የሉቃስ ወንጌል 7:1-10

የሉቃስ ወንጌል 7:1-10 አማ05

ኢየሱስ ይህን ሁሉ ለሕዝቡ ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ሄደ። በዚያም አንድ ሮማዊ የመቶ አለቃ ነበረ። እርሱም የሚወድደው አገልጋይ በጠና ታሞበት ለሞት ተቃርቦ ነበር። የመቶ አለቃው ስለ ኢየሱስ በሰማ ጊዜ የአይሁድ ሽማግሌዎችን “እባካችሁ ኢየሱስ መጥቶ አገልጋዬን እንዲፈውስልኝ ሄዳችሁ ለምኑልኝ፥” ሲል ላካቸው። እነርሱም ወደ ኢየሱስ ሄደው፥ “ይህን ልታደርግለት የሚገባው ሰው ነው፤ እርሱ ሕዝባችንን ይወዳል፤ ምኲራብም ሠርቶልናል፤” ሲሉ አጥብቀው ለመኑት። ስለዚህ ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር አብሮ ሄደ፤ ወደ ቤቱም በቀረበ ጊዜ የመቶ አለቃው ወዳጆቹን እንዲህ ሲል ወደ ኢየሱስ ላከ፦ “ጌታ ሆይ፥ አንተ ወደ ቤቴ ትገባ ዘንድ ያልተገባሁ ነኝና ወደ ቤቴ ለመምጣት አትድከም። እኔም ራሴ ወደ አንተ ለመምጣት የበቃሁ ሰው አይደለሁም። ስለዚህ አንተ እዚያው ሆነህ አንድ ቃል ተናገር፤ አገልጋዬም ይድናል። እኔ ራሴ ለባለ ሥልጣኖች ታዛዥ ስሆን ከእኔ በታች የማዛቸው ወታደሮች አሉኝ። ስለዚህ አንዱን ‘ሂድ!’ ስለው ይሄዳል፤ ሌላውን ‘ና!’ ስለው ይመጣል፤ አገልጋዬንም ‘ይህን አድርግ!’ ስለው ያደርጋል።” ኢየሱስ ይህን በሰማ ጊዜ ተደነቀ፤ ወደሚከተሉትም ሰዎች መለስ ብሎ፥ “በእስራኤል እንኳ እንዲህ ያለ እምነት ከቶ አላገኘሁም እላችኋለሁ፤” አላቸው። የተላኩትም ሰዎች ወደ መቶ አለቃው ቤት ተመልሰው በመጡ ጊዜ አገልጋዩን ድኖ አገኙት።