ኦሪት ዘዳግም 32:1-43

ኦሪት ዘዳግም 32:1-43 መቅካእኤ

“ሰማያት ሆይ፥ አድምጡ፥ እኔም እናገራለሁ፤ ምድርም የአፌን ቃሎች ትስማ። ትምህርቴ እንደ ዝናብ ይዝነብ፤ ንግግሬ እንደ ጠል ይንጠባጠብ፤ በልምላሜ ላይ እንደ ጤዛ፥ በሣርም ላይ እንደ ካፊያ፥ በቡቃያም ላይ እንደሚወርድ ዝናብ፥ የጌታን ስም አውጃለሁ፤ ለአምላካችን ታላቅነትን ስጡ!” “እርሱ ዐለት፥ ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ የቀና ነው፥ የታመነ አምላክ፥ ተንኮል የሌለበት፥ እርሱ ቀጥተኛና ጻድቅ ነው። በእርሱ ፊት ክፋት ፈጽመዋል፤ ከነውራቸው የተነሣ ከእንግዲህ ልጆቹ አይደሉም፤ ወልጋዳና ጠማማ ትውልዶች ናቸው። አንተ የማታስተውልና ኀሊና ቢስ ሕዝብ፥ ለጌታ ምላሽህ እንዲህ ነው? እርሱ አባትህ አይደለምን? የፈጠረህና የሠራህ ያጸናህም እርሱ አይደለምን?” “የቀድሞውን ዘመን አስታውስ፤ የብዙ ትውልድንም ዓመታት አስተውል፥ አባትህን ጠይቅ፥ እርሱም ያስታውቅሃል፥ ሽማግሌዎችህን ጠይቅ፥ እነርሱም ይነግሩሃል። ልዑል ለአሕዛብ ርስታቸውን ባወረሰ ጊዜ፥ የሰውን ልጆች በለየ ጊዜ፥ እንደ እስራኤል ልጆች ቍጥር የአሕዛብን ድንበር አቆመ። ሕዝቡ የጌታ ድርሻ ነው፥ ያዕቆብም የተለየ ርስቱ ነው።” “በምድረ በዳ በጥማት፥ የነፋስ ጩኸትም በሞላበት በምድረ በዳ አገኘው፥ መከታ ሆነለት፥ ተጠነቀቀለትም፥ እንደ ዐይን ብሌኑም ጠበቀው። ንስር ጎጆዋን ቆስቁሳ፥ በጫጩቶቿም ላይ እንደምትሰፍፍ፥ ክንፎቹን ዘርግቶ ይወስደዋል፥ በክንፎቹም ያዝለዋል። ጌታ ብቻውን መራው፥ ከእርሱም ጋር ባዕድ አምላክ አልነበረም።” “በምድር ከፍታ ላይ አወጣው፥ የምድሩንም ፍሬ በላ፤ ከዓለትም ድንጋይ ማር፥ ከባልጩትም ድንጋይ ዘይት መገበው። የላሙንም ቅቤ፥ የመንጋውንም ወተት፥ ከሰቡት በጎችና ፍየሎች ጋር፥ የባሳንንም አውራ በጎች፥ ፍየሎችም፥ ከምርጥ ስንዴ ጋር በላህ፥ ከወይኑም ዘለላ የወይን ጠጅ ጠጣህ።” “ይሹሩን ወፈረ፥ ረገጠ፥ ወፈረ፥ ደነደነ፥ ሰባ፥ የፈጠረውንም አምላክ ተወ፥ የመድኃኒቱንም አምላክ ናቀ። በባዕዳን አማልክታቸው አስቀኑት፥ በርኩሰታቸውም አስቆጡት። አምላክ ላልሆኑ አጋንንት፥ ለማያውቋቸውም አማልክት፥ በቅርብ ጊዜ ለተነሡ ለአዲሶች አባቶቻቸውም ላልፈሩአቸው አማልክት ሠዉ። የወለደህን አምላክ ተውህ፥ የፈጠረህን እግዚአብሔር ረሳህ።” “ወንዶችና ሴቶች ልጆችም ስላስቆጡት ጌታ አይቶ ጣላቸው። እርሱም እንዲህ አለ፦ ‘ጠማማ ትውልድ፥ ያልታመኑም ልጆች ናቸውና፥ ፊቴን እሰውርባቸዋለሁ፥ ፍጻሜያቸው ምን እንደሆነ አያለሁ። አምላክ ባልሆነው አስቀኑኝ፤ በምናምንቴዎቻቸውም አስቆጡኝ፥ እኔም በተናቀ ሕዝብ አስቀናቸዋለሁ፥ በማያስተውል ሕዝብ አስቆጣቸዋለሁ። እሳት ከቁጣዬ ትነድዳለች፤ እስከ ሲኦል ድረስ ታቃጥላለች፤ ምድርንም ከፍሬዋ ጋር ትበላለች፤ የተራሮችን መሠረትም ታነድዳለች።’” “‘በመዓት ላይ መዓት አመጣባቸዋለሁ፤ ፍላጻዬንም በእነርሱ ላይ እጨርሳለሁ። በሚያቃጥል ንዳድና በራብ ያልቃሉ፤ በወረርሽኝ መቅሠፍት ይጠፋሉ፤ ተናካሽ አውሬዎችን፥ ከሚሳቡ መርዘኛ እባቦችን ጋር እሰድባቸዋለሁ። ወጣት ወንዶችና ሴቶች፥ ሕፃኑንም ከሽማግሌ ጋር፥ በየመንገዱ ላይ በጦርነት፥ በቤትም ውስጥ በድንጋጤ ያጠፋቸዋል። ፈጽሜ እበትናቸዋለሁ፤ ከሰዎችም መካከል መታሰቢያቸውን አጠፋለሁ፤’ አልኩ። ነገር ግን ጠላቶቻቸው እንዳይታበዩ፦ ‘እጃችን ከፍ ከፍ አለች እንጂ ጌታ ይህን ሁሉ አላደረገም’ እንዳይሉ፥ ስለ ጠላት ትንኮሳ አሰብኩ።” “ምክር ያጡ ሕዝብ ናቸው፥ ማስተዋልም የሌላቸው ናቸው። አስተዋዮች ቢሆኑ፥ ይህንን በተገነዘቡ፥ ፍጻሜያቸውንም ባሰቡ ነበር! እርሱ አንባቸው ካልሸጣቸው፥ ጌታም አሳልፎ ካልሰጣቸው፥ እንዴት አንዱ ሺህን ያሳድዳል? ሁለቱስ እንዴት ዐሥር ሺህ ያባርራሉ? ጠላቶቻችን እንኳ እንደሚስማሙበት፥ ዓለታቸው እንደ እኛ ዓለት አይደለም። ወይናቸው ከሰዶም ወይን፥ ከገሞራም እርሻ ይመጣል፤ ፍሬያቸው በመርዝ የተሞላ፥ ዘለላቸውም መራራ ነው። ወይናቸው የእባብ መርዝ፥ የጨካኝ እፉኝት መርዝ ነው።” “ይህስ በእኔ ዘንድ የተጠበቀ፥ በመዝገቤስ የታተመ አይደለምን? በቀልና ብድራት መመለስ የእኔ ነው፤ እግራቸው የሚሰናከልበት ጊዜው፥ የመጥፊያቸው ቀን ቀርቧልና፥ የሚመጣባቸው ፍርድ ይፈጥናል። ጌታ ለሕዝቡ ይፈርዳል፥ ለአገልጋዮቹም ያዝናል። ኃይላቸውም እንደደከመ፥ የታሰረም ሆነ የተለቀቀ እንደሌለ ሲያዩ፥ እርሱም ሕዝቡን እንዲህ ይላል፦ ‘ይታመኑባቸው የነበሩት አምባዎች፥ አማልክቶቻቸው የት ናቸው? እነዚያ የመሥዋዕታቸውን ስብ የበሉ፥ የመጠጥ መለማመኛቸውንም ወይን የጠጡ? እስቲ እነርሱ ይነሡና ይርዱአችሁ! እስቲ መጠጊያም ይሁኑላችሁ!’” “እኔ ራሴ እርሱ እንደሆንሁ እዩ፤ ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ እኔ እገድላለሁ፤ በሕይወትም አኖራለሁ፤ እኔ አቆስላለሁ፤ እፈውሳለሁም፤ ከእጄም የሚያስጥል ማንም የለም። እጄን ወደ ሰማይ ዘርግቼ፥ ለዘለዓለም እኔ ሕያው እንደሆንኩ፥ እምላለሁ። የሚያንጸባርቅ ሰይፌን ከሳልኩ፥ እጄም ለፍርድ ካነሳችው፥ ጠላቶቼንም እበቀላለሁ፥ ለሚጠሉኝም ፍዳቸውን እመልሳለሁ። ከተገደሉት ደም፥ ከተማረኩትም ደም፥ ከጠላት አለቆችም ራስ፥ ፍላጾቼን በደም አሰክራለሁ፥ ሰይፌም ሥጋ ይቆራርጣል።” “የአገልጋዮቹን ደም ይበቀላልና፥ ጠላቶቹንም ይበቀላቸዋልና፥ ምድሪቱንና ሕዝቡን ይክሳልና፥ እናንተ አሕዛብ ሆይ፥ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ።”