አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 13
13
1ኢዮርብዓም መሥዋዕት ለማቅረብ በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ ሳለ በእግዚአብሔር ትእዛዝ የተላከ አንድ ነቢይ እነሆ ከይሁዳ መጥቶ እዚያ ደረሰ፤ 2ነቢዩም እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ያንን መሠዊያ በመቃወም እንዲህ ሲል የትንቢት ቃል ተናገረበት፦ “መሠዊያ! መሠዊያ ሆይ! እግዚአብሔር ስለ አንተ የሚለው ቃል ይህ ነው፦ ‘እነሆ ለዳዊት ቤተሰብ ኢዮስያስ ተብሎ የሚጠራ ልጅ ይወለዳል፤ እርሱም በኮረብታ ላይ ለተሠራው ለአሕዛብ መሠዊያ አገልጋዮች ሆነው መሥዋዕት የሚያቀርቡብህን ካህናት በአንተው ላይ ያርዳቸዋል፤ የሰዎችንም አጥንት በአንተ ላይ ያቃጥላል። #2ነገ. 23፥15-16። 3እግዚአብሔር ይህን ምልክት ይሰጣል፤ ይህ መሠዊያ ተሰባብሮ ይወድቃል፤ በእርሱ ላይ ያለውም ዐመድ ይበተናል፤ ይህንንም የትንቢት ቃል በእኔ አማካይነት የተናገረው ራሱ እግዚአብሔር መሆኑን ይህ እንደ ተፈጸመ ወዲያውኑ ትገነዘባለህ’ ” አለ።
4ንጉሥ ኢዮርብዓምም ይህን በሰማ ጊዜ እጁን አንሥቶ ወደ ነቢዩ በማመልከት! “ያዙት!” የሚል ትእዛዝ ሰጠ፤ የንጉሡም ክንድ ወዲያውኑ ድርቅ ብሎ ሽባ ስለ ሆነ የዘረጋውን እጁን መመለስ አልቻለም። 5የእግዚአብሔርም ነቢይ በእግዚአብሔር ስም በተናገረው የትንቢት ቃል መሠረት በእግዚአብሔር የተሰጠውም ምልክት ተፈጸመ፤ መሠዊያው ወዲያውኑ ተሰባብሮ ወደቀ፤ ዐመዱም መሬት ላይ ፈሰሰ። 6ንጉሡ ኢዮርብዓም “እባክህ እጄን ያድንልኝ ዘንድ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይልኝ!” ሲል የእግዚአብሔርን ነቢይ ለመነው። የእግዚአብሔርም ነቢይ ወደ እግዚአብሔር ጸልዮለት የንጉሡ እጅ ዳነች። እንደ ቀድሞም ሆነች። 7ከዚህም በኋላ ንጉሡ ነቢዩን “ና ከእኔ ጋር አብረህ ወደ ቤቴ ግባ፤ እህልም ቅመስ፤ ስጦታ እሰጥሃለሁ” አለው።
8የእግዚአብሔር ነቢይ ግን “የሀብትህን እኩሌታ ብትሰጠኝ እንኳ ወደ ቤትህ አልሄድም፤ ከአንተ ጋር እህል ውሃም አልቀምስም። 9ምንም ዐይነት እህል ውሃ እንዳልቀምስና ወደ ቤቴ ስመለስም በመጣሁበት መንገድ እንኳ እንዳልሄድ እግዚአብሔር አዞኛል” ሲል መለሰለት። 10ስለዚህም እርሱ ወደ ቤቴል የመጣበትን መንገድ በመተው በሌላ መንገድ ተመልሶ ሄደ።
ሽማግሌው የቤትኤል ነቢይ
11በዚያን ጊዜ በቤትኤል የሚኖር አንድ ሽማግሌ ነቢይ ነበር፤ ወንዶች ልጆቹ ወደ እርሱ ቀርበው፥ ከይሁዳ የመጣው ነቢይ በቤትኤል ስላደረገውና በንጉሥ ኢዮርብዓምም ላይ ስለ ተናገረው ቃል ሁሉ አወሩለት፤ 12አባታቸውም “ታዲያ ያ የእግዚአብሔር ነቢይ ከዚያ ተነሥቶ በየትኛው መንገድ ሄደ” ሲል ጠየቃቸው፤ እነርሱም የሄደበትን መንገድ በማመልከት አሳዩት፤ 13ከዚህም በኋላ እርሱ “አህያዬን ጫኑልኝ!” አላቸው፤ ልጆቹም አህያውን ጭነውለት ሽማግሌው ነቢይ በአህያው ላይ ተቀምጦ፥ 14ከይሁዳ የመጣው የእግዚአብሔር ነቢይ የሄደበትን መንገድ አቅጣጫ ይዞ ተከተለው፤ በአንድ የወርካ ዛፍ ሥር ተቀምጦም አገኘው።
ሽማግሌውም “ከይሁዳ የመጣኸው የእግዚአብሔር ነቢይ አንተ ነህን?” ሲል ጠየቀው።
እርሱም “አዎ እኔ ነኝ” ሲል መለሰለት።
15ሽማግሌውም “ወደ ቤቴ መጥተህ ከእኔ ጋር እህል ብላ” አለው።
16ከይሁዳ የመጣው የእግዚአብሔር ነቢይ ግን እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ከአንተ ጋር አብሬ ወደ ቤት መሄድም ሆነ ግብዣህን መቀበል አልችልም፤ በዚህም ከአንተ ጋር ምንም ዐይነት እህል ውሃ አልቀምስም፤ 17በዚህ ቦታ ምንም ዐይነት እህል ውሃ እንዳልቀምስ በመጣሁበት መንገድ እንኳ ተመልሼ እንዳልሄድ እግዚአብሔር አዞኛል።”
18ከዚህ በኋላ ከቤትኤል የመጣው ሽማግሌ ነቢይ “እኔም እንዳንተው ነቢይ ነኝ፤ ከእኔ ጋር ወደ ቤቴ ወስጄ እንዳስተናግድህ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ነግሮኛል” አለው፤ ሽማግሌው ነቢይ የተናገረው ግን በመዋሸት ነበር።
19ስለዚህ ከይሁዳ የመጣው የእግዚአብሔር ነቢይ ከሽማግሌው ነቢይ ጋር አብሮት ወደ ቤቱ ሄደ፤ ከእርሱም ጋር ተመገበ። 20በገበታም ቀርበው ሳሉ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ሽማግሌው ነቢይ መጣ፤ 21ከይሁዳ ለመጣው የእግዚአብሔር ሰው እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘አምላክህ እግዚአብሔር ያዘዘህን ትእዛዝ ባለመታዘዝ የእግዚአብሔርን ቃል አላከበርክም። 22ይህን በማድረግ ፈንታ እኔ በዚያ ምንም ዐይነት እህል ውሃ እንዳትቀምስ ወዳዘዝኩህ ቦታ ተመልሰህ በላህ፤ ይህንንም በማድረግህ ምክንያት ትገደላለህ፤ ሬሳህም በቤተሰብህ መቃብር አይቀበርም።’ ”
23ከተመገቡም በኋላ ሽማግሌው ነቢይ ከይሁዳ መልሶ ላመጣው የእግዚአብሔር ነቢይ አህያውን ጫነለት፤ 24እርሱም በአህያው ላይ ተቀምጦ ሄደ፤ በመንገድም አንበሳ አገኘውና ገደለው፤ ሬሳውም በመንገድ ላይ ተጋደመ፤ አህያውና አንበሳውም በሬሳው አጠገብ ቆመው ነበር። 25አንዳንድ ሰዎች በዚያ በኩል ሲያልፉ አጠገቡ ከቆመው አንበሳ ጋር ሬሳው በመንገድ ላይ ተጋድሞ አዩ፤ ሽማግሌው ነቢይ ወደሚኖርበት ወደ ቤቴል ከተማ መጥተው አወሩ።
26ሽማግሌው ነቢይ ይህን በሰማ ጊዜ “ያ ሰው የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ያልጠበቀው ነቢይ መሆን አለበት! ስለዚህም እግዚአብሔር ለአንበሳ አሳልፎ ሰጥቶታል ማለት ነው” አለ። 27ከዚህም በኋላ ልጆቹን “አህያዬን ጫኑልኝ!” አላቸው፤ እነርሱም ጫኑለት፤፥ 28በአህያው ላይ ተቀምጦ ሄደ፤ የነቢዩንም ሬሳ አህያውና አንበሳው እስከ አሁን በአጠገቡ እንደ ቆሙ በመንገድ ላይ ተጋድሞ አገኘው። አንበሳውም የነቢዩን ሬሳ አልበላም፤ በአህያውም ላይ አደጋ አልጣለበትም ነበር። 29ሽማግሌው ነቢይ ሬሳውን አንሥቶ በአህያው ላይ ጫነው፤ እንዲለቀስለትና እንዲቀበር ወደ ቤትኤል መልሶ ወሰደው። 30ሽማግሌውም ነቢይ በገዛ ራሱ ቤተሰብ መቃብር ቀበረው፤ እነርሱም “ወንድሜ ሆይ! ወንድሜ ሆይ!” እያሉ አለቀሱለት። 31ከቀብሩም ሥነ ሥርዓት በኋላ ሽማግሌው ነቢይ ለልጆቹ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ ስሞት በዚሁ መቃብር ቅበሩኝ፤ ሬሳዬንም ከእርሱ ሬሳ አጠገብ አጋድሙት፤ 32በቤትኤል በሚገኘው መሠዊያ ላይና በሰማርያ ታናናሽ ከተሞች በየኮረብታው ባሉት የማምለኪያ ስፍራዎች ላይ ከእግዚአብሔር በተሰጠው ትእዛዝ መሠረት ይህ የእግዚአብሔር ነቢይ የተናገረው የትንቢት ቃል በእርግጥ ይፈጸማል።”
መቅሠፍትን ያስከተለ የኢዮርብዓም አስከፊ ኃጢአት
33ይህም ሁሉ ሆኖ የእስራኤል ንጉሥ ኢዮርብዓም ከሚያደርገው ክፉ ነገር ሁሉ አልተመለሰም፤ ይልቁንም እርሱ በሠራቸው መሠዊያዎች የሚያገለግሉ ከሌዊ ዘር ውጪ ከሆኑ ቤተሰቦች መምረጡን ቀጥሎ ካህን ለመሆን ከፈለገ ማንኛውንም ሰው ይሾመው ነበር፤ 34ይህም ኃጢአቱ ለሥረወ መንግሥቱ መጥፋትና በሙሉ ለመደምሰሱ ምክንያት ሆነ።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 13: አማ05
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997