ሉቃስ 7:1-10

ሉቃስ 7:1-10 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ለሕ​ዝ​ቡም ቃሉን ነግሮ ከፈ​ጸመ በኋላ ወደ ቅፍ​ር​ና​ሆም ገባ። አንድ የመቶ አለ​ቃም ነበረ፤ አገ​ል​ጋ​ዩም ታሞ ሊሞት ቀርቦ ነበር፤ እር​ሱም በእ​ርሱ ዘንድ የተ​ወ​ደደ ነበር። የጌ​ታ​ችን የኢ​የ​ሱ​ስ​ንም ነገር በሰማ ጊዜ፥ መጥቶ አገ​ል​ጋ​ዩን እን​ዲ​ያ​ድ​ን​ለት ይማ​ል​ዱት ዘንድ የአ​ይ​ሁ​ድን ሽማ​ግ​ሎች ወደ እርሱ ላከ። ወደ ጌታ​ችን ወደ ኢየ​ሱ​ስም መጥ​ተው ማለ​ዱት፤ እን​ዲ​ህም አሉት፥ “ፈጥ​ነህ ውረድ፤ ይህን ልታ​ደ​ር​ግ​ለት ይገ​ባ​ዋ​ልና። እርሱ ወገ​ና​ች​ንን ይወ​ዳ​ልና፤ ምኵ​ራ​ባ​ች​ን​ንም ሠር​ቶ​ል​ና​ልና።” ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም ከእ​ነ​ርሱ ጋር ሄደ፤ ወደ ቤቱም በቀ​ረበ ጊዜ፥ የመቶ አለ​ቃዉ ወዳ​ጆ​ቹን እን​ዲህ ብሎ ላከ፥ “አቤቱ፥ አት​ድ​ከም፤ ከቤቴ ጣራ በታች ልት​ገባ አይ​ገ​ባ​ኝ​ምና። እኔም ወደ አንተ ልመጣ አይ​ገ​ባ​ኝም፤ ነገር ግን በቃ​ልህ እዘዝ፤ ብላ​ቴ​ና​ዬም ይድ​ናል። እኔም እኮ ገዢ ሰው ነኝ፤ ወታ​ደ​ሮ​ችም አሉኝ፤ አን​ዱን ሂድ ብለው ይሄ​ዳል፤ ሌላ​ው​ንም ና ብለው ይመ​ጣል፤ አገ​ል​ጋ​ዬ​ንም እን​ዲህ አድ​ርግ ብለው ያደ​ር​ጋል።” ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም ይህን ከእ​ርሱ በሰማ ጊዜ አደ​ነ​ቀው፤ ዘወር ብሎም ይከ​ተ​ሉት ለነ​በ​ሩት ሕዝብ፥ “እላ​ች​ኋ​ለሁ፥ በእ​ስ​ራ​ኤ​ልስ እንኳ እን​ዲህ ያለ እም​ነት ያለው ሰው አላ​ገ​ኘ​ሁም” አላ​ቸው። የተ​ላ​ኩ​ትም በተ​መ​ለሱ ጊዜ ብላ​ቴ​ና​ውን ድኖ አገ​ኙት።

ሉቃስ 7:1-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ኢየሱስ ይህን ሁሉ በሕዝቡ ፊት ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ገባ። በዚያም አንድ የመቶ አለቃ ነበረ፤ እጅግ የሚወድደው ባሪያውም ታምሞበት ለሞት ተቃርቦ ነበር። እርሱም ስለ ኢየሱስ በሰማ ጊዜ፣ ባሪያውን መጥቶ እንዲፈውስለት ይለምኑት ዘንድ አንዳንድ የአይሁድ ሽማግሌዎችን ላከበት። መልእክተኞቹም ወደ ኢየሱስ በመጡ ጊዜ እንዲህ ብለው አጥብቀው ለመኑት፤ “ይህን ልታደርግለት ይገባዋል፤ ምክንያቱም ይህ ሰው ሕዝባችንን ይወድዳል፤ ምኵራባችንንም ያሠራልን እርሱ ነው።” ኢየሱስም ከእነርሱ ጋራ ሄደ። እርሱም ወደ ቤቱ በተቃረበ ጊዜ፣ የመቶ አለቃው ወዳጆቹን ልኮ እንዲህ አለው፤ “ጌታ ሆይ፤ ከቤቴ ጣራ በታች ልትገባ የሚገባኝ ሰው አይደለሁምና አትድከም፤ ከዚህም የተነሣ በአንተ ፊት ለመቅረብ እንኳ እንደሚገባኝ ራሴን አልቈጠርሁም፤ ብቻ አንድ ቃል ተናገር፤ ብላቴናዬም ይፈወሳል። እኔ ራሴ የበላይ አለቃ አለኝ፤ ከበታቼም የማዝዛቸው ወታደሮች አሉኝ፤ አንዱን፣ ‘ሂድ’ ስለው ይሄዳል፤ ሌላውን፣ ‘ና’ ስለው ይመጣል፤ ባሪያዬንም፣ ‘ይህን አድርግ’ ስለው ያደርጋል።” ኢየሱስም ይህን ሲሰማ በርሱ ተደነቀ፤ ዘወር ብሎም ይከተለው ለነበረው ሕዝብ፣ “እላችኋለሁ፤ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት በእስራኤል እንኳ አላገኘሁም” አላቸው። የተላኩት ሰዎችም ወደ ቤት በተመለሱ ጊዜ፣ ባሪያውን ድኖ አገኙት።

ሉቃስ 7:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ቃሉን ሁሉ በሕዝብ ጆሮዎች በጨረሰ ጊዜ ወደ ቅፍርናሆም ገባ። አንድ የመቶ አለቃም ነበረ፤ የሚወደውም ባሪያው ታሞ ሊሞት ቀርቦ ነበር። ስለ ኢየሱስም በሰማ ጊዜ የአይሁድን ሽማግሎች ወደ እርሱ ላከና መጥቶ ባሪያውን እንዲያድን ለመነው። እነርሱም ወደ ኢየሱስ መጥተው፦ ይህን ልታደርግለት ይገባዋል፤ ሕዝባችንን ይወዳልና ምኵራብም ራሱ ሠርቶልናል ብለው አጽንተው ለመኑት። ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ሄደ። አሁንም ወደ ቤቱ በቀረበ ጊዜ የመቶው አለቃ ወዳጆቹን ወደ እርሱ ላከ፤ አለውም፦ ጌታ ሆይ በቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝምና አትድከም፤ ስለዚህም ወደ አንተ ልመጣ እንዲገባኝ ሰውነቴን አልቈጠርሁትም፤ ነገር ግን ቃል ተናገር፥ ብላቴናዬም ይፈወሳል። እኔ ደግሞ ከሌሎች በታች የምገዛ ሰው ነኝ፥ ከእኔም በታች ወታደሮች አሉኝ፥ አንዱንም፦ ሂድ ብለው ይሄዳል፥ ሌላውንም፦ ና ብለው ይመጣል፥ ባሪያዬንም፦ ይህን አድርግ ብለው ያደርጋል። ኢየሱስም ይህን ሰምቶ በእርሱ ተደነቀ፥ ዘወርም ብሎ ለተከተሉት ሕዝብ፦ እላችኋለሁ፥ በእስራኤልስ እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም አላቸው። የተላኩትም ወደ ቤት ተመልሰው ባሪያውን ባለ ጤና ሆኖ አገኙት።

ሉቃስ 7:1-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ኢየሱስ ይህን ሁሉ ለሕዝቡ ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ሄደ። በዚያም አንድ ሮማዊ የመቶ አለቃ ነበረ። እርሱም የሚወድደው አገልጋይ በጠና ታሞበት ለሞት ተቃርቦ ነበር። የመቶ አለቃው ስለ ኢየሱስ በሰማ ጊዜ የአይሁድ ሽማግሌዎችን “እባካችሁ ኢየሱስ መጥቶ አገልጋዬን እንዲፈውስልኝ ሄዳችሁ ለምኑልኝ፥” ሲል ላካቸው። እነርሱም ወደ ኢየሱስ ሄደው፥ “ይህን ልታደርግለት የሚገባው ሰው ነው፤ እርሱ ሕዝባችንን ይወዳል፤ ምኲራብም ሠርቶልናል፤” ሲሉ አጥብቀው ለመኑት። ስለዚህ ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር አብሮ ሄደ፤ ወደ ቤቱም በቀረበ ጊዜ የመቶ አለቃው ወዳጆቹን እንዲህ ሲል ወደ ኢየሱስ ላከ፦ “ጌታ ሆይ፥ አንተ ወደ ቤቴ ትገባ ዘንድ ያልተገባሁ ነኝና ወደ ቤቴ ለመምጣት አትድከም። እኔም ራሴ ወደ አንተ ለመምጣት የበቃሁ ሰው አይደለሁም። ስለዚህ አንተ እዚያው ሆነህ አንድ ቃል ተናገር፤ አገልጋዬም ይድናል። እኔ ራሴ ለባለ ሥልጣኖች ታዛዥ ስሆን ከእኔ በታች የማዛቸው ወታደሮች አሉኝ። ስለዚህ አንዱን ‘ሂድ!’ ስለው ይሄዳል፤ ሌላውን ‘ና!’ ስለው ይመጣል፤ አገልጋዬንም ‘ይህን አድርግ!’ ስለው ያደርጋል።” ኢየሱስ ይህን በሰማ ጊዜ ተደነቀ፤ ወደሚከተሉትም ሰዎች መለስ ብሎ፥ “በእስራኤል እንኳ እንዲህ ያለ እምነት ከቶ አላገኘሁም እላችኋለሁ፤” አላቸው። የተላኩትም ሰዎች ወደ መቶ አለቃው ቤት ተመልሰው በመጡ ጊዜ አገልጋዩን ድኖ አገኙት።

ሉቃስ 7:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

እርሱም ለአድማጩ ሕዝብ ንግግሩን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ገባ። አንድ የመቶ አለቃም ነበረ፤ የሚወደውም ባርያው ታሞ ሊሞት ቀርቦ ነበር። ስለ ኢየሱስም በሰማ ጊዜ የአይሁድን ሽማግሌዎች ወደ እርሱ ልኮ ባርያውን መጥቶ እንዲያድን ለመነው። እነርሱም ወደ ኢየሱስ መጥተው እንዲህ እያሉ አጥብቀው ለመኑት፦ “ይህን ልታደርግለት ይገባዋል፤ ሕዝባችንን ይወዳልና፤ ምኵራብም የሠራልን እርሱ ነው።” ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ሄደ። ወደ ቤቱም በቀረበ ጊዜ መቶ አለቃው ወዳጆቹን ወደ እርሱ ልኮ እንዲህ አለው፦ “ጌታ ሆይ! ከቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝምና ራስህን አታድክም፤ ወደ አንተም ለመምጣት እንኳ ራሴን የተገባሁ አድርጌ አልቆጠርሁትም፤ ነገር ግን አንዲት ቃል ተናገር፤ አገልጋዬም ይፈወሳል። እኔ በእርግጥ ከሌሎች ሥልጣናት በታች የተሾምሁ ሰው ነኝ፤ ከእኔም በታች ወታደሮች አሉኝ፤ አንዱንም ‘ሂድ!’ ብለው ይሄዳል፤ ሌላውንም ‘ና!’ ብለው ይመጣል፤ ኣገልጋዬንም ‘ይህን አድርግ!’ ብለው ያደርጋል።” ኢየሱስም ይህንን ሰምቶ በእርሱ ተደነቀ፤ ዘወርም ብሎ ለተከተሉት ሕዝብ እንዲህ አለ፦ “እላችኋለሁ፤ በእስራኤል እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም።” የተላኩትም ወደ ቤት ተመልሰው ኣገልጋዩን በመልካም ጤንነት ላይ ሆኖ አገኙት።