ኦሪት ዘፀአት 14
14
ቀይ ባሕርን መሻገር
1ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2“እንዲመለሱና በሚግዶልና በባሕሩ መካከል፥ በበዓልጽፎንም ፊት ለፊት ባለው በፒሃሒሮት ፊት እንዲሰፍሩ የእስራኤልን ልጆች ንገራቸው፤ ከእርሱም አንጻር በባህሩ ትሰፍራላችሁ።” 3ፈርዖንም ስለ እስራኤል ልጆች፦ “በምድር ግራ በመጋባት ይቅበዘበዛሉ፥ ምድረ በዳም ዘጋቻቸው” ይላል። 4እኔም የፈርዖንን ልብ አጸናለሁ፥ እርሱም ያሳድዳቸዋል፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ ላይ ክብር አገኛለሁ፤ ግብፃውያንም እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። እነርሱም እንዲሁ አደረጉ። 5ሕዝቡም ማምለጣቸውን ለግብጽ ንጉሥ ነገሩት፤ የፈርዖንና የአገልጋዮቹም ልብ በሕዝቡ ላይ ተለወጠና፦ “ምንድነው ያደረግነው? እንዳያገለግለን እስራኤልን ለቀቅነው” አሉ። 6ሠረገላውንም አሰናዳ፥ ሕዝቡንም ከእርሱ ጋር ወሰደ፤ 7ስድስት መቶ የተመረጡ ሰረገሎችን፥ የግብጽንም ሰረገሎችን ሁሉ፥ የጦር አዛዦች በእያንዳንዱ ሠረገላ ላይ ነበሩ። 8ጌታም የግብጽን ንጉሥ የፈርዖንን ልብ አጸና፥ እርሱም የእስራኤልን ልጆች አሳደደ፤ ዳሩ ግን የእስራኤል ልጆች ከፍ ባለች እጅ#14፥8 ብዙ ቦታ ላይ በተዘረጋች እጅ ተብሎ ትጽፏል። አንዳንድ ትርጉሞች “በድፍረት ወጡ” ይላሉ። ወጡ። 9ግብፃውያንም የፈርዖን ፈረሶችና ሰረገሎች ፈረሰኞቹም ሠራዊቱም ሁሉ፥ አሳደዱአቸው፤ በባሕሩ በበዓልጽፎን ፊት ለፊት ባለው በፒሃሒሮት ሰፍረው አገኙአቸው።
10ፈርዖንም በቀረበ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ዓይናቸውን አነሡ፥ እነሆም ግብፃውያን ከኋላቸው እየመጡ ነበር፤ የእስራኤልም ልጆች እጅግ ፈሩ፥ ወደ ጌታም ጮኹ። 11ሙሴንም እንዲህ አሉት፦ “በግብጽ መቃብር ስለ ሌለ ነው በምድረ በዳ እንድንሞት ያወጣኸን? ከግብጽ አውጥተህ ምንድነው ያደረግህብን? 12በግብጽ ሳለን ያልንህ ቃል ይህ አይደለምን? ተወን፥ ግብፃውያንን እናገልግል፤ በምድረ በዳ ከምንሞት ብናገለግላቸው ይሻላልና።” 13ሙሴም ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፦ “አትፍሩ፥ ቁሙ፥ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የጌታን ማዳን እዩ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ለዘለዓለም አታዩአቸውምና። 14ጌታ ስለ እናንተ ይዋጋል፥ እናንተም ዝም ትላላችሁ።”
15ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለምን ትጮኽብኛለህ? የእስራኤልን ልጆች ጉዞ እንዲቀጥሉ ንገራቸው። 16አንተም በትርህን አንሣ፥ እጅህንም በባህሩ ላይ ዘርጋ፥ ክፈለውም፤ የእስራኤልም ልጆች በባህሩ ውስጥ በደረቅ ምድር ያልፋሉ። 17እነሆ እኔ የግብፃውያንን ልብ አጸናለሁ፥ ከኋላቸውም ይገባሉ፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ በሰረገሎቹም በፈረሰኞቹም ላይ ክብር አገኛለሁ። 18ግብፃውያንም በፈርዖንና በሰረገሎቹ በፈረሰኞቹም ላይ ክብር ባገኘሁ ጊዜ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ።” 19በእስራኤልም ሠፈር ፊት ይሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ከኋላቸው ሄደ፤ የደመናውም ዓምድ ከፊታቸው ፈቀቅ ብሎ ከኋላቸው ሄደ፤ 20በግብፃውያን ሰፈርና በእስራኤል ሰፈር መካከልም ገባ፤ ደመናና ጨለማ ነበረ፥ ሌሊቱን አበራ፤ ሌሊቱን ሙሉ ማንም አልቀረበም። 21ሙሴም በባሕሩ ላይ እጁን ዘረጋ፤ ጌታም ሌሊቱን ሁሉ ጽኑ የምሥራቅ ነፋስ አምጥቶ ባሕሩን አስወገደው፥ ባሕሩንም ደረቅ ምድር አደረገው፥ ውኆችም ተከፈሉ። 22#1ቆሮ. 10፥1፤2፤ ዕብ. 11፥29።የእስራኤልም ልጆች በባሕሩ መካከል በደረቅ ምድር ሄዱ፤ ውኃውም በቀኛቸውና በግራቸው ግድግዳ ሆነላቸው። 23ግብፃውያንም፥ የፈርዖን ፈረሶችና ሰረገሎች ፈረሰኞቹም ሁሉ፥ እያሳደዱ በኋላቸው ወደ ባሕር መካከል ገቡ። 24ንጋትም በሆነ ጊዜ ጌታ በእሳትና በደመና ዓምድ ሆኖ የግብፃውያንን ሠፈር ተመለከተ፥ የግብፃውያንንም ሠፈር አወከ።
25የሰረገሎቹንም ጎማ አሰረ፥ ወደ ጭንቅም አስገባቸው፤ ግብፃውያንም፦ “ጌታ ግብፃውያንን ይዋጋላቸዋልና ከእስራኤል ፊት እንሽሽ” አሉ።
የአሳዳጆቹ መስጠም
26ጌታም ሙሴን፦ “እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ፥ ውኆቹም በግብፃውያን ላይ በሰረገሎቻቸው ላይ በፈረሰኞቻቸውም ላይ ይመለስ” አለው። 27ሙሴም እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፥ ባሕሩም ማለዳ ወደ መፍሰሱ ወደ ቀድሞ ሁኔታው ተመለሰ፤ ግብፃውያንም ከእርሱ ሸሹ፥ ጌታም ግብፃውያንን በባሕሩ መካከል ጣላቸው። 28ውኆቹም ተመልሰው በኋላቸው ወደ ባሕር የገቡትን ሰረገሎችን ፈረሰኞችን የፈርዖንንም ሠራዊት ሁሉ ከደኑ፤ ከእነርሱም አንድ ስንኳ አልቀረም። 29የእስራኤል ልጆች ግን በባሕሩ ውስጥ በደረቅ ምድር ተራመዱ፤ ውኆችም በቀኛቸውና በግራቸው ግድግዳ ሆኑላችው። 30ጌታም በዚያን ቀን እስራኤልን ከግብፃውያን እጅ አዳነ፤ እስራኤልም የግብፃውያንን ሞት በባሕር ዳር አዩ። 31እስራኤልም ጌታ በግብጽ ላይ ያደረጋትን ታላቅ ኃይል አየ፥ ሕዝቡም ጌታን ፈሩ፥ በጌታና በአገልጋዩ በሙሴ አመኑ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፀአት 14: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ