ሰማያት ሆይ፤ አድምጡ፤ እኔም እናገራለሁ፤ ምድር ሆይ፤ አንቺም የአፌን ቃል ስሚ። ትምህርቴ እንደ ዝናብ ትውረድ፤ ቃሌም እንደ ጤዛ ይንጠባጠብ፤ በቡቃያ ሣር ላይ እንደ ካፊያ፣ ለጋ ተክልም ላይ እንደ ከባድ ዝናብ ይውረድ። እኔ የእግዚአብሔርን ስም ዐውጃለሁ፤ የአምላካችንን ታላቅነት አወድሱ! እርሱ ዐለት፣ ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ ትክክል ነው፤ የማይሳሳት ታማኝ አምላክ፣ ቀጥተኛና ጻድቅ አምላክም እርሱ ነው። በርሱ ላይ ክፋት ፈጽመዋል፤ ከነውራቸው የተነሣ ከእንግዲህ ልጆቹ አይደሉም፤ ወልጋዳና ጠማማ ትውልዶች ናቸው። አንተ ሞኝና ጥበብ የጐደለህ ሕዝብ፣ ለእግዚአብሔር የምትመልስለት በዚህ መንገድ ነውን? አባትህ ፈጣሪህ፣ የሠራህና ያበጀህ እርሱ አይደለምን? የጥንቱን ዘመን አስታውስ፤ አባትህን ጠይቅ፤ ይነግርሃልም፤ ሽማግሌዎችህንም ጠይቅ፤ ያስረዱሃል። ልዑል ለአሕዛብ ርስታቸውን በሰጠ ጊዜ፣ የሰውንም ዘር በለያየ ጊዜ፣ በእስራኤል ልጆች ቍጥር ልክ፣ የአሕዛብን ርስት ድንበር ለየ፤ የእግዚአብሔር ድርሻ የገዛ ሕዝቡ፣ ያዕቆብ የተለየ ርስቱ ነውና። እርሱን በምድረ በዳ፣ ባዶና ጭው ባለ በረሓ ውስጥ አገኘው፤ ጋሻ ሆነው፤ ተጠነቀቀለትም፤ እንደ ዐይኑ ብሌን ጠበቀው። ንስር ጐጆዋን በትና፣ በጫጩቶቿም ላይ እንደምትረብብ፣ እነርሱን ለመያዝ ክንፎቿን እንደምትዘረጋ፣ በክንፎቿም እንደምትሸከማቸው፣ እግዚአብሔር ብቻ መራው፤ ምንም ባዕድ አምላክ ዐብሮት አልነበረም። በምድር ከፍታ ላይ አወጣው፤ የዕርሻንም ፍሬ መገበው። ከዐለት ድንጋይ ማር አበላው፤ ከባልጩትም ድንጋይ ዘይት መገበው። የላሙንና የበጉን መንጋ ቅቤና ወተት፣ የሰቡትን በጎችና ፍየሎች፣ የባሳንን ምርጥ አውራ በግ፣ መልካም የሆነውንም ስንዴ፣ ማለፊያውንም የወይን ጠጅ። ይሹሩን ወፈረ፤ ረገጠ፤ ጠገበ፤ ሰውነቱ ደነደነ፤ ለሰለሰ፤ የፈጠረውንም አምላክ ተወ፤ መጠጊያ ዐለት የሆነውን አዳኙንም ናቀ። በባዕዳን አማልክታቸው አስቀኑት፤ በአስጸያፊ ጣዖቶቻቸውም አስቈጡት። አምላክ ላልሆኑ አጋንንት፦ ላላወቋቸው አማልክት፣ ከጊዜ በኋላ ለተነሡ አማልክት፣ አባቶቻችሁ ላልፈሯቸው አማልክት ሠዉ። አባት የሆነህን ዐለት ከዳኸው፤ የወለደህን አምላክ ረሳኸው። እግዚአብሔር ይህን አይቶ ናቃቸው፤ በወንድና በሴት ልጆቹ ተቈጥቷልና። እርሱም፣ “ፊቴን ከእነርሱ እሰውራለሁ፤ መጨረሻቸው ምን እንደሚሆንም አያለሁ” አለ፤ ጠማማ ትውልድ፣ የማይታመኑም ልጆች ናቸውና። አምላክ ባልሆነው አስቀኑኝ፤ በከንቱ ጣዖቶቻቸው አስቈጡኝ። እኔም ሕዝብ ባልሆነው አስቀናቸዋለሁ፤ በሞኝ ሕዝብም አስቈጣቸዋለሁ። በቍጣዬ እሳት ተቀጣጥሏልና፤ እርሱ እስከ ሲኦል ዘልቆ ይነድዳል። ምድርን እስከ ሰብሏ ይበላል፤ የተራሮችንም መሠረት ያቀጣጥላል። “በመዓት ላይ መዓት አመጣባቸዋለሁ። ፍላጻዬንም በእነርሱ ላይ እጨርሳለሁ። የሚያጠፋ ራብ፣ በልቶ የሚጨርስ ቸነፈርና ከባድ መቅሠፍት እሰድድባቸዋለሁ፤ የአራዊትን ሹል ጥርስ፣ በምድር የሚሳብ የእባብ መርዝም እሰድድባቸዋለሁ። ሰይፍ መንገድ ላይ ያስቀራቸዋል፤ ቤታቸውም ውስጥ ድንጋጤ ይነግሣል፤ ጕልማሳውና ልጃገረዷ፣ ሕፃኑና ሽማግሌው ይጠፋሉ። እበትናቸዋለሁ፤ ከሰዎችም መካከል መታሰቢያቸውን አጠፋለሁ አልሁ፤ ነገር ግን ጠላቶቻቸው እንዳይታበዩ፣ ‘ድል ያደረገችው እጃችን እንጂ፣ እግዚአብሔር ይህን ሁሉ አላደረገም’ እንዳይሉ፣ የጠላትን መነሣሣት ሠጋሁ።” አእምሮ የጐደላቸው፣ ማስተዋልም የሌላቸው ሕዝብ ናቸው። አስተዋዮች ቢሆኑ ኖሮ ይህን በተገነዘቡ፣ መጨረሻቸውም ምን እንደሚሆን ባስተዋሉ ነበር። መጠጊያ ዐለታቸው ካልሸጣቸው፣ እግዚአብሔር ካልተዋቸው በቀር፣ አንድ ሰው እንዴት ሺሑን ያሳድዳል? ሁለቱስ እንዴት ዐሥር ሺሑን እንዲሸሹ ያደርጋሉ? የእነርሱ መጠጊያ ዐለት እንደ እኛ መጠጊያ ዐለት አይደለምና፤ ጠላቶቻችንም እንኳ ይህን አይክዱም። ወይናቸው ከሰዶም ወይን፣ ከገሞራም ዕርሻ ይመጣል፤ የወይናቸው ፍሬ በመርዝ፣ ዘለላቸውም በምሬት የተሞላ ነው። ወይናቸው የእባብ መርዝ፣ የመራዥ እባብም መርዝ ነው። “ይህ በእኔ ዘንድ ተጠብቆ ያለ፣ በመዝገቤስ የታተመ አይደለምን? በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ፤ ጊዜው ሲደርስ እግራቸው ይሰናከላል፤ የመጥፊያቸው ቀን ቀርቧል፤ የሚመጣባቸውም ፍርድ ፈጥኖባቸዋል።” ኀይላቸው መድከሙን፣ ባሪያም ሆነ ነጻ ሰው አለመቅረቱን በሚያይበት ጊዜ፣ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ይፈርዳል፤ ለአገልጋዮቹም ይራራል። እንዲህም ይላል፤ “መጠጊያ ዐለት የሆኗቸው፣ እነዚያ አማልክታቸው የት አሉ? የመሥዋዕታቸውን ሥብ የበሉ፣ የመጠጥ ቍርባናቸውንም የወይን ጠጅ የጠጡ አማልክት ወዴት ናቸው? እስኪ ይነሡና ይርዷችሁ! እስኪ መጠለያ ይስጧችሁ! “እኔ ራሴ እርሱ እንደ ሆንሁ እዩ፤ ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ እገድላለሁ፤ አድናለሁም፤ አቈስላለሁ፤ እፈውሳለሁም፤ ከእጄም የሚያስጥል ማንም የለም። እጄን ወደ ሰማይ አነሣለሁ፤ ለዘላለምም ሕያው እንደ ሆንሁ እናገራለሁ፤ የሚያብረቀርቅ ሰይፌን ስዬ፣ እጄ ለፍርድ ስትይዘው፣ ባላጋራዎቼን እበቀላቸዋለሁ፤ የሚጠሉኝንም እንደ ሥራቸው እከፍላቸዋለሁ። ሰይፌ ሥጋ በሚበላበት ጊዜ፣ ፍላጾቼ በደም እንዲሰክሩ አደርጋለሁ፤ ደሙ የታረዱትና የምርኮኞች፣ የጠላት አለቆችም ራስ ደም ነው።” አሕዛብ ሆይ፤ ከሕዝቡ ጋራ ደስ ይበላችሁ፤ እርሱ የአገልጋዮቹን ደም ይመልሳል፤ ጠላቶቹንም ይበቀላል። ምድሪቱንና ሕዝቡን ያነጻልና።
ዘዳግም 32 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘዳግም 32
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘዳግም 32:1-43
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos