ሰማይ ሆይ፥ የምናገረውን አድምጥ፤ ምድርም ከአፌ የሚወጣውን ቃል ትስማ፤ ትምህርቴ እንደ ዝናብ ይዝነብ፤ ንግግሬም እንደ ጤዛ ይንጠባጠብ፤ በሣር ላይ እንደ ለስላሳ ዝናብ፥ በቡቃያም ላይ እንደሚወርድ ካፊያ፥ የእግዚአብሔርን ስም ዐውጃለሁ፤ የአምላካችንን ታላቅነት ተናገሩ። “እርሱ ምሽጋችን ነው፤ ሥራዎቹም ፍጹሞች ናቸው፤ መንገዶቹም ሁሉ የቀኑ ናቸው፤ የማይሳሳት ታማኝ አምላክ፥ እርሱም ቀጥተኛና እውነተኛ ነው። በእርሱ ፊት የረከሰ ጠባያቸውን አሳዩ፤ በዚህም የእርሱ ልጆች አለመሆናቸው ይታወቃል፤ እነርሱ የተበላሹና ጠማማ ትውልድ ናቸው። እናንተ ሞኞችና ኅሊና ቢሶች፥ የእግዚአብሔርን ዋጋ የምትከፍሉ በዚህ ዐይነት ነውን? እርሱ የፈጠራችሁ አባታችሁ አይደለምን? የመሠረታችሁስ እርሱ አይደለምን? “የቀድሞውን ዘመን አስታውስ፤ ከዘመናት በፊት የነበረውን አስተውል፤ አባትህን ጠይቅ እርሱም ይነግርሃል፤ ሽማግሌዎችህን ጠይቅ እነርሱም ይተርኩልሃል። ልዑል እግዚአብሔር ለሕዝቡ ርስታቸውን ባከፋፈለ ጊዜ፥ የሰውን ዘር በለያየ ጊዜ፥ እንደ እስራኤል ልጆች ቊጥር ብዛት፥ ለሕዝቡ ድንበርን ሠራላቸው። እስራኤል የእግዚአብሔር ድርሻ ነው፤ ያዕቆብም አንጡራ ሀብቱ ነው። “በነፋሻማ ባዶ በረሓ በምድረ በዳ አገኘው፤ መከታ ሆነለት፤ ጠበቀውም፤ እንደ ዐይን ብሌኑም ተንከባከበው። በጫጩቶችዋ ላይ እንደምታንዣብብ፥ ጎጆዋን እንደምትጠብቅ ንስር፥ እርሱን ለመያዝ ክንፎቹን ይዘረጋል፤ በክንፎቹም ጫፍ ይደግፈዋል። እግዚአብሔር ብቻውን መራው፤ ባዕድ አምላክ ከእርሱ ጋር አልነበረም። “በከፍተኛ ቦታ ላይ አኖረው፤ የምድሩንም ምርት መገበው፤ ከቋጥኝ የተገኘውን ማርና ከድንጋያማ መሬት ከበቀለው ወይራ የተገኘውን ዘይት መገበው። ከከብቶች፥ ከበጎችና ከፍየሎች መንጋ በሚገኝ ወተትና ዕርጎ፥ ከባሳን በሚገኙ ምርጥ ጠቦቶች፥ አውራ በጎች፥ ኰርማዎችና ፍየሎች ጮማ ሥጋ ከምርጥ ስንዴ ዳቦ ጋር መገባቸው። እናንተም ሕዝቦቹ ከቀይ ወይን ዘለላ ጭማቂ የወይን ጠጅ ጠጣችሁ። “እስራኤላውያንም ወፈሩ፤ ዐመፁም። በጣም በልተው ወፈሩ፤ ሰቡ፤ የፈጠራቸውንም አምላክ ተዉ፤ መጠጊያ አዳኛቸውን አቃለሉ። እግዚአብሔርን በጣዖት አምልኮ አስቀኑት፤ በሚያደርጉትም ክፉ ነገር ሁሉ አስቈጡት። ከዚህ በፊት ላላወቁአቸው፥ በቅርቡ አዲስ ለመጡ፥ ለአምላክ ሳይሆን ለአጋንንት የቀድሞ አባቶቻቸው ላላመለኩአቸው አማልክት መሥዋዕት አቀረቡ። ያስገኛቸውን አምላክ ተዉ፤ የፈጠራቸውንም እግዚአብሔር ረሱ። “ሴቶችና ወንዶች ልጆቻቸው ስላስቈጡት እግዚአብሔር አስወገዳቸው። ‘ፊቴን ከእነርሱ እሰውራለሁ፤ መጨረሻቸው ምን እንደሚሆን አያለሁ፤ እነርሱ የተበላሸ ትውልድ እምነት የሚጣልባቸው ልጆች አይደሉም’ አለ። እውነተኛ ባልሆኑ አማልክት አስቀንተውኛል፤ ዋጋቢስ በሆኑ ጣዖቶቻቸው አስቈጥተውኛል፤ በተናቀ ሕዝብ አስቀናቸዋለሁ፤ በማያስተውል ሕዝብ አስቈጣቸዋለሁ። በቊጣዬ እሳት ይቀጣጠላል፤ እስከ ሲኦል ጥልቀት ድረስ ይነዳል፤ ምድርንና ምርቱን ይበላል። ቃጠሎውም እስከ ተራራዎች መሠረት ድረስ ያቃጥላል። “ተከታታይ ጥፋት አመጣባቸዋለሁ፤ ፍላጻዎቼን ሁሉ በእነርሱ ላይ እጨርሳለሁ። የሚጨርስ ራብ በእነርሱ ላይ እልካለሁ፤ በወረርሽኝና በመቅሠፍት ያልቃሉ፤ ተናካሽ አውሬዎችንና መርዘኛ ተናዳፊ እባቦችን እሰድባቸዋለሁ። በየመንገዱ ላይ ጦርነት ልጅ አልባ ያደርጋቸዋል፤ በቤት ውስጥ ፍርሀት ይሰፍናል፤ ወጣት ወንዶችና ሴቶች፥ ሕፃናትና ሽማግሌዎችም ያልቃሉ። እኔ ፈጽሜ እደመስሳቸዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ የሚያስታውሳቸው አይኖርም፤ ነገር ግን ጠላቶቻቸው ‘አሸናፊዎች እኛ ነን እንጂ እግዚአብሔር አይደለም’ ብለው በመታበይ ያስቈጡኛል ብዬ አስባለሁ። “የእስራኤል ሕዝብ አእምሮ ቢሶች ናቸው፤ አያስተውሉምም። ምነው ብልኆች ሆነው ይህን ባስተዋሉና፤ መጨረሻውንም በተገነዘቡ ነበር! ፈጣሪአቸው አሳልፎ ካልሰጣቸውና አምላካቸውም ካልተዋቸው በቀር እንዴት አንዱ ሺሁን ያሳድዳል? ወይም ሁለቱ ዐሥር ሺሁን ያባርራሉ? ጠላቶቻችን እንኳ እንደሚስማሙበት የእነርሱ አምላክ እንደ እኛ አምላክ አይደለም። ጠላቶቻችን እንደ ሰዶምና ገሞራ የረከሱ ናቸው፤ እነርሱም መራራና መርዘኛ ፍሬ እንደሚሰጥ የወይን ተክል ናቸው። ወይናቸው እንደ እባብ መርዝ ነው፤ እንደ ክፉ እፉኝትም መርዝ ነው። “ጠላቶቻችን የፈጸሙት በደል በእግዚአብሔር መዝገብ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል። የምበቀል እኔ ነኝ ለሁሉም እንደየሥራቸው እከፍላለሁ፤ የጥፋታቸው ቀን ስለ ደረሰ ይሰናከላሉ፤ ፈጥነውም ይጠፋሉ። ኀይል ማጣታቸውን ሲያይ፥ እግዚአብሔር ለአገልጋዮቹ ይራራል፤ ነጻም፥ ባሪያም ሳይለይ ጌታ ለሕዝቡ ይፈርዳል። እግዚአብሔርም ሕዝቡን እንዲህ ብሎ ጠየቀ፦ ‘የሚተማመኑባቸው አማልክቶቻቸው የት አሉ? ከዚያም የተማመኑበት አለት አማልክቶቻቸውስ የት አሉ’ ይላል። የመሥዋዕታቸውን ስብ የበሉ፥ የወይን ቊርባናቸውን የጠጡ አማልክታቸው ተነሥተው ይርዱአቸው፤ መጠጊያም ይሁኑአቸው። “አምላክ እኔ ብቻ መሆኔን ዕወቁ፤ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ የምገድልም፥ ሕይወትንም የምሰጥ እኔ ነኝ፤ አቈስላለሁ፤ እፈውሳለሁም ከእጄ ማንም ሊያድን አይችልም እጄን ወደ ሰማይ ዘርግቼ እንዲህ በማለት እምላለሁ፦ ‘እኔ ለዘለዓለም ሕያው ነኝ፤ የሚያንጸባርቅ ሰይፌን እስለዋለሁ፤ እኔም ፍርድን እፈርዳለሁ፤ ጠላቶቼንም እበቀላለሁ፤ ለሚጠሉኝም ዋጋቸውን እሰጣለሁ። ከተገደሉትና ከተማረኩት ከጠላት መሪዎችም ራስ ደም ፍላጻዎቼን አሰክራለሁ፤ ሰይፌ የጠላትን ሥጋ ይቈራርጣል።’ “ሕዝቦች ሆይ፥ እግዚአብሔር የአገልጋዮቹን ደም ይበቀላል፤ ጠላቶቹንም ይበቀላቸዋል፤ የሚጠሉትን ቀጥቶ የሕዝቡን ኃጢአት ያስተሰርያል፤ የምድሪቱን ርኲሰት ያነጻል ስለዚህ ከእርሱ ሕዝብ ጋር ደስ ይበላችሁ።”
ኦሪት ዘዳግም 32 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘዳግም 32:1-43
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች