የሉቃስ ወንጌል 7:1-10

የሉቃስ ወንጌል 7:1-10 መቅካእኤ

እርሱም ለአድማጩ ሕዝብ ንግግሩን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ገባ። አንድ የመቶ አለቃም ነበረ፤ የሚወደውም ባርያው ታሞ ሊሞት ቀርቦ ነበር። ስለ ኢየሱስም በሰማ ጊዜ የአይሁድን ሽማግሌዎች ወደ እርሱ ልኮ ባርያውን መጥቶ እንዲያድን ለመነው። እነርሱም ወደ ኢየሱስ መጥተው እንዲህ እያሉ አጥብቀው ለመኑት፦ “ይህን ልታደርግለት ይገባዋል፤ ሕዝባችንን ይወዳልና፤ ምኵራብም የሠራልን እርሱ ነው።” ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ሄደ። ወደ ቤቱም በቀረበ ጊዜ መቶ አለቃው ወዳጆቹን ወደ እርሱ ልኮ እንዲህ አለው፦ “ጌታ ሆይ! ከቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝምና ራስህን አታድክም፤ ወደ አንተም ለመምጣት እንኳ ራሴን የተገባሁ አድርጌ አልቆጠርሁትም፤ ነገር ግን አንዲት ቃል ተናገር፤ አገልጋዬም ይፈወሳል። እኔ በእርግጥ ከሌሎች ሥልጣናት በታች የተሾምሁ ሰው ነኝ፤ ከእኔም በታች ወታደሮች አሉኝ፤ አንዱንም ‘ሂድ!’ ብለው ይሄዳል፤ ሌላውንም ‘ና!’ ብለው ይመጣል፤ ኣገልጋዬንም ‘ይህን አድርግ!’ ብለው ያደርጋል።” ኢየሱስም ይህንን ሰምቶ በእርሱ ተደነቀ፤ ዘወርም ብሎ ለተከተሉት ሕዝብ እንዲህ አለ፦ “እላችኋለሁ፤ በእስራኤል እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም።” የተላኩትም ወደ ቤት ተመልሰው ኣገልጋዩን በመልካም ጤንነት ላይ ሆኖ አገኙት።