የእግዚአብሔርም ቃል በባኦስ ላይ እንዲህ ብሎ ወደ አናኒ ልጅ ወደ ኢዩ መጣ። እኔ ከመሬት አስነሥቼ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ አለቃ አድርጌሃለሁ፤ አንተ ግን በኢዮርብዓም መንገድ ሄደሃል፤ በኀጢአታቸውም ያስቆጡኝ ዘንድ ሕዝቤን እስራኤልን አስተሃቸዋል። ስለዚህም፥ እነሆ፥ ባኦስንና ቤቱን ፈጽሜ እጠርጋለሁ፤ ቤትህንም እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት አደርጋለሁ። ከባኦስም ወገን በከተማይቱ ውስጥ የሚሞተውን ውሾች ይበሉታል፤ በሜዳውም የሚሞተውን የሰማይ ወፎች ይበሉታል። የቀረውም የባኦስ ነገር፥ ሥራውና ጭከናውም፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? ባኦስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በቴርሳም ተቀበረ፤ ልጁም ኤላ በፋንታው ነገሠ። በእጁም ሥራ ያስቆጣው ዘንድ፥ እንደ ኢዮርብዓም ቤት በእግዚአብሔር ፊት ስላደረገው ክፋት ሁሉ እርሱንም ስለ ገደለው፥ የእግዚአብሔር ቃል በባኦስና በቤቱ ላይ ወደ አናኒ ልጅ ወደ ነቢዩ ወደ ኢዩ መጣ። በይሁዳም ንጉሥ በአሳ በኻያ ስድስተኛው ዓመት የባኦስ ልጅ ኤላ በእስራኤል ላይ በቴርሳ ሁለት ዓመት ነገሠ። የእኩሌቶቹም ሠረገሎች አለቃ ዘምሪ ተማማለበት፤ ኤላም በቴርሳ ነበረ፤ በቴርሳም በነበረው በቤት አሽከሮች አለቃ በአሳ ቤት ይሰክር ነበር። በይሁዳም ንጉሥ በአሳ በኻያ ሰባተኛው ዓመት ዘምሪ ገብቶ መታው፤ ገደለውም፤ በፋንታውም ነገሠ። ንጉሥም በሆነ ጊዜ፥ በዙፋኑም በተቀመጠ ጊዜ፥ የባኦስን ቤት ሁሉ መታ፤ ከዘመዶችና ከወዳጆች ሁሉ አንድ ወንድ እንኳ አልቀረም። ባኦስና ልጁ ኤላ ስለ ሠሩት ኀጢአት ሁሉ፥ በምናምንቴም ሥራቸው የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ያስቆጡት ዘንድ እስራኤልን ስለ አሳቱበት ኀጢአት፥ በነቢዩ በኢዩ አማካይነት በባኦስ ላይ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል ዘምሪ የባኦስን ቤት ሁሉ እንዲሁ አጠፋ። የቀረውም የኤላ ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? በይሁዳ ንጉሥ በአሳ በኻያ ሰባተኛው ዓመት ዘምሪ በቴርሳ ሰባት ቀን ነገሠ። ሕዝቡም በፍልስጥኤም አገር የነበረው ገባቶንን ከብበው ነበር። ከተማይቱንም ከብበው የነበሩ ሕዝብ ዘምሪ እንደ ዐመፀ፥ ንጉሡንም እንደ ገደለ ሰሙ፤ እስራኤልም ሁሉ በዚያ ቀን በሰፈሩ ውስጥ የሠራዊቱን አለቃ ዖምሪን አነገሡ። ዖምሪም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ከገባቶን ወጥተው ቴርሳን ከበቡ። ዘምሪም ከተማይቱ እንደ ተያዘች ባየ ጊዜ ወደ ንጉሡ ቤት ግንብ ውስጥ ገባ፤ የንጉሡንም ቤት በራሱ ላይ በእሳት አቃጠለ፤ ስላደረገውም ኀጢአት፥ እስራኤልንም ስላሳተበት ኀጢአት፥ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አድርጎአልና፥ በኢዮርብዓምም መንገድ ሄዶአልና ሞተ። የቀረውም የዘምሪ ነገር፥ ያደረገውም ዐመፅ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 16 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 16:1-20
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች