አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 17

17
ኤልያስ የድርቅ ጊዜ ስለ መምጣቱ መናገሩ
1በገለዓድ የምትገኘው የቱቢ ተወላጅ የሆነውና ኤልያስ ተብሎ የሚጠራው ነቢይ፤ ንጉሥ አክዓብን “በእኔ ቃል ካልሆነ በቀር በሚቀጥሉት ዓመቶች በምድር ላይ ጠል ወይም ዝናብ እንደማይኖር እኔ በማገለግለው በእስራኤል አምላክ፥ በሕያው እግዚአብሔር ስም እነግርሃለሁ” አለው። #ያዕ. 5፥17።
2ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤልያስ መጣ፤ 3“ከዚህ ተነሥተህ ወደ ምሥራቅ ሂድ፤ እዚያም ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ በሚገኘው ከሪት ተብሎ በሚጠራው ሸለቆ ተሸሸግ፤ 4የምትጠጣውንም ውሃ ከዚያው ወንዝ ታገኛለህ፤ ቊራዎችም ምግብ እንዲያመጡልህ አዝዣለሁ።”
5ኤልያስም እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ሄዶ በከሪት ሸለቆ ተቀመጠ፤ 6ከወንዙም ውሃ ጠጣ፤ ቊራዎችም ዘወትር ጧትና ማታ እንጀራና ሥጋ ያመጡለት ነበር፤ 7ዝናብ ጠፍቶ ድርቅ ከመሆኑ የተነሣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ያ ወንዝ ደረቀ።
ኤልያስና በስራጵታ ትኖር የነበረች መበለት
8ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ኤልያስን እንዲህ አለው፤ 9“እንግዲህ አሁን ከዚህ ተነሥተህ ሂድና በሲዶና በምትገኘው በስራጵታ ከተማ ተቀመጥ፤ እነሆ በዚያ የምትኖር አንዲት መበለት እንድትመግብህ አዝዣለሁ” አለው። #ሉቃ. 4፥25-26። 10ስለዚህ ኤልያስ ወደ ሰራጵታ ሄደ፤ ወደ ከተማይቱም ቅጽር በር በደረሰ ጊዜ አንዲት ባልዋ የሞተባት ሴት እንጨት ስትለቅም አይቶ “እባክሽ የምጠጣው ውሃ አምጪልኝ” አላት። 11ውሃም ልታመጣለት በመሄድ ላይ ሳለች ወዲያውኑ ጠርቶ “እባክሽ በተጨማሪ ትንሽ እንጀራ አምጪልኝ” አላት።
12እርስዋም እንዲህ ስትል መለሰችለት፤ “ምንም እንጀራ እንደሌለኝ በአምላክህ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ፤ በዱቄት ዕቃዬ ውስጥ ካለችው ከአንድ እፍኝ ዱቄትና በማሰሮዬ ውስጥ ካለችው ከጥቂት የወይራ ዘይት በቀር ምንም የለኝም፤ ወደዚህ የመጣሁት ትንሽ እንጨት ለቃቅሜ ወደ ቤቴ በመመለስ ይህችኑ ያለችኝን ትንሽ ዱቄት ለልጄና ለእኔ ለመጋገር ነው፤ ይህችም የመጨረሻ ምግባችን ናት፤ ከዚያም በኋላ በራብ ከመሞት አንተርፍም።”
13ኤልያስም እንዲህ አላት፤ “አይዞሽ አትጨነቂ! ሄደሽ ምግብሽን አዘጋጂ፤ አስቀድመሽ ግን ከዚያችው ካለችሽ ዱቄት ለእኔ ትንሽ እንጐቻ ጋግረሽ አምጪልኝ፤ የቀረውንም ለራስሽና ለልጅሽ ጋግሪው፤ 14የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ‘እኔ እግዚአብሔር ዝናብን እስከማወርድ ድረስ ዱቄቱ ከማኖሪያው ዕቃ፥ ዘይቱም ከማሰሮው ከቶ አያልቅም’ ሲል ተናግሮአል።”
15እርስዋም ሄዳ ኤልያስ እንደ ነገራት አደረገች፤ በዚህም ዐይነት እርስዋ፥ ቤተሰብዋና ኤልያስም ለብዙ ቀን የሚሆን በቂ ምግብ አገኙ። 16እግዚአብሔር በኤልያስ አማካይነት በሰጠው ተስፋ መሠረት ዱቄቱ ከማኖሪያው ዕቃ፥ ዘይቱም ከማሰሮው አላለቀም።
17ከጥቂት ጊዜም በኋላ የዚያች ባልዋ የሞተባት ሴት ልጅ ታመመ፤ ሕመሙም እየባሰበት ስለ ሄደ በመጨረሻ ሞተ፤ 18እርስዋም ኤልያስን “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ! ስለምን ይህን አደረግህብኝ? ወደዚህ የመጣኸው ኃጢአቴን አስታውሰህ ልጄ እንዲሞትብኝ ለማድረግ ነውን?” ስትል ጠየቀችው።
19ኤልያስም “ልጅሽን ወደ እኔ አምጪው” አላት። ልጁንም ከዕቅፍዋ ወስዶ እርሱ ወደሚኖርበት ሰገነት አውጥቶ በአልጋው ላይ አጋደመው፤ 20ከዚህ በኋላ ኤልያስ ድምፁን ከፍ በማድረግ “እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ! ስለምን በዚህች ባልዋ በሞተባት ሴት ላይ ይህን የመሰለ አሠቃቂ ነገር አደረግህ? እርስዋ እኔን በማስተናገድ ታላቅ ቸርነት አድርጋልኛለች፤ ታዲያ አንተ ስለምን ልጅዋ እንዲሞት አደረግህ?” ሲል ጸለየ። 21ከዚህ በኋላ ኤልያስ በልጁ ላይ ሦስት ጊዜ ተዘርሮ “እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ! እባክህ ይህን ልጅ ከሞት አስነሣው!” ሲል ጸለየ። #2ነገ. 4፥34-35። 22እግዚአብሔርም የኤልያስን ጸሎት ሰማ፤ የልጁም እስትንፋስ እንደገና ተመልሶለት ዳነ።
23ኤልያስ ልጁን ከሰገነት ወደ ምድር ቤት አውርዶ ለእናቱ በመስጠት “ተመልከቺ፤ እነሆ ልጅሽ ከሞት ወደ ሕይወት ተመልሶአል!” አላት።
24እርስዋም “እነሆ አንተ የእግዚአብሔር ሰው መሆንህንና እግዚአብሔርም በአንተ አማካይነት መናገሩን አሁን አረጋገጥኩ!” ስትል መለሰችለት።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ