የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 14

14
የኢዮርብዓም ወንድ ልጅ ሞት
1በዚያን ጊዜ የንጉሥ ኢዮርብዓም ወንድ ልጅ አቢያ ታሞ ነበር፤ 2ስለዚህ ኢዮርብዓም ሚስቱን እንዲህ አላት፦ “የእኔ ሚስት መሆንሽን ማንም እንዳያውቅ ልብስሽን ለውጠሽ ሌላ ሴት በመምሰል እኔ የእስራኤል ንጉሥ እንደምሆን የትንቢት ቃል የተናገረው ነቢዩ አኪያ ወደሚኖርባት ወደ ሴሎ ሂጂ፤ 3ዐሥር እንጀራ፥ ጥቂት ሙልሙል ዳቦና አንድ ገንቦ ማር. ውሰጂለት፤ ስለ ልጁ ሁኔታ እርሱ ይነግርሻል።”
4ስለዚህ የኢዮርብዓም ሚስት ይህን ሁሉ አዘጋጅታ በሴሎ ወደሚገኘው ወደ አኪያ ቤት ሄደች፤ ነቢዩ አኪያም በዕድሜው ከመሸምገሉ የተነሣ ዐይኖቹ ፈዘው ነበር፤ 5ይሁን እንጂ የኢዮርብዓም ሚስት ስለታመመው ልጅዋ ልትጠይቀው እንደምትመጣና ምን ሊነግራት እንደሚገባውም እግዚአብሔር አስቀድሞ ለነቢዩ አኪያ ገልጦለት ነበር።
የኢዮርብዓም ሚስት እዚያ በደረሰች ጊዜ ሌላ ሴት ለመምሰል ሞከረች፤ 6ነገር ግን ነቢዩ አኪያ ወደ በሩ ስትቀርብ የኮቴዋን ድምፅ ሰምቶ እንዲህ አላት፥ “ግቢ! የኢዮርብዓም ሚስት መሆንሽን ዐውቃለሁ፤ ሌላ ሴት ለመምሰል ስለምን ሞከርሽ? ለአንቺ እነግርሽ ዘንድ የታዘዝኩት አሳዛኝ ዜና አለ። 7ወደ ኢዮርብዓም ሂጂ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለውን ንገሪው፤ ቃሉም ይህ ነው፤ ‘ከሕዝብ መካከል መርጬ የሕዝቤ የእስራኤል መሪ አደረግኹህ፤ 8መንግሥትንም ከዳዊት ትውልድ ወስጄ ለአንተ ሰጠሁህ፤ ይሁን እንጂ አንተ ለእኔ ፍጹም ታማኝ ሆኖ ትእዛዞቼን እንደ ጠበቀውና እኔ ደስ የምሰኝበትን ነገር ሁሉ ያደርግ እንደ ነበረው እንደ አገልጋዬ እንደ ዳዊት ሆነህ አልተገኘህም፤ 9ይልቁንም ከአንተ በፊት መሪዎች ከነበሩ ሰዎች የከፋ ኃጢአት ሠራህ፤ እኔንም ትተህ ጣዖቶችና ከብረት የተቀረጹ ምስሎችን ለማምለክ በመሥራትህ ቊጣዬን አነሣሥተሃል፤ 10በዚህ ምክንያት እነሆ፥ በኢዮርብዓም ቤት ላይ ክፉ ነገርን አመጣለሁ፤ ከቤቱም ነጻም ሆነ ባሪያ፥ ወንድ ልጅን ሁሉ ከእስራኤል አጠፋለሁ፤ ፋንድያን አቃጥለው እንደሚጨርሱት የኢዮርብዓምን ቤት አወድማለሁ። #1ነገ. 15፥29። 11በከተማይቱ የሚሞተውን ማንኛውንም የቤተሰብህን አባል ውሾች ይበሉታል፤ ገላጣ በሆነው ገጠር የሚሞቱትንም አሞራ ይበላቸዋል፤ ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።’ ”
12አኪያም የሚናገረውን የትንቢት ቃል በመቀጠል ለኢዮርብዓም ሚስት እንዲህ አላት፤ “እንግዲህ አሁን ወደ ቤትሽ ተመልሰሽ ሂጂ፤ ወደ ከተማም እንደ ገባሽ ወዲያውኑ ልጁ ይሞታል፤ 13እስራኤላውያንም ሁሉ በማዘን አልቅሰው ይቀብሩታል፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የተደሰተበት ልጅ እርሱ ብቻ ስለ ሆነ ከኢዮርብዓምም ቤተሰብ መካከል ሥርዓተ ቀብር በሚገባ የሚፈጸምለት እርሱ ብቻ ይሆናል፤ 14እግዚአብሔርም ለራሱ የኢዮርብዓምን ቤት የሚያጠፋ ንጉሥ ዛሬ ያስነሣል፤ ይኸውም አሁን ነው። 15እግዚአብሔር እስራኤልን ይቀጣል፤ እርስዋም በውሃ ምንጭ ውስጥ እንደሚንቀጠቀጥ ሸምበቆ ትንቀጠቀጣለች፤ አሼራ ተብላ የምትጠራውን ሴት አምላክ ጣዖት በመሥራት ስላስቈጡት፤ የእስራኤልንም ሕዝብ ከዚህች ለቀድሞ አባቶቻቸው ከሰጣቸው ለም ምድር ነቃቅሎ ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ እንዲበታተኑ ያደርጋል፤ 16ኢዮርብዓም ኃጢአት ስለሠራና የእስራኤልንም ሕዝብ ወደ ኃጢአት ስለ መራ፥ እግዚአብሔር እስራኤልን ይተዋል።”
17የኢዮርብዓም ሚስት ወደ ቲርጻ ተመልሳ ወደ ቤትዋ ደጃፍ እንደ ደረሰች ወዲያውኑ ልጁ ሞተ። 18እግዚአብሔር ለአገልጋዩ ለነቢዩ አኪያ በነገረው መሠረት እስራኤላውያን በሐዘን አልቅሰው ቀበሩት።
የኢዮርብዓም መሞት
19ንጉሥ ኢዮርብዓም ያደረጋቸው ሌሎች ነገሮች ሁሉ፥ የተዋጋቸው ጦርነቶችና አገዛዙም እንዴት እንደ ነበር ሁሉም ነገር በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። 20ኢዮርብዓም ንጉሥ ሆኖ ኻያ ሁለት ዓመት ከገዛ በኋላ ሞቶ ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ልጁ ናዳብ ተተክቶ ነገሠ።
የይሁዳ ንጉሥ ሮብዓም
(2ዜ.መ. 11፥5—12፥15)
21የሰሎሞን ልጅ ሮብዓም በይሁዳ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው አርባ አንድ ዓመቱ ነበር፤ እርሱም መኖሪያውን እግዚአብሔር ከመላው የእስራኤል ግዛት መካከል ለስሙ መጠሪያ እንድትሆን በመረጣት ከተማ በኢየሩሳሌም አድርጎ ዐሥራ ሰባት ዓመት ገዛ፤ የሮብዓም እናት ናዕማ ተብላ የምትጠራ ዐሞናዊት ነበረች።
22የይሁዳ ሕዝብ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፤ የቀድሞ አባቶቹ ሲያደርጉት ከነበረው ይበልጥ በክፉ ሁኔታ በራሱ ላይ የእግዚአብሔርን ቊጣ አነሣሣ። 23ለባዕዳን አማልክትም የማምለኪያ ስፍራዎችን ሠሩ፤ በኮረብታዎች ላይና በዛፎች ጥላ ሥር የሚያመልኩአቸውን የድንጋይ ቅርጾችንና የአሼራን ምስሎች አቆሙ፤ #2ነገ. 17፥9-10። 24ከዚህም ሁሉ የከፋ በእነዚያ ሕዝቦች የማምለኪያ ስፍራዎች የቤተ ጣዖት አመንዝራዎች ነበሩ፤ እስራኤላውያን ወደ አገሪቱ ለመግባት እየገፉ በሄዱ መጠን እግዚአብሔር ከፊታቸው ነቃቅሎ ያባረራቸው አሕዛብ ይፈጽሙት የነበረውን አሳፋሪ ነገር ሁሉ የይሁዳም ሕዝብ ይፈጽመው ነበር። #ዘዳ. 23፥17።
25ሮብዓም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅ በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ ጣለ፤ 26በቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥት ተከማችቶ የነበረውንም ሀብት ሁሉ፥ ሰሎሞን ከወርቅ ያሠራቸውን ጋሻዎች ጭምር ዘርፎ ወሰደ፤ #1ነገ. 10፥16-17፤ 2ዜ.መ. 9፥15-16። 27እነርሱንም ለመተካት ንጉሥ ሮብዓም ጋሻዎችን ከነሐስ አሠርቶ የቤተ መንግሥቱን ቅጽር በር የመጠበቅ ኀላፊነት ባላቸው የዘብ አለቆች እንዲጠበቁ አደረገ፤ 28ንጉሡ ወደ ቤተ መቅደሱ በመጣ ቊጥር፥ የቤተ መቅደሱ ዘበኞች ጋሻዎችን አንግበው ይቀበሉታል፤ ከሄደም በኋላ ጋሻዎቹን መልሰው በዘበኞች በሚጠበቁበት ክፍል ያኖሩአቸው ነበር።
29ንጉሥ ሮብዓም ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፤ 30በዚህም ዘመን ሁሉ ሮብዓምና ኢዮርብዓም እርስ በርሳቸው በማያቋርጥ ጦርነት ላይ ነበሩ፤ 31ሮብዓም ሞተ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘው በነገሥታቱ መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ልጁ አቢያ ተተክቶ ነገሠ። የሮብዓም እናት ናዕማ ተብላ የምትጠራ ዐሞናዊት ነበረች።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ