከተማ ከበው ነበር። ዚምሪ ዐምፆ ንጉሡን መግደሉን በሰሙ ጊዜ በዚያው እንዳሉ ወዲያውኑ የጦር አዛዣቸው የነበረውን ዖምሪን አነገሡ። ዖምሪና ወታደሮቹ የጊበቶንን ከበባ አቆሙ፤ ከዚያም ገሥግሠው ሄደው ቲርጻን ከበቡ፤ ዚምሪ ከተማይቱ እንደ ተያዘች ባየ ጊዜ በቤተ መንግሥቱ ውስጠኛ ክፍል ወዳለው ምሽግ ውስጥ ገብቶ በቤተ መንግሥቱ ላይ እሳት ለቀቀበት፤ እርሱም በእሳት ነበልባል ተቃጥሎ ሞተ። ይህ የሆነበት ምክንያት በሠራው ኃጢአት እግዚአብሔርን በማሳዘኑ ነው፤ እርሱ ራሱ በሠራው ኃጢአትና እስራኤልንም ወደ ኃጢአት በመምራቱ ምክንያት ከእርሱ በፊት እንደ ነበረው እንደ ኢዮርብዓም እግዚአብሔርን አስቈጥቶአል። ዚምሪ የሠራው ሌላው ነገር ሁሉና ያደረገውም ሤራ ጭምር በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል።