ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለምን ትጮኽብኛለህ? የእስራኤልን ልጆች ጉዞ እንዲቀጥሉ ንገራቸው። አንተም በትርህን አንሣ፥ እጅህንም በባህሩ ላይ ዘርጋ፥ ክፈለውም፤ የእስራኤልም ልጆች በባህሩ ውስጥ በደረቅ ምድር ያልፋሉ። እነሆ እኔ የግብፃውያንን ልብ አጸናለሁ፥ ከኋላቸውም ይገባሉ፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ በሰረገሎቹም በፈረሰኞቹም ላይ ክብር አገኛለሁ። ግብፃውያንም በፈርዖንና በሰረገሎቹ በፈረሰኞቹም ላይ ክብር ባገኘሁ ጊዜ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ።” በእስራኤልም ሠፈር ፊት ይሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ከኋላቸው ሄደ፤ የደመናውም ዓምድ ከፊታቸው ፈቀቅ ብሎ ከኋላቸው ሄደ፤ በግብፃውያን ሰፈርና በእስራኤል ሰፈር መካከልም ገባ፤ ደመናና ጨለማ ነበረ፥ ሌሊቱን አበራ፤ ሌሊቱን ሙሉ ማንም አልቀረበም። ሙሴም በባሕሩ ላይ እጁን ዘረጋ፤ ጌታም ሌሊቱን ሁሉ ጽኑ የምሥራቅ ነፋስ አምጥቶ ባሕሩን አስወገደው፥ ባሕሩንም ደረቅ ምድር አደረገው፥ ውኆችም ተከፈሉ። የእስራኤልም ልጆች በባሕሩ መካከል በደረቅ ምድር ሄዱ፤ ውኃውም በቀኛቸውና በግራቸው ግድግዳ ሆነላቸው። ግብፃውያንም፥ የፈርዖን ፈረሶችና ሰረገሎች ፈረሰኞቹም ሁሉ፥ እያሳደዱ በኋላቸው ወደ ባሕር መካከል ገቡ። ንጋትም በሆነ ጊዜ ጌታ በእሳትና በደመና ዓምድ ሆኖ የግብፃውያንን ሠፈር ተመለከተ፥ የግብፃውያንንም ሠፈር አወከ። የሰረገሎቹንም ጎማ አሰረ፥ ወደ ጭንቅም አስገባቸው፤ ግብፃውያንም፦ “ጌታ ግብፃውያንን ይዋጋላቸዋልና ከእስራኤል ፊት እንሽሽ” አሉ። ጌታም ሙሴን፦ “እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ፥ ውኆቹም በግብፃውያን ላይ በሰረገሎቻቸው ላይ በፈረሰኞቻቸውም ላይ ይመለስ” አለው። ሙሴም እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፥ ባሕሩም ማለዳ ወደ መፍሰሱ ወደ ቀድሞ ሁኔታው ተመለሰ፤ ግብፃውያንም ከእርሱ ሸሹ፥ ጌታም ግብፃውያንን በባሕሩ መካከል ጣላቸው። ውኆቹም ተመልሰው በኋላቸው ወደ ባሕር የገቡትን ሰረገሎችን ፈረሰኞችን የፈርዖንንም ሠራዊት ሁሉ ከደኑ፤ ከእነርሱም አንድ ስንኳ አልቀረም። የእስራኤል ልጆች ግን በባሕሩ ውስጥ በደረቅ ምድር ተራመዱ፤ ውኆችም በቀኛቸውና በግራቸው ግድግዳ ሆኑላችው። ጌታም በዚያን ቀን እስራኤልን ከግብፃውያን እጅ አዳነ፤ እስራኤልም የግብፃውያንን ሞት በባሕር ዳር አዩ። እስራኤልም ጌታ በግብጽ ላይ ያደረጋትን ታላቅ ኃይል አየ፥ ሕዝቡም ጌታን ፈሩ፥ በጌታና በአገልጋዩ በሙሴ አመኑ።
ኦሪት ዘፀአት 14 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፀአት 14:15-31
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች