የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 15

15
የይሁዳ ንጉሥ አቢያ
(2ዜ.መ. 13፥1—14፥1)
1ኢዮርብዓም በእስራኤል ላይ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት አቢያ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤ 2መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ሦስት ዓመት ነገሠ፤ እናቱ ማዕካ ተብላ የምትጠራ የአቤሴሎም ልጅ ነበረች፤ 3አቢያም፥ እንደ ታላቁ አያቱ እንደ ዳዊት በእግዚአብሔር ዘንድ ፍጹም ታማኝ ሆኖ በመገኘት ፈንታ፥ አባቱ ሮብዓም ይፈጽመው የነበረውን ኃጢአት ሁሉ መሥራቱን ቀጠለ። 4ይሁን እንጂ ከእርሱ በኋላ በኢየሩሳሌም እንዲነግሥና ኢየሩሳሌምንም በሰላም እንዲጠብቅ አምላኩ እግዚአብሔር ስለ ዳዊት ሲል ለአቢያ አንድ ወንድ ልጅ ሰጠው፥ #1ነገ. 11፥36። 5እግዚአብሔር ይህን ያደረገበት ምክንያት ዳዊት በሒታዊው ኦርዮን ላይ ከፈጸመው ኃጢአት በቀር እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ነገር በማድረጉና ትእዛዙንም በብርቱ ጥንቃቄ በመጠበቁ ነው። #2ሳሙ. 11፥1-27። 6በአቢያ ዘመነ መንግሥት ሁሉ፥ በሮብዓምና ኢዮርብዓም ዘመን ተጀምሮ የነበረው ጦር ሳያቋርጥ ቀጠለ፤ 7አቢያ ያደረገውም ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። 8ከዚህ በኋላ አቢያ ሞተ፤ በዳዊት ከተማም ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ልጁ አሳ ተተክቶ ነገሠ።
የይሁዳ ንጉሥ አሳ
(2ዜ.መ. 15፥16—16፥6)
9ኢዮርብዓም በእስራኤል ላይ በነገሠ በሃያኛው ዓመት አሳ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤ 10መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ አርባ አንድ ዓመት ገዛ፤ አያቱም ማዕካ ተብላ የምትጠራ የአቤሴሎም ልጅ ነበረች። 11አሳ፥ የቀድሞ አያቱ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠራ። 12ንጉሥ አሳ በአሕዛብ የማምለኪያ ቦታዎች የቤተ ጣዖትን አመንዝራዎችን ሁሉ ከሀገሪቱ አስወገደ፤ ከእርሱም በፊት የነበሩ ነገሥታት የሠሩአቸውን ጣዖቶችንም ሁሉ ነቃቅሎ ጣለ። 13አያቱ ማዕካ አሼራ ተብላ የምትጠራውን የሴት አምላክ አጸያፊ ጣዖት ስለ ሠራች ከእቴጌነት ሻራት፤ የሠራችውንም ጣዖት ሰባብሮ በቄድሮን ሸለቆ ውስጥ በእሳት አቃጠለው። 14አሳ በኰረብቶች ላይ የሚገኙ የአሕዛብ የማምለኪያ ቦታዎችን በሙሉ ባያስወግድም እንኳ እስከ ዕድሜው ፍጻሜ ድረስ ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆኖ ኖረ። 15አባቱ ለእግዚአብሔር የተለዩ እንዲሆኑ ያደረጋቸውንና እርሱም ራሱ ከወርቅና ከብር አሠርቶ ለመንፈሳዊ አገልግሎት ብቻ እንዲውሉ ያደረጋቸውን ንዋያተ ቅድሳት ሁሉ በቤተ መቅደስ አኖረ።
16የይሁዳ ንጉሥ አሳና የእስራኤል ንጉሥ ባዕሻ በሥልጣን በነበሩበት ዘመን ሁሉ በማያቋርጥ የእርስበርስ ጦርነት ላይ ነበሩ። 17ባዕሻ ይሁዳን በመውረር ራማን ምሽግ አድርጎ መሥራት ጀመረ፤ ይህንንም ያደረገው ወደ ይሁዳ ማንም እንዳይገባና ከዚያም ማንም እንዳይወጣ ለመከልከል ነው። 18በዚህም ምክንያት ንጉሥ አሳ በቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥቱ የተረፈውን ወርቅና ብር ሁሉ በማውጣት በባለሟሎቹ እጅ፥ በደማስቆ ከተማ ለነበረው የጣብሪሞን ልጅ፥ የሔዝዮን የልጅ ልጅ ለሆነው ለሶርያ ንጉሥ ቤንሀዳድ ስጦታ አድርጎ ላከለት፤ ከስጦታውም ጋር እንዲህ የሚል መልእክት ነበረ፤ 19“የእኔ አባትና የአንተ አባት ያደርጉት በነበረው ዐይነት በመካከላችን የስምምነት ውል እናድርግ፤ ይህም ብርና ወርቅ ለአንተ የላክኹልህ ገጸ በረከት ነው፤ እንግዲህ የእስራኤል ንጉሥ ባዕሻ ወታደሮቹን ከግዛቴ ያስወጣ ዘንድ እንድትረዳኝ ቀደም ሲል ከእርሱ ጋር ያደረግኸውን የስምምነት ውል አሁን እንድታፈርሰው እለምንሃለሁ።”
20ንጉሥ ቤንሀዳድም አሳ ባቀረበው ሐሳብ ተስማምቶ የጦር አዛዦቹንና ሠራዊቱን በመላክ በእስራኤል ከተሞች ላይ አደጋ እንዲጥሉ አደረገ፤ እነርሱም ዒዮን፥ ዳን፥ አቤልቤትማዕካና የገሊላ ባሕር ተብለው የሚጠሩትን ከተሞች በገሊላ ባሕር አጠገብ የሚገኘውን አገርና የንፍታሌምን ግዛት ሁሉ ያዙ። 21ንጉሥ ባዕሻ የሆነውን ነገር ሁሉ በሰማ ጊዜ ራማን የመመሸጉ ሥራ እንዲቆም አድርጎ ወደ ቲርጻ ሄደ።
22ከዚህም በኋላ ንጉሥ አሳ፥ ባዕሻ ራማን ለመመሸግ አከማችቶት የነበረውን ድንጋይና እንጨት ከዚያ ለማንሣት እንዲረዳው ሕዝቡ አንድም ሳይቀር እንዲመጣ ወደ ይሁዳ ግዛቶች ሁሉ ትእዛዝ አስተላለፈ፤ ንጉሥ አሳ ከዚያ የተገኘውን ድንጋይና እንጨት ሁሉ ወስዶ ምጽጳንና በብንያም ግዛት ውስጥ የምትገኘውን የጌባዕን ከተማ ምሽግ አድርጎ ሠራበት።
23ንጉሥ አሳ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ፥ የጀግንነት ሥራውና የመሸጋቸውም ከተሞች ጭምር በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፤ ንጉሥ አሳ በዕድሜ በሸመገለ ጊዜ ግን ከእግሩ ሕመም የተነሣ ሽባ ሆኖ ነበር። 24እርሱም ሞተ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘው በነገሥታት መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ኢዮሣፍጥ ነገሠ።
የእስራኤል ንጉሥ ናዳብ
25አሳ በይሁዳ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት የኢዮርብዓም ልጅ ናዳብ የእስራኤል ንጉሥ ሆኖ ሁለት ዓመት ገዛ፤ 26ከእርሱም በፊት እንደ ነበረው እንደ አባቱ ኃጢአት በመሥራት የእስራኤልን ሕዝብ ወደ ኃጢአት መራ።
27የይሳኮር ነገድ የሆነው የአኪያ ልጅ ባዕሻ በናዳብ ላይ ዐምፆ ገደለው፤ በዚያም ጊዜ ናዳብና ሠራዊቱ በፍልስጥኤም ግዛት የምትገኘውን የጊበቶንን ከተማ በመክበብ ላይ ነበሩ። 28ይህም የሆነው የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ነው፤ በዚህ ዐይነት ባዕሻ በናዳብ እግር ተተክቶ የእስራኤል ንጉሥ ሆነ። 29ወዲያውኑም የኢዮርብዓምን ቤተሰብ አባላት ሁሉ መፍጀት ጀመረ፤ እግዚአብሔር የሴሎ ተወላጅ በሆነው በአገልጋዩ በነቢዩ አኪያ አማካይነት በተናገረው ቃል መሠረት የኢዮርብዓም ቤተሰብ በሙሉ ተገደሉ፤ በሕይወት የተረፈ አንድም አልነበረም። #1ነገ. 14፥10። 30ይህም የሆነበት ምክንያት ኢዮርብዓም ራሱ በሠራው ኃጢአትና የእስራኤልም ሕዝብ ኃጢአት እንዲሠሩ በማድረግ የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ቊጣ ስላነሣሣ ነው።
31ናዳብ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። 32የይሁዳ ንጉሥ አሳ እና የእስራኤል ንጉሥ ባዕሻ በሥልጣን በነበሩበት ዘመን ሁሉ የማያቋርጥ የእርስበርስ ጦርነት ላይ ነበሩ።
የእስራኤል ንጉሥ ባዕሻ
33አሳ በይሁዳ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የአኪያ ልጅ ባዕሻ በመላው እስራኤል ላይ ነገሠ፤ መኖሪያውንም በቲርጻ በማድረግ ኻያ አራት ዓመት ገዛ። 34ከእርሱም በፊት እንደ ነበረው እንደ ንጉሥ ኢዮርብዓም ባዕሻ ራሱ ኃጢአት በመሥራትና የእስራኤልንም ሕዝብ ወደ ኃጢአት በመምራት እግዚአብሔርን አሳዘነ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ