ዘፀአት 14:15-31
ዘፀአት 14:15-31 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “ለምን ትጮኽብኛለህ? ከብቶቻቸውን እንዲነዱ ለእስራኤል ልጆች ንገር። አንተም በትርህን አንሣ፤ እጅህንም በባሕሩ ላይ ዘርጋ፤ ክፈለውም፤ የእስራኤልም ልጆች በባሕሩ ውስጥ በየብስ ያልፋሉ። እነሆም፥ እኔ የፈርዖንንና የግብፃውያንን ልብ አጸናለሁ፤ በኋላቸውም ይገባሉ፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ፥ በሰረገሎቹም፥ በፈረሰኞቹም ላይ እከብራለሁ። ግብፃውያንም በፈርዖንና በሰረገሎቹ፥ በፈረሰኞቹም ላይ ክብር በአገኘሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” በእስራኤልም ሠራዊት ፊት ይሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ሄደ፤ የደመናውም ዐምድ ከፊታቸው ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ቆመ፤ በግብፃውያን ሰፈርና በእስራኤል ሰፈር መካከልም ገባ፤ በዚያም ጭጋግና ጨለማ ነበረ፤ ሌሊቱም አለፈ፤ ሌሊቱንም ሁሉ እርስ በእርሳቸው አልተቃረቡም። ሙሴም በባሕሩ ላይ እጁን ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም ሌሊቱን ሁሉ ጽኑ የአዜብ ነፋስ አምጥቶ ባሕሩን አስወገደው፤ ባሕሩንም አደረቀው፤ ውኃውም ተከፈለ። የእስራኤልም ልጆች በባሕሩ መካከል በየብስ ገቡ፤ ውኃውም በቀኛቸውና በግራቸው እንደ ግድግዳ ሆነላቸው። ግብፃውያንም፥ የፈርዖን ፈረሶችና ሰረገሎች፥ ፈረሰኞቹም ሁሉ እያሳደዱ በኋላቸው ወደ ባሕር መካከል ገቡ። ንጋትም በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር በእሳትና በደመና ዐምድ ሆኖ የግብፃውያንን ሠራዊት ተመለከተ፤ የግብፃውያንንም ሠራዊት አወከ። የሰረገሎቹንም መንኰራኵር አሰረ፤ ወደ ጭንቅም አገባቸው፤ ግብፃውያንም፥ “እግዚአብሔር ስለ እነርሱ ይዋጋላቸዋልና ከእስራኤል ፊት እንሽሽ” አሉ። እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ፤ ውኃውም በግብፃውያን፥ በሰረገሎቻቸውም፥ በፈረሰኞቻቸውም ላይ ይመለስ፤ ይሸፍናቸውም።” ሙሴም እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፤ ባሕሩም ማለዳ ወደ መፍሰሱ ተመለሰ፤ ግብፃውያንም ከእርሱ ሸሹ፤ እግዚአብሔርም ግብፃውያንን በባሕሩ መካከል ጣላቸው። ውኃውም ተመልሶ በኋላቸው ወደ ባሕር የገቡትን ሰረገሎችን፥ ፈረሰኞችንም፥ የፈርዖንንም ሠራዊት ሁሉ ከደነ፤ ከመጡትም ሁሉ አንድ ስንኳ የቀረ የለም። የእስራኤል ልጆች ግን በባሕሩ ውስጥ በየብስ ሄዱ፤ ውኃውም በቀኛቸውና በግራቸው እንደ ግድግዳ ሆነላቸው። እግዚአብሔርም በዚያ ቀን እስራኤልን ከግብፃውያን እጅ አዳናቸው፤ እስራኤልም ግብፃውያን እንደ ሞቱ በባሕር ዳር አዩ። እስራኤልም እግዚአብሔር በግብፃውያን ላይ ያደረጋትን ታላቂቱን እጅ አዩ፤ ሕዝቡም እግዚአብሔርን ፈሩ፤ በእግዚአብሔርም አመኑ፤ ባሪያውንም ሙሴን አከበሩ።
ዘፀአት 14:15-31 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ለምን ትጮኹብኛላችሁ? ይልቅስ እስራኤላውያንን ወደ ፊት እንዲጓዙ ንገራቸው፤ ውሃውን ለመክፈል በትርህን አንሣና እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ፤ እስራኤላውያን በባሕሩ ውስጥ በየብስ ይሻገራሉ። ተከትለዋቸው እንዲገቡም የግብጻውያንን ልብ አጸናለሁ፤ በፈርዖንና በሰራዊቱ ሁሉ፣ በሠረገሎቹና በፈረሰኞቹ ለራሴ ክብርን አገኛለሁ። በፈርዖንና በሰራዊቱ ሁሉ በከበርሁ ጊዜ፣ ግብጻውያን እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” ከዚያም ከእስራኤል ሰራዊት ፊት ፊት ሆኖ ሲሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ተመለሰና ወደ ኋላቸው መጣ፤ የደመናውም ዐምድ እንዲሁ ከፊት ተነሥቶ ከኋላቸው ቆመ፤ በግብጽና በእስራኤል ሰራዊት መካከል በመሆን፣ ሌሊቱን ሙሉ ደመናው በአንድ በኩል ጨለማን ሲያመጣ፣ በሌላው በኩል ብርሃን አመጣ፤ ስለዚህ ሌሊቱን በሙሉ አንዱ ወደ ሌላው ሊጠጋ አልቻለም። ሙሴ እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፤ እግዚአብሔር ሌሊቱን በሙሉ ብርቱ የምሥራቅ ነፋስ አስነሥቶ ባሕሩን ወደ ኋላ በማሸሽ ደረቅ ምድር አደረገው፤ ውሃውም ተከፈለ። እስራኤላውያን ውሃው በግራና በቀኝ እንደ ግድግዳ ሆኖ በየብስ በባሕሩ ውስጥ ዐለፉ። ግብጻውያንም አሳደዷቸው፤ የፈርዖን ፈረሶች፣ ሠረገሎችና ፈረሰኞች በሙሉ ተከትለዋቸው ወደ ባሕሩ ገቡ። ሲነጋጋም እግዚአብሔር በእሳትና በደመና ዐምድ ሆኖ የግብጻውያንን ሰራዊት ቍልቍል ተመለከተ፤ በግብጻውያን ሰራዊት ላይም ሽብር ላከባቸው። መንዳት እንዳይችሉም የሠረገላዎቹን መሽከርከሪያዎች አቈላለፈባቸው፤ ግብጻውያኑም፣ “ከእስራኤላውያን እንሽሽ! እግዚአብሔር ግብጽን እየተዋጋላቸው ነው” አሉ። ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን፣ “ውሃው ግብጻውያንን ሠረገሎቻቸውንና ፈረሰኞቻቸውን ተመልሶ እንዲሸፍናቸው እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ” አለው። ሙሴም እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፤ ንጋት ላይም ባሕሩ ወደ ቀድሞ ቦታው ተመለሰ። ግብጻውያን ከውሃው ሸሹ፤ እግዚአብሔርም ግብጻውያንን በባሕሩ ውስጥ ጣላቸው። ውሃውም ተመልሶ እስራኤላውያንን ተከትለው ወደ ባሕሩ የገቡትን ሠረገሎች፣ ፈረሰኞች፣ መላውን የፈርዖን ሰራዊት ሁሉ ሸፈነ። አንድም እንኳ አልተረፈም። እስራኤላውያን ግን ውሃው ግራና ቀኝ እንደ ግድግዳ ሆኖ፣ በደረቅ ምድር ባሕሩን ተሻገሩ። በዚያች ዕለት እግዚአብሔር እስራኤልን ከግብጻውያን እጅ አዳናቸው፤ እስራኤልም የግብጻውያን ሬሳ በባሕሩ ዳርቻ ወድቆ ተመለከቱ። እስራኤላውያን እግዚአብሔር በግብጻውያን ላይ ያደረገውን ታላቅ ኀይል ባዩ ጊዜ፣ እግዚአብሔርን ፈሩ፤ በእግዚአብሔርና በባሪያው በሙሴም አመኑ።
ዘፀአት 14:15-31 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ “ለምን ትጮኽብኛለህ? እንዲጓዙ ለእስራኤል ልጆች ንገር። አንተም በትርህን አንሣ፤ እጅህንም በባህሩ ላይ ዘርጋ፤ ክፈለውም፤ የእስራኤልም ልጆች በባህሩ ውስጥ በየብስ ያልፋሉ። እነሆም እኔ የግብፃውያንን ልብ አጸናለሁ፤ በኋላቸውም ይገባሉ፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ በሰረገሎቹም በፈረሰኞቹም ላይ ክብር አገኛለሁ። ግብፃውያንም በፈርዖንና በሰረገሎቹ በፈረሰኞቹም ላይ ክብር ባገኘሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” በእስራኤልም ሠራዊት ፊት ይሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ሄደ፤ የደመናውም ዓምድ ከፊታቸው ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ቆመ፤ በግብፃውያን ሰፈርና በእስራኤል ሰፈር መካከልም ገባ፤ በዚያም ደመናና ጨለማ ነበረ፤ በዚህ በኩል ግን ሌሊቱን አበራ፤ ሌሊቱንም ሁሉ እርስ በእርሳቸው አልተቃረቡም። ሙሴም በባሕሩ ላይ እጁን ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም ሌሊቱን ሁሉ ጽኑ የምሥራቅ ነፋስ አምጥቶ ባሕሩን አስወገደው፤ ባሕሩንም አደረቀው፤ ውኃውም ተከፈለ። የእስራኤልም ልጆች በባሕሩ መካከል በየብስ ገቡ፤ ውኃውም በቀኛቸውና በግራቸው እንደ ግድግዳ ሆነላቸው። ግብፃውያንም፥ የፈርዖን ፈረሶችና ሰረገሎች ፈረሰኞቹም ሁሉ፥ እያሳደዱ በኋላቸው ወደ ባሕር መካከል ገቡ። ንጋትም በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር በእሳትና በደመና ዓምድ ሆኖ የግብፃውያንን ሠራዊት ተመለከተ፤ የግብፃውያንንም ሠራዊት አወከ። የሰረገሎቹንም መንኮራኵር አሰረ፤ ወደ ጭንቅም አገባቸው፤ ግብፃውያንም፦ “እግዚአብሔር በግብፃውያን ላይ ይዋጋላቸዋልና ከእስራኤል ፊት እንሽሽ፤” አሉ። እግዚአብሔርም ሙሴን፦ “እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ፤ ውኃውም በግብፃውያን፥ በሰረገሎቻቸውም፥ በፈረሰኞቻቸውም ላይ ይመለስ፤” አለው። ሙሴም እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፤ ባሕሩም ማለዳ ወደ መፍሰሱ ተመለሰ፤ ግብፃውያንም ከእርሱ ሸሹ፤ እግዚአብሔርም ግብፃውያንን በባሕሩ መካከል ጣላቸው። ውኃውም ተመልሶ በኋላቸው ወደ ባሕር የገቡትን ሰረገሎችን፥ ፈረሰኞችንም፥ የፈርዖንንም ሠራዊት ሁሉ ከደነ፤ ከእነርሱም አንድ ስንኳ አልተረፈም። የእስራኤል ልጆች ግን በባሕሩ ውስጥ በየብስ ሄዱ፤ ውኆችም በቀኛቸውና በግራቸው እንደ ግድግዳ ሆኑላችው። እግዚአብሔር በዚያን ቀን እስራኤልን እንደዚህ ከግብፃውያን እጅ አዳነ፤ እስራኤልም የግብፃውያንን ሬሳ በባሕር ዳር አዩ። እስራኤልም እግዚአብሔር በግብፃውያን ላይ ያደረጋትን ታላቂቱን እጅ አዩ፤ ሕዝቡም እግዚአብሔርን ፈሩ፤ በእግዚአብሔርም በባሪያውም በሙሴ አመኑ።
ዘፀአት 14:15-31 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደ እኔ የምትጮኸው ለምንድን ነው? ይልቅስ ሰዎቹን ወደ ፊት እንዲጓዙ ንገራቸው፤ በትርህን አንሣ፤ በባሕሩም ላይ ዘርጋው፤ ውሃውም ከሁለት ይከፈላል፤ እስራኤላውያንም በደረቅ ምድር ባሕሩን አቋርጠው ይሄዳሉ፤ የግብጻውያንን ልብ ስለማደነድን ሕዝቡን ያሳድዳሉ፤ ንጉሡንና ሠራዊቱን፥ ሠረገሎቹንና ፈረሰኞቹን ድል በመንሣት ክብርን እጐናጸፋለሁ። እነርሱንም በማሸንፍበት ጊዜ ግብጻውያን እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩ ያውቃሉ።” የእስራኤልን ሠራዊት ፊት ፊት ይመራ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ወደ ኋላ ተመልሶ ደጀን ሆነ፤ የደመናውም ዐምድ አልፎ በኋላ በኩል ቆመ፤ ደመናውም በግብጻውያንና በእስራኤላውያን መካከል መጥቶ ግብጻውያንን በጨለማ ሲጋርድ ለእስራኤል ሕዝብ ግን ብርሃን ይሰጥ ነበር፤ ስለዚህ የግብጽ ሠራዊት ሌሊቱን ሙሉ ወደ እስራኤላውያን መጠጋት አልቻለም። ሙሴ እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም በብርቱ የምሥራቅ ነፋስ ባሕሩን ወደ ኋላ መለሰው፤ ነፋሱም ሌሊቱን ሙሉ በመንፈሱ፥ ባሕሩን ወደ ደረቅ ምድር ለወጠው፤ ውሃውም ከሁለት ተከፈለ፤ እስራኤላውያንም በደረቅ ምድር ባሕሩን ተሻግረው ሄዱ፤ ውሃውም በግራና በቀኝ እንደ ግድግዳ ቆሞ ነበር። ግብጻውያንም በሠረገሎቻቸው፥ በፈረሶቻቸውና በፈረሰኞቻቸው እየተረዱ አሳደዱአቸው፤ ተከታትለዋቸውም ወደ ባሕሩ ገቡ። ገና ጎሕ ሳይቀድ እግዚአብሔር በእሳትና በደመና ዐምድ ሆኖ የግብጻውያንን ሠራዊት በተመለከተ ጊዜ ሁሉም በፍርሃት ተጨነቁ። እግዚአብሔር የሠረገላዎቻቸውን መንኰራኲሮች ከመሬት ጋር ስላጣበቀባቸው ሠረገሎቻቸውን ነድተው ማንቀሳቀስ አልቻሉም፤ ግብጻውያንም፥ “እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ረድቶ እኛን እየተዋጋን ነው፤ ስለዚህ ከፊታቸው እንሽሽ!” ተባባሉ። እግዚአብሔርም ሙሴን፦ “እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ፤ ውሃውም በግብጻውያን፥ በሠረገሎቻቸውና በፈረሰኞቻቸው ላይ ይመለስባቸው” አለው። ስለዚህ ሙሴ እጁን ወደ ባሕሩ ዘረጋ፤ ጎሕ ሲቀድ ውሃው ወደ ቀድሞ ቦታው ተመለሰ፤ ግብጻውያንም ከውሃው ሸሽተው ለመውጣት ሞከሩ፤ እግዚአብሔር ግን በባሕር ውስጥ ጣላቸው። ውሃውም ተመልሶ እስራኤላውያንን ይከተሉ የነበሩትን ሠረገሎችን፥ ፈረሰኞችንና መላውን የግብጽ ሠራዊት ሸፈነ፤ ከእነርሱ አንድ ሰው እንኳ አልተረፈም። እስራኤላውያን ግን ውሃው በግራና በቀኝ እንደ ግድግዳ ሆኖ ስለ ቆመላቸው በደረቅ ምድር ተሻገሩ። በዚያን ቀን እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ከግብጻውያን እጅ አዳናቸው፤ በባሕር ሸሸ የተረፈረፈውንም የግብጻውያንን ሬሳ ተመለከቱ። እግዚአብሔር በእንዴት ያለ ታላቅ ኀይል ግብጻውያንን እንዳሸነፈ እስራኤላውያን ባዩ ጊዜ እግዚአብሔርን ፈሩ፤ በእግዚአብሔርና በአገልጋዩ በሙሴ አመኑ።
ዘፀአት 14:15-31 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለምን ትጮኽብኛለህ? የእስራኤልን ልጆች ጉዞ እንዲቀጥሉ ንገራቸው። አንተም በትርህን አንሣ፥ እጅህንም በባህሩ ላይ ዘርጋ፥ ክፈለውም፤ የእስራኤልም ልጆች በባህሩ ውስጥ በደረቅ ምድር ያልፋሉ። እነሆ እኔ የግብፃውያንን ልብ አጸናለሁ፥ ከኋላቸውም ይገባሉ፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ በሰረገሎቹም በፈረሰኞቹም ላይ ክብር አገኛለሁ። ግብፃውያንም በፈርዖንና በሰረገሎቹ በፈረሰኞቹም ላይ ክብር ባገኘሁ ጊዜ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ።” በእስራኤልም ሠፈር ፊት ይሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ከኋላቸው ሄደ፤ የደመናውም ዓምድ ከፊታቸው ፈቀቅ ብሎ ከኋላቸው ሄደ፤ በግብፃውያን ሰፈርና በእስራኤል ሰፈር መካከልም ገባ፤ ደመናና ጨለማ ነበረ፥ ሌሊቱን አበራ፤ ሌሊቱን ሙሉ ማንም አልቀረበም። ሙሴም በባሕሩ ላይ እጁን ዘረጋ፤ ጌታም ሌሊቱን ሁሉ ጽኑ የምሥራቅ ነፋስ አምጥቶ ባሕሩን አስወገደው፥ ባሕሩንም ደረቅ ምድር አደረገው፥ ውኆችም ተከፈሉ። የእስራኤልም ልጆች በባሕሩ መካከል በደረቅ ምድር ሄዱ፤ ውኃውም በቀኛቸውና በግራቸው ግድግዳ ሆነላቸው። ግብፃውያንም፥ የፈርዖን ፈረሶችና ሰረገሎች ፈረሰኞቹም ሁሉ፥ እያሳደዱ በኋላቸው ወደ ባሕር መካከል ገቡ። ንጋትም በሆነ ጊዜ ጌታ በእሳትና በደመና ዓምድ ሆኖ የግብፃውያንን ሠፈር ተመለከተ፥ የግብፃውያንንም ሠፈር አወከ። የሰረገሎቹንም ጎማ አሰረ፥ ወደ ጭንቅም አስገባቸው፤ ግብፃውያንም፦ “ጌታ ግብፃውያንን ይዋጋላቸዋልና ከእስራኤል ፊት እንሽሽ” አሉ። ጌታም ሙሴን፦ “እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ፥ ውኆቹም በግብፃውያን ላይ በሰረገሎቻቸው ላይ በፈረሰኞቻቸውም ላይ ይመለስ” አለው። ሙሴም እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፥ ባሕሩም ማለዳ ወደ መፍሰሱ ወደ ቀድሞ ሁኔታው ተመለሰ፤ ግብፃውያንም ከእርሱ ሸሹ፥ ጌታም ግብፃውያንን በባሕሩ መካከል ጣላቸው። ውኆቹም ተመልሰው በኋላቸው ወደ ባሕር የገቡትን ሰረገሎችን ፈረሰኞችን የፈርዖንንም ሠራዊት ሁሉ ከደኑ፤ ከእነርሱም አንድ ስንኳ አልቀረም። የእስራኤል ልጆች ግን በባሕሩ ውስጥ በደረቅ ምድር ተራመዱ፤ ውኆችም በቀኛቸውና በግራቸው ግድግዳ ሆኑላችው። ጌታም በዚያን ቀን እስራኤልን ከግብፃውያን እጅ አዳነ፤ እስራኤልም የግብፃውያንን ሞት በባሕር ዳር አዩ። እስራኤልም ጌታ በግብጽ ላይ ያደረጋትን ታላቅ ኃይል አየ፥ ሕዝቡም ጌታን ፈሩ፥ በጌታና በአገልጋዩ በሙሴ አመኑ።