እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “ለምን ትጮኽብኛለህ? ከብቶቻቸውን እንዲነዱ ለእስራኤል ልጆች ንገር። አንተም በትርህን አንሣ፤ እጅህንም በባሕሩ ላይ ዘርጋ፤ ክፈለውም፤ የእስራኤልም ልጆች በባሕሩ ውስጥ በየብስ ያልፋሉ። እነሆም፥ እኔ የፈርዖንንና የግብፃውያንን ልብ አጸናለሁ፤ በኋላቸውም ይገባሉ፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ፥ በሰረገሎቹም፥ በፈረሰኞቹም ላይ እከብራለሁ። ግብፃውያንም በፈርዖንና በሰረገሎቹ፥ በፈረሰኞቹም ላይ ክብር በአገኘሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” በእስራኤልም ሠራዊት ፊት ይሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ሄደ፤ የደመናውም ዐምድ ከፊታቸው ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ቆመ፤ በግብፃውያን ሰፈርና በእስራኤል ሰፈር መካከልም ገባ፤ በዚያም ጭጋግና ጨለማ ነበረ፤ ሌሊቱም አለፈ፤ ሌሊቱንም ሁሉ እርስ በእርሳቸው አልተቃረቡም። ሙሴም በባሕሩ ላይ እጁን ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም ሌሊቱን ሁሉ ጽኑ የአዜብ ነፋስ አምጥቶ ባሕሩን አስወገደው፤ ባሕሩንም አደረቀው፤ ውኃውም ተከፈለ። የእስራኤልም ልጆች በባሕሩ መካከል በየብስ ገቡ፤ ውኃውም በቀኛቸውና በግራቸው እንደ ግድግዳ ሆነላቸው። ግብፃውያንም፥ የፈርዖን ፈረሶችና ሰረገሎች፥ ፈረሰኞቹም ሁሉ እያሳደዱ በኋላቸው ወደ ባሕር መካከል ገቡ። ንጋትም በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር በእሳትና በደመና ዐምድ ሆኖ የግብፃውያንን ሠራዊት ተመለከተ፤ የግብፃውያንንም ሠራዊት አወከ። የሰረገሎቹንም መንኰራኵር አሰረ፤ ወደ ጭንቅም አገባቸው፤ ግብፃውያንም፥ “እግዚአብሔር ስለ እነርሱ ይዋጋላቸዋልና ከእስራኤል ፊት እንሽሽ” አሉ። እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ፤ ውኃውም በግብፃውያን፥ በሰረገሎቻቸውም፥ በፈረሰኞቻቸውም ላይ ይመለስ፤ ይሸፍናቸውም።” ሙሴም እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፤ ባሕሩም ማለዳ ወደ መፍሰሱ ተመለሰ፤ ግብፃውያንም ከእርሱ ሸሹ፤ እግዚአብሔርም ግብፃውያንን በባሕሩ መካከል ጣላቸው። ውኃውም ተመልሶ በኋላቸው ወደ ባሕር የገቡትን ሰረገሎችን፥ ፈረሰኞችንም፥ የፈርዖንንም ሠራዊት ሁሉ ከደነ፤ ከመጡትም ሁሉ አንድ ስንኳ የቀረ የለም። የእስራኤል ልጆች ግን በባሕሩ ውስጥ በየብስ ሄዱ፤ ውኃውም በቀኛቸውና በግራቸው እንደ ግድግዳ ሆነላቸው። እግዚአብሔርም በዚያ ቀን እስራኤልን ከግብፃውያን እጅ አዳናቸው፤ እስራኤልም ግብፃውያን እንደ ሞቱ በባሕር ዳር አዩ። እስራኤልም እግዚአብሔር በግብፃውያን ላይ ያደረጋትን ታላቂቱን እጅ አዩ፤ ሕዝቡም እግዚአብሔርን ፈሩ፤ በእግዚአብሔርም አመኑ፤ ባሪያውንም ሙሴን አከበሩ።
ኦሪት ዘፀአት 14 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፀአት 14:15-31
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች