መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 16
16
1የእግዚአብሔርም ቃል ስለ ባኦስ እንዲህ ብሎ ወደ አናኒ ልጅ ወደ ኢዩ መጣ። 2“እኔ ከመሬት አንሥቼ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ አለቃ አድርጌሃለሁ፤ አንተ ግን በከንቱ ጣዖታቸው ያስቈጡኝ ዘንድ ሕዝቤን እስራኤልን በአሳታቸው በኢዮርብዓም መንገድ ሄድህ፤ 3ስለዚህም፥ እነሆ፥ ባኦስንና ቤቱን ፈጽሜ አጠፋለሁ፤ ቤትህንም እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት አደርጋለሁ። 4ከባኦስም ወገን በከተማዪቱ ውስጥ የሚሞተውን ውሾች ይበሉታል፤ በሜዳውም የሚሞተውን የሰማይ ወፎች ይበሉታል።”
5የቀረውም የባኦስ ነገር፥ የሠራውም ሁሉ፥ ኀይሉም ሁሉ፥ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ ነው። 6ባኦስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በቴርሳም ተቀበረ፤ ልጁም ኤላ በአሳ በሃያ ስድስተኛው ዓመተ መንግሥት በፋንታው ነገሠ። 7በእጁም ሥራ ያስቈጣው ዘንድ፥ እንደ ኢዮርብዓም ቤት በእግዚአብሔር ፊት ስላደረገው ክፋት ሁሉ እርሱንም ስለ ገደለው፥ የእግዚአብሔር ቃል በባኦስና በቤቱ ላይ ወደ አናኒ ልጅ ወደ ነቢዩ ኢዩ መጣ።
8የባኦስም ልጅ ኤላ በእስራኤል ላይ በቴርሳ ሁለት ዓመት ነገሠ። 9የእኩሌቶቹ ፈረሶች አለቃ ዘምሪም አሽከሮቹን ሁሉ ሰብስቦ ዐመፀ፤ ኤላም በቴርሳ ነበረ፤ በቴርሳም በነበረው በመጋቢው በአሳ ቤት ይሰክር ነበር። 10በይሁዳም ንጉሥ በአሳ በሃያ ሰባተኛው ዓመት ዘምሪ ገብቶ ወጋና ገደለው፤ በፋንታውም ነገሠ። 11ከነገሠና በዙፋኑም ከተቀመጠ በኋላ፥ የባኦስን ቤት ሁሉ አጠፋ፤ አንድ ወንድ እንኳ አላስቀረለትም። 12በነቢዩ በኢዩ አፍ በባኦስ ቤት ላይ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል፥ 13ባኦስና ልጁ ኤላ ስለ ሠሩት ኀጢአት ሁሉ፥ በርኵሰታቸው የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ያስቈጡት ዘንድ እስራኤልን ስለ አሳቱበት ኀጢአት፥ ዘምሪ የባኦስን ቤት ሁሉ እንዲሁ አጠፋ። 14የቀረውም የኤላ ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ ነው።
15በይሁዳም ንጉሥ በአሳ በሃያ ዘጠነኛው ዓመት#ዕብ. “በሃያ ሰባተኛው ዓመት” ይላል በግሪክ ሰባ. ሊ. ግን ሁሉም የለም። ዘምሪ በቴርሳ ሰባት ቀን ነገሠ። የእስራኤል ሠራዊት ግን በፍልስጥኤም ሀገር በገባቶን ሰፍረው ነበር። 16በሰፈር ያሉ ሕዝቡም “ዘምሪ ከድቶ ኤላን ገደለው፥ በፋንታውም ነገሠ” ሲሉ ሰሙ። እስራኤልም ሁሉ በዚያ ቀን በሰፈሩ ውስጥ የሠራዊቱን አለቃ ዘንበሪን#ዕብ. “ኦምሪን” ይላል። አነገሡ። 17ዘንበሪም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ከገባቶን ወጥተው ቴርሳን ከበቡ። በእርስዋም ተቀመጡ። 18ዘምሪም ከተማዪቱ እንደ ተያዘች ባየ ጊዜ ወደ ንጉሡ ቤት ግንብ ውስጥ ገባ፤ የንጉሡንም ቤት በራሱ ላይ በእሳት አቃጠለ፤ ሞተም። 19ስላደረገውም ኀጢአት፥ እስራኤልንም ስላሳተበት ኀጢአት፥ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አድርጎአልና፥ በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓምም መንገድ ሄዶአልና ሞተ። 20የቀረውም የዘምሪ ነገር፥ ያደረገውም ዐመፅ፥ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ ነው።
21በዚያም ጊዜ የእስራኤል ሕዝብ በሁለት ተከፈለ፤ የሕዝቡም እኩሌታ የጎናትን ልጅ ታምኒን ያነግሡት ዘንድ ተከተሉት፤ እኩሌቶችም ዘንበሪን ተከተሉ። 22ዘንበሪንም የተከተሉ ሕዝብ የጎናት ልጅ ታምኒን የተከተሉትን ሕዝብ ድል አደረጉአቸው፤ ታምኒም ሞተ፤ ወንድሙም ኢዮራም በዚያው ዘመን ሞተ፤#“ወንድሙ ኢዮራም በዚያው ዘመን ሞተ” የሚለው በዕብ. የለም። ከታምኒ በኋላ ዘንበሪ ነገሠ። 23በይሁዳ ንጉሥ በአሳ በሠላሳ አንደኛው ዓመተ መንግሥት ዘንበሪ በእስራኤል ላይ ዐሥራ ሁለት ዓመት ነገሠ። በቴርሳም ስድስት ዓመት ነገሠ። 24ዘንበሪም ከዚያች ተራራ ባለቤት ከሴሜር በሁለት መክሊት ብር የሳምሮንን ተራራ ገዛ፤ በተራራውም ላይ ከተማ ሠራ፤ የሠራትንም ከተማ በተራራው ባለቤት በሳምር ስም ሰማርያ ብሎ ጠራት። 25ዘንበሪም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፤ ከእርሱም አስቀድሞ ከነበሩት ይልቅ እጅግ ከፋ። 26በናባጥም ልጅ በኢዮርብዓም መንገድ ሁሉ በርኩስነታቸው የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ያስቈጡት ዘንድ እስራኤልን ባሳተበት ኀጢአት ሄደ። 27የቀረውም ዘንበሪ ያደረገው ነገር፥ የሠራውም ጭከና፥ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ ነው። 28ዘንበሪም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በሰማርያም ቀበሩት፤ ልጁም አክአብ በፋንታው ነገሠ።
28 ‘ሀ’ ዘንበሪም ዐሥራ አንድ ዓመት ሲሆነው የአሳ ልጅ ኢዮሳፍጥ ነገሠ። በነገሠም ጊዜ ሠላሳ አምስት ዓመት ሆኖት ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሃያ አምስት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ጋዙባ የምትባል የሴላህ ልጅ ነበረች።
28 ‘ለ’ በአባቱም በአሳ መንገድ ሄደ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ጽድቅን ያደርግ ዘንድ ከእርስዋ ፈቀቅ አላለም። በተራሮች የነበሩትንም አማልክት አላስወገደም፤ ሕዝቡም በተራሮቹ ይሠዉላቸውና ያጥኑላቸው ነበረ። 28 ‘ሐ’ ኢዮሳፍጥም ከእስራኤል ንጉሥ ጋር የሠራው፥ የተዋጋውና ያደረገው ኀይል ሁሉ እነሆ፥ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ ነው። 28 ‘መ’ በአባቱም በአሳ ዘመን የነበረውን ርኵሰት ሁሉ ከምድር አስወገደ። በኤዶምም#“ኤዶም” የሚለው በአንዳንድ ትርጕሞች “ሶርያ” ይላል። ንጉሥ አልነበረም።#ግሪክ ሰባ. ሊ. “በናሴብ ሶርያ” ይላል።
28 ‘ሠ’ ንጉሥ ኢዮሳፍጥም ወርቅና ብርን ሊያመጡለት ወደ አፌር ይልክ ዘንድ በተርሴስ መርከብ አሠራ፤ በጋስዮንጋቤር የነበረችው መርከብ ተሰብራለችና አልሄደችም። 28 ‘ረ’ የእስራኤልም ንጉሥ አካዝያስ ኢዮሳፍጥን፥ “አገልጋዮችህንና አገልጋዮቼን በመርከብ እንላክ” አለው። ኢዮሳፍጥም እንቢ አለ። 28 ‘ሰ’ ኢዮሳፍጥም እንደ አባቶቹ አንቀላፋ። በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ። በእርሱም ፋንታ ልጁ ኢዮራም ነገሠ።#ምዕ. 16 ከቍ. 28“ሀ” እስከ 28“ሰ” ያለው በዕብ. የለም ግሪክ ሰባ. ሊ. ያለ ቍጥር ይጽፋል።
የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ እንደ ነገሠ
29በይሁዳም ንጉሥ በኢዮሳፍጥ በሁለተኛው ዓመት#ዕብ. “በአሳ በሠላሳ ስምንተኛው ዓመት የዘንበሪ ልጅ አክዓብ በእስራኤል ላይ ነገሠ” ይላል። የዘንበሪ ልጅ አክዓብ በእስራኤል ላይ በሰማርያ ሃያ ሁለት ዓመት ነገሠ። 30አክዓብም ከእርሱ በፊት ከነበሩት ሁሉ ይልቅ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ። 31በናባጥም ልጅ በኢዮርብዓም ኀጢአት መሄድ አልበቃውም፤ የሲዶናውያንንም ንጉሥ የኤያትባሔልን ልጅ ኤልዛቤልን አገባ፤ ሄዶም በዓልን አመለከ ሰገደለትም። 32በሰማርያም በሠራው በበዓል ቤት ውስጥ ለበዓል መሠዊያን ሠራ። 33አክዓብም የማምለኪያ ዐፀድን አሠራ፤ አክዓብም ሰውነቱ እንድትጠፋ ከእርሱ በፊት ከነበሩት ከእስራኤል ነገሥታት ሁሉ ይልቅ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን የሚያስቈጣውን ነገር አበዛ። 34በእርሱም ዘመን የቤቴል ሰው አኪያል ኢያሪኮን ሠራ፤ በነዌም ልጅ በኢያሱ ቃል እንደ ተነገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል፥ በበኵር ልጁ በአቢሮን መሠረቷን አደረገ፥ በታናሹ ልጁም በዜጉብ በሮችዋን አቆመ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 16: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ