ኦሪት ዘጸአት 14:15-31

ኦሪት ዘጸአት 14:15-31 አማ54

እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ “ለምን ትጮኽብኛለህ? እንዲጓዙ ለእስራኤል ልጆች ንገር። አንተም በትርህን አንሣ፤ እጅህንም በባህሩ ላይ ዘርጋ፤ ክፈለውም፤ የእስራኤልም ልጆች በባህሩ ውስጥ በየብስ ያልፋሉ። እነሆም እኔ የግብፃውያንን ልብ አጸናለሁ፤ በኋላቸውም ይገባሉ፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ በሰረገሎቹም በፈረሰኞቹም ላይ ክብር አገኛለሁ። ግብፃውያንም በፈርዖንና በሰረገሎቹ በፈረሰኞቹም ላይ ክብር ባገኘሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” በእስራኤልም ሠራዊት ፊት ይሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ሄደ፤ የደመናውም ዓምድ ከፊታቸው ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ቆመ፤ በግብፃውያን ሰፈርና በእስራኤል ሰፈር መካከልም ገባ፤ በዚያም ደመናና ጨለማ ነበረ፤ በዚህ በኩል ግን ሌሊቱን አበራ፤ ሌሊቱንም ሁሉ እርስ በእርሳቸው አልተቃረቡም። ሙሴም በባሕሩ ላይ እጁን ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም ሌሊቱን ሁሉ ጽኑ የምሥራቅ ነፋስ አምጥቶ ባሕሩን አስወገደው፤ ባሕሩንም አደረቀው፤ ውኃውም ተከፈለ። የእስራኤልም ልጆች በባሕሩ መካከል በየብስ ገቡ፤ ውኃውም በቀኛቸውና በግራቸው እንደ ግድግዳ ሆነላቸው። ግብፃውያንም፥ የፈርዖን ፈረሶችና ሰረገሎች ፈረሰኞቹም ሁሉ፥ እያሳደዱ በኋላቸው ወደ ባሕር መካከል ገቡ። ንጋትም በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር በእሳትና በደመና ዓምድ ሆኖ የግብፃውያንን ሠራዊት ተመለከተ፤ የግብፃውያንንም ሠራዊት አወከ። የሰረገሎቹንም መንኮራኵር አሰረ፤ ወደ ጭንቅም አገባቸው፤ ግብፃውያንም፦ “እግዚአብሔር በግብፃውያን ላይ ይዋጋላቸዋልና ከእስራኤል ፊት እንሽሽ፤” አሉ። እግዚአብሔርም ሙሴን፦ “እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ፤ ውኃውም በግብፃውያን፥ በሰረገሎቻቸውም፥ በፈረሰኞቻቸውም ላይ ይመለስ፤” አለው። ሙሴም እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፤ ባሕሩም ማለዳ ወደ መፍሰሱ ተመለሰ፤ ግብፃውያንም ከእርሱ ሸሹ፤ እግዚአብሔርም ግብፃውያንን በባሕሩ መካከል ጣላቸው። ውኃውም ተመልሶ በኋላቸው ወደ ባሕር የገቡትን ሰረገሎችን፥ ፈረሰኞችንም፥ የፈርዖንንም ሠራዊት ሁሉ ከደነ፤ ከእነርሱም አንድ ስንኳ አልተረፈም። የእስራኤል ልጆች ግን በባሕሩ ውስጥ በየብስ ሄዱ፤ ውኆችም በቀኛቸውና በግራቸው እንደ ግድግዳ ሆኑላችው። እግዚአብሔር በዚያን ቀን እስራኤልን እንደዚህ ከግብፃውያን እጅ አዳነ፤ እስራኤልም የግብፃውያንን ሬሳ በባሕር ዳር አዩ። እስራኤልም እግዚአብሔር በግብፃውያን ላይ ያደረጋትን ታላቂቱን እጅ አዩ፤ ሕዝቡም እግዚአብሔርን ፈሩ፤ በእግዚአብሔርም በባሪያውም በሙሴ አመኑ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}