አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 16
16
1የሐናኒ ልጅ በሆነው በነቢዩ ኢዩ አማካይነት እግዚአብሔር ስለ ባዕሻ የተናገረው ቃል ይህ ነው፦ 2“እኔ ግን ከትቢያ አንሥቼ የሕዝቤ የእስራኤል መሪ አደረግሁህ፤ ታዲያ አንተ እንደ ኢዮርብዓም ኃጢአት ሠራህ፤ ሕዝቤንም ወደ ኃጢአት መራህ፤ የኃጢአታቸውም ብዛት የእኔን ቊጣ አነሣሥቶአል፤ 3ስለዚህም ኢዮርብዓምን እንዳስወገድኩ አንተንና ቤተሰብህንም አስወግዳለሁ። 4በከተማይቱ ውስጥ የሚሞተውን ማንኛውንም የቤተሰብህን አባል ውሾች ይበሉታል፤ በየገጠሩም ሜዳ ላይ የሚሞተውን አሞራዎች ይበሉታል።”
5ባዕሻ ያደረገው ሌላው ነገርና የጀግንነት ሥራዎቹም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፤ 6ባዕሻ ሞተ፤ በቲርጻም ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ኤላ ነገሠ።
7እግዚአብሔር በነቢዩ ኢዩ አማካይነት በባዕሻና በቤተሰቡ ላይ ያን የትንቢት ቃል የተናገረበት ምክንያት፥ ባዕሻ በፈጸመው ኃጢአት እግዚአብሔርን ስላሳዘነ ነበር፤ ባዕሻ እግዚአብሔርን ያስቈጣውም ከእርሱ ፊት የነበረው ንጉሥ ባደረገው ዐይነት ስለ ሠራው ክፉ ነገር ብቻ ሳይሆን የኢዮርብዓምንም ቤተሰብ ሁሉ በመግደሉ ጭምር ነው።
የእስራኤል ንጉሥ ኤላ
8አሳ በይሁዳ በነገሠ በሃያ ስድስተኛው ዓመት የባዕሻ ልጅ ኤላ የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፤ መኖሪያውንም በቲርጻ አድርጎ ሁለት ዓመት ገዛ። 9የሠረገላዎቹ እኩሌታ ኀላፊ የሆነ ዚምሪ ተብሎ የሚጠራ ከጦር መኰንኖቹ አንዱ በንጉሡ ላይ ዐደመ፤ አንድ ቀን ኤላ በቲርጻ ከተማ የቤተ መንግሥቱ ኀላፊ በሆነው አርጻ ተብሎ በሚጠራው ባለሟሉ ቤት ብዙ መጠጥ ጠጥቶ ሰክሮ ነበር። 10በዚህን ጊዜ ዚምሪ ወደዚያ ቤት ሰተት ብሎ ገብቶ ኤላን ገደለው፤ እርሱም በኤላ እግር ተተክቶ ነገሠ፤ ይህም የሆነው የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሃያ ሰባተኛው ዓመት ነበር።
11ዚምሪ እንደ ነገሠ ወዲያውኑ የባዕሻ ቤተሰብ አባላት የሆኑትን በሙሉ ገደለ፤ የባዕሻ ዘመድና ወዳጅ የሆነውን ወንድ ሁሉ በሞት ቀጣ። 12በዚህም ዐይነት እግዚአብሔር በነቢዩ ኢዩ አማካይነት በባዕሻ ላይ ባናገረው ትንቢት መሠረት ዚምሪ የባዕሻን ቤተሰብ በሙሉ ፈጀ። 13ይህም የሆነበት ምክንያት ባዕሻና ልጁ ኤላ ጣዖት በማምለካቸውና የእስራኤልን ሕዝብ ወደ ኃጢአት በመምራታቸው የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ቊጣ በማነሣሣታቸው ነው። 14ኤላ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል።
የእስራኤል ንጉሥ ዚምሪ
15አሳ በይሁዳ በነገሠ በሃያ ሰባተኛው ዓመት ዚምሪ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ መኖሪያውንም በቲርጻ አድርጎ በእስራኤል ላይ ሰባት ቀን ብቻ ነገሠ፤ በዚያን ጊዜ የእስራኤል ወታደሮች በፍልስጥኤም የምትገኘውን የጊበቶንን ከተማ ከበው ነበር። 16ዚምሪ ዐምፆ ንጉሡን መግደሉን በሰሙ ጊዜ በዚያው እንዳሉ ወዲያውኑ የጦር አዛዣቸው የነበረውን ዖምሪን አነገሡ። 17ዖምሪና ወታደሮቹ የጊበቶንን ከበባ አቆሙ፤ ከዚያም ገሥግሠው ሄደው ቲርጻን ከበቡ፤ 18ዚምሪ ከተማይቱ እንደ ተያዘች ባየ ጊዜ በቤተ መንግሥቱ ውስጠኛ ክፍል ወዳለው ምሽግ ውስጥ ገብቶ በቤተ መንግሥቱ ላይ እሳት ለቀቀበት፤ እርሱም በእሳት ነበልባል ተቃጥሎ ሞተ። 19ይህ የሆነበት ምክንያት በሠራው ኃጢአት እግዚአብሔርን በማሳዘኑ ነው፤ እርሱ ራሱ በሠራው ኃጢአትና እስራኤልንም ወደ ኃጢአት በመምራቱ ምክንያት ከእርሱ በፊት እንደ ነበረው እንደ ኢዮርብዓም እግዚአብሔርን አስቈጥቶአል። 20ዚምሪ የሠራው ሌላው ነገር ሁሉና ያደረገውም ሤራ ጭምር በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል።
የእስራኤል ንጉሥ ዖምሪ
21በዚያን ጊዜ የእስራኤል ሕዝብ ወገን በመለየት ከሁለት ተከፍለው ነበር፤ ከዚህም የተነሣ አንደኛው ክፍል ቲብኒ ተብሎ የሚጠራውን የጊናትን ልጅ ለማንገሥ ሲፈልግ፥ ሌላው ክፍል ደግሞ ዖምሪን ለመደገፍ ይሻ ነበር። 22በመጨረሻም የዖምሪ ደጋፊዎች አሸነፉ፤ ስለዚህም ቲብኒ ተገደለ፤ ዖምሪም ንጉሥ ሆነ፤ 23በዚህ ዐይነት አሳ በይሁዳ በነገሠ በሠላሳ አንደኛው ዓመት ዖምሪ በእስራኤል ላይ ነግሦ ዐሥራ ሁለት ዓመት ገዛ፤ የመጀመሪያዎቹን ስድስት ዓመቶች የገዛውም መኖሪያውን በቲርጻ አድርጎ ነበር። 24ከዚያም በኋላ ሼሜር ተብሎ ከሚጠራው ሰው የሰማርያን ኰረብታ በስድስት ሺህ ጥሬ ብር ገዛ፤ ዖምሪ ኰረብታውን ከመሸገ በኋላ ከተማ ቈረቈረ፤ ከተማይቱንም ቀድሞ የኮረብታው ባለንብረት በሆነው በሼሜር ስም “ሰማርያ” ብሎ ሰየማት።
25ዖምሪ ከእርሱ በፊት ከነበሩት ነገሥታት ይበልጥ የከፋ ኃጢአት በመሥራቱ እግዚአብሔርን አሳዘነ። 26እርሱ ራሱ በሠራው ኃጢአትና፥ እንዲሁም እስራኤልን ወደ ኃጢአትና ወደ ዋጋቢስ ጣዖት አምልኮ በመምራቱ ከእርሱ በፊት እንደ ነበረው እንደ ኢዮርብዓም የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ቊጣ አነሣሣ። 27ዖምሪ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉና ያከናወነውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። 28ዖምሪ ሞተ፤ በሰማርያም ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ አክዓብ ነገሠ።
የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ
29አሳ በይሁዳ በነገሠ በሠላሳ ስምንተኛው ዓመት የዖምሪ ልጅ አክዓብ የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፤ እርሱም መኖሪያውን በሰማርያ አድርጎ ኻያ ሁለት ዓመት ገዛ። 30አክዓብ ከእርሱ በፊት ከነበሩት ነገሥታት ሁሉ ይበልጥ የከፋ ኃጢአት በመሥራቱ እግዚአብሔርን አሳዘነ፤ 31አክዓብ፥ ንጉሥ ኢዮርብዓም የሠራውን ኃጢአት እንደ ቀላል ነገር አድርጎ በመቊጠር እርሱም ራሱ ያንኑ ኃጢአት ሠራ፤ ከዚህም ሁሉ አልፎ የሲዶና ንጉሥ የኤትበዓል ልጅ የሆነችውን አረማዊቷን ኤልዛቤልን አገባ፤ ባዓል ተብሎ የሚጠራውንም ጣዖት አመለከ፤ ሰገደለትም፤ 32በሰማርያም ለባዓል ቤተ መቅደስ አሳንጾ መሠዊያ ሠራለት፤ 33አሼራ ተብላ የምትጠራውንም የሴት አምላክ ምስል አቆመ፤ ከእርሱ በፊት ከነበሩትም የእስራኤል ነገሥታት ሁሉ ይበልጥ የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ቊጣ የሚያነሣሣ ኃጢአት ሠራ። 34በአክዓብ ዘመነ መንግሥት ሒኤል ተብሎ የሚጠራ የቤትኤል ተወላጅ ኢያሪኮን መልሶ ሠራ፤ እግዚአብሔር በነዌ ልጅ በኢያሱ አማካይነት አስቀድሞ በተናገረው ቃል መሠረት ሒኤል የኢያሪኮን የመሠረት ድንጋይ በሚያኖርበት ጊዜ የበኲር ልጁ አቢራም ሞተበት፤ የቅጽርዋንም በሮች በሚሠራበት ጊዜ ታናሹ ልጁ ሠጉብ ሞተ።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 16: አማ05
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997