ኦሪት ዘጸአት 14:15-31

ኦሪት ዘጸአት 14:15-31 አማ05

እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደ እኔ የምትጮኸው ለምንድን ነው? ይልቅስ ሰዎቹን ወደ ፊት እንዲጓዙ ንገራቸው፤ በትርህን አንሣ፤ በባሕሩም ላይ ዘርጋው፤ ውሃውም ከሁለት ይከፈላል፤ እስራኤላውያንም በደረቅ ምድር ባሕሩን አቋርጠው ይሄዳሉ፤ የግብጻውያንን ልብ ስለማደነድን ሕዝቡን ያሳድዳሉ፤ ንጉሡንና ሠራዊቱን፥ ሠረገሎቹንና ፈረሰኞቹን ድል በመንሣት ክብርን እጐናጸፋለሁ። እነርሱንም በማሸንፍበት ጊዜ ግብጻውያን እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩ ያውቃሉ።” የእስራኤልን ሠራዊት ፊት ፊት ይመራ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ወደ ኋላ ተመልሶ ደጀን ሆነ፤ የደመናውም ዐምድ አልፎ በኋላ በኩል ቆመ፤ ደመናውም በግብጻውያንና በእስራኤላውያን መካከል መጥቶ ግብጻውያንን በጨለማ ሲጋርድ ለእስራኤል ሕዝብ ግን ብርሃን ይሰጥ ነበር፤ ስለዚህ የግብጽ ሠራዊት ሌሊቱን ሙሉ ወደ እስራኤላውያን መጠጋት አልቻለም። ሙሴ እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም በብርቱ የምሥራቅ ነፋስ ባሕሩን ወደ ኋላ መለሰው፤ ነፋሱም ሌሊቱን ሙሉ በመንፈሱ፥ ባሕሩን ወደ ደረቅ ምድር ለወጠው፤ ውሃውም ከሁለት ተከፈለ፤ እስራኤላውያንም በደረቅ ምድር ባሕሩን ተሻግረው ሄዱ፤ ውሃውም በግራና በቀኝ እንደ ግድግዳ ቆሞ ነበር። ግብጻውያንም በሠረገሎቻቸው፥ በፈረሶቻቸውና በፈረሰኞቻቸው እየተረዱ አሳደዱአቸው፤ ተከታትለዋቸውም ወደ ባሕሩ ገቡ። ገና ጎሕ ሳይቀድ እግዚአብሔር በእሳትና በደመና ዐምድ ሆኖ የግብጻውያንን ሠራዊት በተመለከተ ጊዜ ሁሉም በፍርሃት ተጨነቁ። እግዚአብሔር የሠረገላዎቻቸውን መንኰራኲሮች ከመሬት ጋር ስላጣበቀባቸው ሠረገሎቻቸውን ነድተው ማንቀሳቀስ አልቻሉም፤ ግብጻውያንም፥ “እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ረድቶ እኛን እየተዋጋን ነው፤ ስለዚህ ከፊታቸው እንሽሽ!” ተባባሉ። እግዚአብሔርም ሙሴን፦ “እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ፤ ውሃውም በግብጻውያን፥ በሠረገሎቻቸውና በፈረሰኞቻቸው ላይ ይመለስባቸው” አለው። ስለዚህ ሙሴ እጁን ወደ ባሕሩ ዘረጋ፤ ጎሕ ሲቀድ ውሃው ወደ ቀድሞ ቦታው ተመለሰ፤ ግብጻውያንም ከውሃው ሸሽተው ለመውጣት ሞከሩ፤ እግዚአብሔር ግን በባሕር ውስጥ ጣላቸው። ውሃውም ተመልሶ እስራኤላውያንን ይከተሉ የነበሩትን ሠረገሎችን፥ ፈረሰኞችንና መላውን የግብጽ ሠራዊት ሸፈነ፤ ከእነርሱ አንድ ሰው እንኳ አልተረፈም። እስራኤላውያን ግን ውሃው በግራና በቀኝ እንደ ግድግዳ ሆኖ ስለ ቆመላቸው በደረቅ ምድር ተሻገሩ። በዚያን ቀን እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ከግብጻውያን እጅ አዳናቸው፤ በባሕር ሸሸ የተረፈረፈውንም የግብጻውያንን ሬሳ ተመለከቱ። እግዚአብሔር በእንዴት ያለ ታላቅ ኀይል ግብጻውያንን እንዳሸነፈ እስራኤላውያን ባዩ ጊዜ እግዚአብሔርን ፈሩ፤ በእግዚአብሔርና በአገልጋዩ በሙሴ አመኑ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}